“መንግሥት በሩን ከፍቷል”

0
272

የዚህ ዕትማችን እንግዳ አቶ ዘላለም ንጉሤ ናቸው፡፡ አቶ ዘላለም ከሰሞኑ “ፀሐይ በማለዳ” የተሠኘ በግብረ ገብነት ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡

አሚኮን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት በባለሙያነት እና መሪነት የሠሩት እንግዳችን ጡረታ ከወጡ በኋላም ዕውቀታቸውን ለትውልድ ለማጋራት በትጋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ግብረ ገብነትን በሚመለከት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮዽያ ግብረ ገብና ሥነ-ምግባር ማኀበር ፕሬዝዳንት ሆነው እያገለገሉ ከሚገኙት አቶ ዘላለም ጋር በግብረ ገብነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን አካፍለውናል፤ እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡

ግብረ ገብ እና ሥነ-ምግባር ምን እና ምን ናቸው?

ግብረ-ገብ  ትውፊት ነው፡፡ በጽሁፍም በቃልም የሚመጣ ትውፊት ነው፡፡ ትውፊት አስተምህሮ ማለት ነው፡፡ ሥነ-ምግባር አጥኝ ግብረ-ገብ ተጠኝ ነው፡፡ ይሄንን ዶክተር ጠና ደቦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር   “ሰውና ግብረ-ገብ” ብለው በፃፉት መፅሃፋቸው ላይ በደንብ አድርገው ገልጸውታል፡፡

አሁን እንደ ሀገር ያለንበት የግብረ-ገብነት ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ ነው ብለው ያስባሉ?

በአስተምህሮ ደረጃ ግብረ-ገብነት ለበርካታ ዓመታት ትኩረት ተነፍጎት ነበር፤ መንግሥት  ቁርጥ አድርጎ ገብረ-ገብ ብሎ ስሙን አምጥቶታል፡፡ ስለዚህ ገብረ-ገብ በአሁኑ ሰዓት የሕዝብ አጀንዳ ሆኗል፤ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ ይህን ስል ግን በተግባር ተተርጉሟል ማለት አይደለም፤ በአስተሳሰብ ደረጃ ሕዝቡ ነቅቷል፤ አስፈላጊ መሆኑን አምኖበታል እያልኩ ነው፡፡

በሀገር ደረጃም በዓለም አቀፍ ደረጃም ግብረ-ገብነትን ያስፈልገናል ወደሚለው ሃሳብ ያመጣን ነገር ምንድነው? አስፈላጊስ ነው ወይ?

በጣም አስፈላጊ ነው፡፡  ምክንያቱም   የበጎ ባሕርይ  ስጦታን  ማፍራት  ብርሃን  መፈንጠቅ    ነው፡፡ ፀሐይ በማለዳ ብለን እኛ መጽሐፍ እኮ የጻፍነው ጨለማ ውስጥ ነበርን፤ የማለዳዋ ፀሐይ አሁን ወጣች፡፡ አስቻይ ሁኔታዎች ወይም ደግሞ ምቹ ሁኔታዎች የምላቸው አንደኛ በመንግሥት ዘንድ ስሙ እየተቀነቀነ ነው፤ ግብረ-ገብ የሚለው ተተክሏል፡፡

እንደሀገር ግብረ-ገብ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ደግፎታል፤ ይህ አንዱ ምቹ ሁኔታ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ወደ ክልላችን ስናመጣ የክልላችን ትምህርት ቢሮ ቁርጠኛ ሆኖ አስጀምሮታል፤ ለዚህ ራሱን ችሎ መምህር ቀጥሮለታል፡፡

ዓለም አቀፋዊነትን (ግሎባላይዜሽን) እና የግብረ-ገብነት ሁኔታን እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው?

ቴክኖሎጂ ጥሩ ነው፤ ቴክኖሎጂ ውብ ነው፤ ሥራዎችን ያቀላጥፋል፤ ጊዜን ይቆጥባል፤ ጉልበትን ይቆጥባል፡፡ ማንነትን መዘንጋት  ሰውነትን መዘንጋት ነው፡፡ ምክንያቱም ልብስ የሚለበሰው እኮ እርቃንን ሊሸፍን ነው፡፡   አለበለዚያ ልብስ አያስፈልገንም ነበር፡፡

እርቃናችን      መሸፈን ስላለበት ነው፡፡

ጃፓን   ብትሄድ፣  ኮሪያ  ብትሄድ  ዝግ ነው፡፡ በቃ ባህላቸው ለዚህ ዝግ ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ግን አሜሪካንንም አስከንድተው እየበለጡ ነው ያሉት፡፡

መጥቀው ሄደዋል፤ በጣም፡፡ ግን ከባህላቸው አልወጡም፤ ባህላቸውን አላስደፈሩም፡፡

አሁን ማነው የኛ ልጆች አሳዳጊ? አስተማሪው ነው? ማሕበረሰቡ ነው? እስኪ ሃሳብዎን?

የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በመንግሥት ደረጃ የተፈጠረው ለዚህ ነው፡፡ የባህል   ተቋማት ተብሎ የተፈጠሩት    ለዚህ ነው፡፡ ይሄንን እንዲከላከሉ ነው፡፡

መምህሩ የአሁኑ ትውልድ ስለሆነ የድሮውን ማንነት አያውቀውም፡፡ አሁን እኛ እጅና ጓንት ነን፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ጋራ ሥንሠራ ለውጥ እያመጣን ነው፡፡ በነገራችን ላይ በባህር ዳር ትምህርት ቤቶች ላይ  ሥራ ሠርተናል፡፡ ወላጆች ላይ ነው አሁን የሚቀረን፡፡ ወላጅ ደግሞ ልጆች የሚፈልጉትን እንጂ የሚያስፈልጋቸውን እያደረገ አይደለም፡፡ አሁን ላንተም ምክሬ ልጅህን የሚፈልገውን አታድርግለት፤ የሚያስፈልገውን ግን ተቸግረህም ቢሆን አድርግለት፤ የሚያስፈልገውን አንተ ታውቃለህና፡፡

አሁን በቴክኖሎጂ የሚመራ የፀረ-ግብረ ገብነት ወጀብ አለ፡፡ እና ይሄንን እንዴት ነው መከላከል የሚቻለው?

ፀሐይ በማለዳ የተባለችው መጽሐፍ ለወላጆችም ለመምህራንም ለተማሪዎችም የተጻፈች መጽሐፍ ናት፡፡ ስለዚህ የእኛ ዘመቻ ወላጆች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ወላጅ ልጁን የሚፈልገውን ሞባይል እፈልጋለሁ ሲል ሞባይልን ማታለያ አድርጎ ነው እያሳደገ ያለው፡፡ ከዚህ እንዲታቀቡ ነው የምናደርግ፡፡

የእድሜ ደረጃቸውን መጥነን ነው፡፡ ረዣዥም  ቀሚስ  አሁን  እየተለመደ   መጥቷል፡፡

ይሄ የሥራችን ውጤት ነው፤ ታክሲም ላይ አስተምራለሁ፤ መንገድ ላይ አስተምራለሁ፤ ሌሎችም ያስተምራሉ፤ በትምህርት ቤቶች እናስተምራለን፡፡ ወላጆች ላይ በምንሠራው ሥራ ልጆች ላይ አሁን ያልካቸው ችግሮች ከቴክኖሎጂ ጋር ያለው ነገር ይቀየራል፡፡

ከመንግሥት እና ከሚመለከታቸው ተጽእኖ ሊፈጥሩ ከሚችሉ አካላት ጋር በምን ትብብር ነው እየሠራችሁ ያላችሁት?

ቀደም ሲል ብቻችንን ነበርን፡፡ አሁን ያሉት መሪዎች  ግብረ-ገብን እንደ አንድ ትምህርት መፍጠራቸው ለእኛ ምቹ ሁኔታ ነው፤ ብቻችንን አይደለንም፡፡ መንግሥት በሩን ከፍቷል፡፡ በተከፈተው፣ ቦይ በተከፈተው በር ገብቶ ደግሞ ሥራን መሥራት ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል፡፡

አሁን ቅርንጫፋችንን በቅርቡ አዲስ አበባ እንከፍታለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ወደ አርባ ምንጭ እንሄዳለን፤ ቀጥለን ደግሞ ወደ ሌሎች ክልሎች እንወጣለን፡፡ አማራ ክልል ባሉት ዞኖች ላይ ቅርንጫፎች ዘርግተን ከዚያ በኋላ በአማራ ክልል ባሉት ዞኖች እንደርሳለን፡፡ ኦሮሚያ ውስጥም እንገባለን እና እንበዛለን ማለት ነው፡፡

በመጨረሻ እንደ ሀገር ሆኖ ማየት የሚፈልጉት የግብረ-ገብነት ውጤት ምንድነው በሚለው  እንቋጭ?

የተዘራው ዘር እንክርዳዱ ብዙ ስለሆነ በአንዴ ተለቅሞ አያልቅም፡፡ ግን ደግሞ ስንዴው የጎመራ፣ የበዛ የግብረ-ገብ ዘመን ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስንዴውን ማበራከት ነው፡፡ እንክርዳዱን እየቀነስን መሄድ ነው፡፡ በእርግጠኝነት እኛ በ2040 ዓ.ም በስትራቴጂክ እቅዳችን ራእያችን ስንዴው የበዛ የግብረ-ገብ ትውልድ ይኖራል፤ ይህንን ነው ማበራከት የምፈልገው፡፡

እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!

እኔም በጣም አመሰግናለሁ!::

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here