የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በስፋት እየተተገበረ የሚገኝ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው። ይህ መርሃ ግብር በአማራ ክልል በምን መልኩ እየተመራ እንደሚገኝ፣ የችግኝ መጽደቅ ምጣኔው ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፣ ዘርፉ ስለሚፈጥረው የስራ እድል እና ስለሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከአቶ እስመለዓለም ምህረት ጋር ቆይታ አድርገናል።
አቶ እስመለዓለም ምህረት በደን ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። ሙሉ የስራ ዘመናቸውን በተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ያሳለፉ እና እያሳከፌ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ያገለገሉ አንጋፋ ባለሙያ እና መሪ ናቸው።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ቅድመ ዝግጅት ምን እንደሚመስል በማብራራት ቢጀምሩልን?
የአረንጓዴ አሻራ ስራ የአንድ ወቅት ሳይሆን የዓመቱን ሙሉ ስራ የሚጠይቅ ነው። ለምሳሌ እንደ ጽድ፣ ወይራ እና ዝግባ ያሉትን ለቀጣይ ዓመት የሚተከሉ ችግኞችን ገና ከሐምሌ ጀምረን ማዘጋጀት እንጀምራለን። የእኛ ትልቁ መርህ “እቅድ ከታች ከማህበረሰቡ መነሳት አለበት” የሚል ነው። ህብረተሰቡ ተወያይቶበት የሚተከለውን የችግኝ አይነትና ቦታ ስለሚለይ፣ እቅድ ለማውጣት ብቻ እስከ ሶስት ወር ተኩል ይወስድብናል። ቦታን ስንለይ የቦታውን ባለቤት (ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ቀበሌ) አብረን እንለያለን። በመቀጠል እንደ አየር ንብረቱ (ደጋ፣ ወይና ደጋ፣ ቆላ) ተስማሚ የሆኑ ችግኞችን በማፍላት እና ጉድጓድ በማዘጋጀት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራ ስንሰራ ከርመናል።
የዘንድሮው ተከላ አፈጻጸምስ ምን ይመስላል?
በዘንድሮው ክረምት የዝናብ መቆራረጥ ሊኖር እንደሚችል ከሜትሮሎጂ ባገኘነው ትንበያ መሰረት ተከላውን ቀደም ብለን ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በሰሜን ጎጃም መራዊ አካባቢ በይፋ ጀምረናል።
ዘንድሮ በክልሉ 1.76 ቢሊዮን ችግኝ ለማዘጋጀት አቅደን ሙሉ ለሙሉ አሳክተናል። ከ261 ሺህ ሄክታር በላይ የተከላ ቦታ የለየን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ113 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ካርታ ሰርተንለታል። ይህም ቢሮ ቁጭ ብለን የተከላ ቦታዎቹን በትክክል እንድንቆጣጠር አስችሎናል። እስካሁንም ከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
የተተከለው ችግኝ የጽድቀት ምጣኔ አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
የችግኝ ጽድቀት ምጣኔን በተመለከተ በ2009 እና 2010 አካባቢ ከ50 እስከ 60 በመቶ አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ ችግሮችን ገምግመን ስልት በመቀየራችን አሁን በአማካይ ወደ 80 እና 81 በመቶ አድርሰነዋል። ለዚህ ትልቁ ስኬት ተተካይ ችግኞች “ባለቤት” እንዲኖራቸው መደረጉና የተከላ ቦታዎች አስቀድመው መለየታቸው ነው።
የችግኞቹ ጥራት እንዴት ነው የሚረጋገጠው? ችግኞቹስ አካባቢን (አግሮ-ኢኮሎጂን) ባገናዘበ መልኩ እንዴት ይመረጣሉ?
