ድቅድቁ የክረምት ደመና ሰማዩን ጋርዶት፣ ዶፍና ጭቃ ምድርን አክብደውት፣ የሰው ልጅ ተስፋ በብርድና በጭጋግ ተውጦ ሲቆይ ልብ በጉጉት የሚናፍቀው አንድ ታላቅ ንጋት አለ፡፡
ያ ንጋት መስከረም ይባላል፡፡ በኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠርና የኅሊና ማኅደር ውስጥ መስከረም ተራ የቀን መቁጠሪያ ገጽ ሽግግር አይደለም፤ የተፈጥሮ ዳግም ልደት፣ የሰው ልጅ ተስፋ፣ የኅሊና ዕርቅና የማኅበራዊ አንድነት ፋና እንጂ፡፡
ታዲያ ይህ የብርሃን ምዕራፍ በአውደ ዓመት ዜማዎቻችን መስታዎት ሲቃኝ ምን ዓይነት ጥልቅ ውክልና ተሰጠው? እስኪ እንመርምረው።
- 1. የተፈጥሮ ዳግም ልደት እና የሥነ ውበት ጸዳል
በበዓል ዜማዎች ውስጥ መስከረም በመጀመሪያ ደረጃ የተፈጥሮ ድል አድራጊነት ማሳያ ሆኖ ይወከላል፡፡ ክረምት ጥሎት ያለፈውን ጭቃና ጭጋግ አውልቃ ምድር በቢጫና በአረንጓዴ ካባ የምትደምቅበት ድንቅ ወቅት ነው፡፡
“ፀሐይ ስትፈነጥቅ መስከረም ሲጠባ…” እንዲሁም “አበባ አየሽ ወይ? በአደይ አበባ መስከረም ጠባ…” እያሉ የሚያቀነቅኑት አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን አደይ አበባን የተፈጥሮ ጌጥ ብቻ ሳይሆን የብርሃን፣ የነጻነትና የአዲስ ሕይወት መባቻ አርማ አድርገው ይስሉታል፡፡
አደይ አበባ ሲፈነዳ ተራራው፣ ሸንተረሩና ሜዳው በፈገግታ ይሞላል፤ ገበሬውም የድካሙን ፍሬ በእሸትና በአዝመራ ማየት ይጀምራል፡፡ ጨለማው በጸዳል፣ ብርዱ በሙቀት፣ ጭንቀቱ በዕረፍት ይተካል፡፡
- 2. የይቅርታ፣ የኅሊና ዕርቅና የተስፋ ስንቅ
በዜማዎቹ ውስጥ የመስከረም ሌላኛው ጥልቅ ውክልና የሰው ልጅ ውስጣዊ ሥነ ልቦናዊ መታደስ ነው፡፡ መስከረም የዘመን ቅያሬ ብቻ ሳይሆን የቂምና የቁርሾ መሸኛ ታላቅ ምዕራፍ ተደርጎ ይገለጻል፡፡
በዳዊት ጽጌ እና ሌሎችም ዘፈኖች ላይ እንደተደመጠው “የቂም እርሾን ጥሎ ቶሎ… ቶሎ መታረቅ ነው ቶሎ…” የሚለው ዜማዊ ጥሪ የሰው ልጅ ልቡን ከጥላቻ ዝገት እንዲያጠራ ይመክራል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ “የዕርቅ ነው ዓመተ ምሕረቱ… ታየኝ ታየኝ የአውዳመት ጭሱ፣ ሰላም ፍቅር ይላል መንፈሱ…” በሚለው “የየኛዎች” እንደገና ዜማ ውስጥ እንደሚስተጋባው ያለ ይቅርታና ያለ ሰላም የሚከበር አውደ ዓመት ባዶ ነው፡፡
መስከረም የኀዘን ማቅ ተወልቆ አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት እና “የእንባ ዘመን ይውጣ የደስታ ