የላሊበላው ዳኛ ሀይማኖት አዳነ

0
252

በተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የተከበረ፤ የተወደደ፣ ለሙያው የታመነ እና ያደረም ነው፡፡ ጫናዎችን ተቋቁሞ የሕግ የበላይነትን አስከብሯል፤ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ምስጉን ዳኛ ተብሎ ተመርጧል፤ በአጠቃላይ በዳኝነት ህይወቱ ከ200 በላይ ጨዋታዎችን መርቷል፡፡ ወጣቱ ዳኛ በቅርቡ የፊፋ ፈቃድ አግኝቷል-ዓለም አቀፉ ዳኛ ሀይማኖት አዳነ፡፡

ዓለም አቀፉ ዳኛ ሀይማኖት አዳነ ላለፉት ስምንት ዓመታት በእግር ኳስ ዳኝነት አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛል፡፡ የዓለም አቀፉ ዳኛ የስፖርት ህይወት የሚጀምረው በተወለደበት እና ባደገበት ታሪካዊቷ ከተማ ላሊበላ ነው፡፡ በልጅነቱ በሁሉም የስፖርት እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት ይሳተፍ እንደነበር የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል፡፡

ህልሙ ስመጥር አስጎብኚ (Tour Guide) መሆን እንደነበር ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ የልጅነት ህልሙን አቅጣጫ ድንገት በመቀየር ወደ ስፖርት መቀላቀሉን ገልጿል፡፡ በ1990ዎቹ መጨረሻ እና በኢትዮጵያ ሚሊኒየም መጀመሪያ በክረምት ወራት በሚዘጋጁ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች (ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች ቡድን) ውስጥ በግብ ጠባቂነት በመሰለፍ ከእግር ኳስ ጋር ተዋውቋል፡፡

የሀይማኖት አዳነ የዳኝነት ፍቅር የተጠነሰሰው ግን እጅግ ባልተለመደ አጋጣሚ እንደነበር ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡ በታዳጊነቱ የፕሌይ ስቴሽን ቪዲዮ ጌም መጫወት ይወድ  እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ታዲያ በጨዋታው መሃል ጥፋት ተሰርቶ ምናባዊው ዳኛ ፊሽካ ሲነፋ ሲያይ በአዕምሮው ውስጥ ጥያቄዎች ይመላለሱ እንደነበር አስታውሷል፡፡

“ይህ ዳኛ እንዴት ነው ጥፋቱን አይቶ የሚወስነው? እንዴትስ ይሄን ሁሉ ነገር በሴኮንዶች ለይቶ ማወቅ ቻለ?” የሚል የማወቅ ጉጉት በውስጡ ይቀሰቀስበታል፡፡ ይህ የማወቅ ረሃብም በውስጡ እየተብላላ ህይወቱን የቀየረ ድንገተኛ አጋጣሚ በላሊበላ ከተማ የክረምት ውድድር ላይ ተከሰተ፡፡

በአንድ ወሳኝ ጨዋታ መሃል የተበሳጨው ረዳት ዳኛ ባንዲራውን በመጣል ሜዳውን ለቆ ወጣ፡፡ ሜዳ ዳር ቆሞ ይመለከት የነበረው የ13 ዓመቱ ታዳጊ ሀይማኖት አዳነ የወደቀውን ባንዲራ አንስቶ በመስመሩ ላይ መሮጥ እና ጨዋታውን ማስቀጠል ጀመረ፡፡ በእረፍት ሰዓት የውድድሩ አስተባባሪ እና በወቅቱ የወረዳው ስፖርት ጽ/ቤት ሃላፊ ሳይታዘዝ ጨዋታውን ማስቀጠሉን ይቃወሙታል፡፡ ይሁን እንጂ ታዳጊው ፍላጎቱን በማሳወቁ ጨዋታውን እንዲጨርስ ተደርጓል፡፡

በማግስቱ ሀይማኖት ቀድሞ ሜዳ ተገኘ፤ ድንቅ ተስፈኛ ባለ ክህሎት መሆኑን የተረዱት ዳኞችም በድጋሚ ረዳት ዳኛ ሆኖ ጨዋታዎችን እንዲመራ ፈቅደውለታል፡፡ ይህንን ተነሳሽነቱን የተመለከቱት የወረዳው የስፖርት አመራሮች ለሙያው ያለውን ተሰጥኦ ተረድተው በ2003 ዓ.ም ገና በ13 ዓመቱ የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና እንዲወስድ አደረጉ፡፡

በ2006 ዓ.ም የዳኝነት ሕጉን በተግባር ሲተረጉም ከተጫዋቾች በደረሰበት ድብደባ መጽሐፉን ከቤት አምጥቶ በማስረዳት ሕግን በተግባር ማስከበር ጀመረ፡፡ በመጀመሪያዎቹ የሀገር ውስጥ ዝቅተኛ ሊጎች እና የነጥብ ፉክክሮች ለበርካታ ጊዜያት በመዳኘት ራሱን አጎለበተ፡፡ ይህ የጽናት ጉዞ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዲይዝ አስችሎታል፤ ይህም ለአፍሪካ እና ለዓለም አቀፍ መድረኮች መሸጋገሪያ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሆኖታል፡፡

በ2009 ዓ.ም የፌደራል ዳኝነት ስልጠና አጠናቋል፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ የፌደራል ረዳት ዳኛ በመሆን በብሔራዊ ሊግ የትግራይ ዋልታ ፖሊስ ከራያ አዘቦ ያደረጉትን ጨዋታ በብቃት በመምራት የወደፊቱ ተተኪ ምርጥ ዳኛ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ በዚሁ ዓመት በሀዋሳ በተካሄደው የመላው ክልሎች ሻምፒዮና የፍፃሜ ጨዋታን በረዳት ዳኝነት በመምራት ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገር መሆኑን አረጋገጠ፡፡

በ2011 ዓ.ም “ዋና ዳኛ መሆን እፈልጋለሁ” በማለት የአካል ብቃት ፈተናውን በማለፍ ወደ ዋና ዳኝነት ተሸጋገረ፡፡ ዋና ዳኛ ሆኖ የአዲስ አበባን ደርቢ (አዲስ ክፍለ ከተማ ከአዲስ አበባ) ያደረጉትን ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና ዳኝነት በመምራት ብቃቱን አሳይቷል፡፡

ለአራት ዓመታት በከፍተኛ ሊግ ዋና ዳኛ ሆኖ ካገለገለ በኋላ በ2015 ዓ.ም ወደ ፕሪሚየር ሊግ አደገ፡፡ በዚሁ ዓመት በሩዋንዳ በተካሄደው የትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ በመጓዝ ጨዋታዎችን መርቷል፡፡ በ2016 እና በ2017 ዓ.ም በፕሪሚየር ሊጉ ባሳየው አስደናቂ ብቃት የከፍተኛ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ በመግባት ለኮከብ ዳኝነት በእጩነት መመረጡ አይዘነጋም፡፡

ሀይማኖት ዘመናዊ የስልጠና ቁሳቁስ ባልነበረበት ወቅት ብቻውን ሜዳ ላይ እየሮጠ ራሱን ለከፍተኛው መድረክ አብቅቷል፡፡ ሀይማኖት አዳነ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የፊፋ መሥፈርቶችን በማሟላት በ2018 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ዳኝነት ፈቃድ (FIFA Referee Badge) አግኝቷል፡፡

የፊፋን ባጅ ካገኘ በኋላ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ይፋዊ ጨዋታ በሩዋንዳ ኪጋሊ ተገኝቶ የሩዋንዳ እና የደሴቷን ግሪናዳን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መርቷል፡፡ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና ሙሉ ስታዲየም የታደሙበትን ይህን ታላቅ ጨዋታ  በድንቅ ብቃት በመምራት የሀገሩን ስም አስጠርቷል፡፡

ሀይማኖት አዳነ ሕግን አጥብቆ የሚያከብር፣ በማንም ጣልቃ ገብነት የማይመራ እና በራሱ ብቃት የሚተማመን ወጣት ዓለም አቀፍ ዳኛ ነው፡፡ በስምንት ዓመታት የዳኝነት ህይወቱ በአጠቃላይ ከ200 በላይ ጨዋታዎችን መርቷል፡፡ በአንድ የውድድር ዘመን ብቻ ከተካሄዱ 38 ሳምንታት ውስጥ 35ቱን ጨዋታዎች በዋና ዳኝነት በመምራት በአስደናቂ ብቃት ተወጥቷል፡፡ በውድድር ዘመኑ 171 ቢጫ እና 11 ቀይ ካርዶችን በመምዘዝ የሕግ የበላይነትን አስከብሯል፡፡

በ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ኮከብ ዋና ዳኛ ተብሎ ተመርጧል፡፡ ሕግን አጥብቆ የማክበር እና በማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት አለመመራት የዳኛ ሀይማኖት ዋነኛ መለያዎቹ ናቸው፡፡ ይህም በወጣት ዳኞች ዘንድ እንደ አርአያ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ የሀይማኖት የዳኝነት ዘይቤ ልዩ የሚያደርገው በሜዳ ላይ የሚያሳየው የተረጋጋ ባህሪ፣ ትክክለኛ ሰዓት አጠባበቁ እና በተጫዋቾች አያያዝ ይታወቃል፡፡ ይህ የተረጋጋ እና የሰለጠነ ስብዕናው ከማንም ተጫዋች ወይም አሰልጣኝ ጋር እንዳይጋጭ አስችሎታል፡፡

ዓለም አቀፉ ዳኛ ገና ብዙ መሥራት በሚያስችለው የሙያ ጉዞ እና በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ዛሬም የማይደበዝዝ ተስፋ እና ዕቅድ አለው፡፡ እንደ ቀደሙት አንጋፋ ኢትዮጵያውያን ዳኞች (እንደ ዓለም አቀፉ ዳኛ በአምላክ ተሰማ) ሀገሩን በዓለም መድረክ ለማስጠራት አልሟል፡፡ በቀጣይ የፊፋ የዓለም ዋንጫ እና በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ዋና ዳኛ ሆኖ መሳተፍ ህልሙ እንደሆነ ይነገራል፡፡።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጳጉሜ 2  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here