ዋነኛው መመዘኛችን አግሮ-ኢኮሎጂካል ቀጠና ነው። የተከላ ቦታዎች ደጋ፣ ወይና ደጋ እና ቆላ ተብለው ይለያሉ። ችግኝ ሲፈላም ለየአካባቢው የአየር ንብረት የሚስማማው ተለይቶ በዛው አካባቢ እንዲፈላ ይደረጋል (ለምሳሌ የቆላው ቆላ ላይ፣ የደጋው ደጋ ላይ)። የዛፍ ዘርም በተቻለ መጠን ችግኙ ከሚፈላበት አካባቢ እንዲለቀም ይደረጋል፤ ያ ከሌለ ግዢ ይፈጸማል። ሌላው የጥራት መለኪያችን ችግኞች ወደ ተከላ የሚወጡት ቢያንስ 40 ሴንቲ ሜትር ቁመት ሲደርሱ ብቻ ነው። ይህን ካላሟሉ እዛው ችግኝ ጣቢያ ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ጋር በማስተሳሰር ረገድ ምን እየተሰራ ነው?
የምንተክላቸው ዛፎች ሁሉ የየራሳቸው ጠቀሜታ አላቸው። በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች እንከፍላቸዋለን፡-
የደን ዛፎች ለደን ሽፋን፣ ለጣውላነት እና አንዳንዶቹ ለእንስሳት መኖነት እንዲሁም ለሰው ምግብነት (እንደ ዶቅማ፣ ሾላ) የሚያገለግሉ ናቸው።
የጥምር ደን እርሻ (አግሮ-ፎረስትሪ) ከእርሻ ማሳና ከሰብል ጋር የሚስማሙ፣ አፈርን የሚያለምኑ (እንደ ዋንዛ፣ ብሳና፣ ግራር) እና የፍራፍሬ ዛፎችን (ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሙዝ) ያካትታል።
ለአካባቢ ጥበቃ የሚተከሉ በተራቆቱ መሬቶች ላይ ተከልለው ለንብ ማነቢያ፣ ለእንስሳት መኖ እና አካባቢን ለማገገም የሚውሉ ናቸው።
በተጨማሪም ዛፎችን ፈጥነው የሚደርሱ (እንደ ግራቪሊያ፣ ግራር፣ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች) እና ዘግይተው የሚደርሱ የሀገር በቀል ዛፎች (እንደ ወይራ እና ጽድ) ብለን ለይተን እንተክላለን። በተለይ አሁን ላይ የፍራፍሬ ክላስተሮችን (በመቶዎች በሚቆጠሩ ሄክታሮች ላይ) በስፋት እየሰራን እንገኛለን።
እስካሁን በተሰሩት ስራዎች የተሻለ የችግኝ እንክብካቤ እና አጠባበቅ የታየባቸውንና እንደ ተሞክሮ የሚወሰዱ አካባቢዎችን መጥቀስ ይቻላል?
አዎ፣ በስፋት ይቻላል። ቀድሞ ልምድ ለመውሰድ ወደ ሌሎች ክልሎች እንሄድ ነበር፤ አሁን ግን እያንዳንዱ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ የራሱን ሞዴል ስራ ፈጥሯል። ጥቂት ምሳሌዎችን ለመጥቀስ፡-
ከጎንቻ እስከ ደጀን ባለው መስመር፣ እንዲሁም ከመካነ ሰላም እስከ መርጦ ለማርያም እና እናርጅ አካባቢዎች ቀድሞ ምድረ-በዳ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ግን በማንኛውም የእርሻ ማሳ ላይ ዛፎች በስፋት ይታያሉ።
በአዊ ብሔረሰብ ዞን የተተከለው የዲከረንስ ግራር (ለማገዶ እና ለከሰል የሚውል) የተራቆተና አሲዳማ የሆነን መሬት ያለማና የአርሶ አደሩን ህይወት የቀየረ ትልቅ ተሞክሮ ነው። ይህ ልምድ አሁን ወደ ደቡብ ጎንደር፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ወሎና ሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ ነው። በአጠቃላይ በየትኛውም ዞን ሄዶ የተሳካ ተሞክሮ ማየትና መዘገብ ይቻላል።
የችግኝ ተከላ እና አረንጓዴ አሻራ ስራ የክረምት ዘመቻ ብቻ ነው ወይስ አመቱን ሙሉ የሚሰራ ስራ ነው?
የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ስራ የክረምት (የፓርት ታይም) ስራ ብቻ አይደለም፤ የዓመቱን ሙሉ ስራ ነው። ምክንያቱም የችግኝ ማፍላት፣ የቦታ ልየታ፣ የእቅድ ዝግጅት፣ የተከላ ጉድጓድ ዝግጅት፣ ተከላ፣ እንዲሁም ከዛም በኋላ የሚደረገው ጥበቃና እንክብካቤ አመቱን ሙሉ የሚከናወን ሰፊ ተግባር ስለሆነ ነው። አንዱ መሳካት ያለበት እቅድ ዝግጅት ላይ በቂ ጊዜ ወስዶ መስራት ነው።
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ወጣቶችን ወደ ስራ በማስገባት በኩል ያለው ሚና ምንድነው?
ይህ ዘርፍ ከፍተኛ የስራ እድል ፈጣሪ ነው። በሶስት መንገዶች የስራ እድል እንፈጥራለን። አንደኛ፣ ወጣቶች በመንግስት የችግኝ ጣቢያዎች ውስጥ በቁሳቁስ ተደግፈው ገበያ ፈላጊ የሆኑ እንደ ባህርዛፍ፣ ጌሾ እና ፍራፍሬዎችን አፍልተው እንዲሸጡ እናደርጋለን። ሁለተኛው፣ የደን ዘር አሰባሰብ ነው። ለምሳሌ ወጣቶች የግራቪሊያ ዘር ሰብስበው አንድ ኩንታል እስከ 9 ሺህ ብር ድረስ ይሸጣሉ። ሶስተኛው፣ መሬት በውል ወስደው የራሳቸውን ደን እንዲያለሙ ማድረግ ነው። ከዚህ ባለፈም በደን ጥበቃ፣ ከሰል በማክሰል፣ እጣን እና ሙጫ በማንጠር፣ እንዲሁም ሳር በማጨድ በዓመት ከ2,000 እስከ 3,000 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጠራል።
ያጋጠሟችሁ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
የደን ስራ ማለት “ተስፋን መትከል” ማለት ነው። ዛሬ ያልሰራነውን ከአስር ዓመት በኋላ ማግኘት አንችልም። ይህንን ለማድረግ ግን በርካታ ፈተናዎች አሉ።
ስራው የዓመት ሙሉ ሆኖ ሳለ፣ በቂ በጀት አለመመደቡ ሰፊ ጫና ፈጥሮብናል።
የደን ዘር ጥራት ችግርም አለ፡፡
አርሶ አደሩ ጥሩውን ዛፍ ለጣውላ ስለሚቆርጠው፣ ዘር የምንሰበስበው ጥራት ከሌላቸው ዛፎች ላይ እየሆነ ነው። ዘር የሚቆይበት የራሱ ክልል ያስፈልገናል። የባለቤትነት ስሜት ሌላው ችግር ነው፡፡
ሁሉም ሰው የተከለውን ‘የእኔ ነው’ ብሎ ካልተንከባከበው መጽደቅ አይችልም። ግልጽ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖር ተራራዎችን እንዴት በደን እንሸፍናለን ለሚለው ፈተና ነው።
ከሁሉም በላይ በጣም የሚያሳዝነው ከ1970ዎቹ ጀምሮ የነበሩ የችግኝ ጣቢያዎቻችን በከተሞች መስፋፋት ሰበብ ለኢንቨስትመንት እየተነጠቁን ነው። ከተማ ሲያድግ አረንጓዴነት አያስፈልገውም የተባለ ይመስል፣ ካርታ (ሰርተፍኬት) የላችሁም እየተባልን ቦታዎቻችንን እያጣን ነው። ይህ ጉዳይ ትልቅ የህልውና አደጋ ስለሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል እላለሁ።
ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!
እኔም በጣም አመሰግናለሁ!
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


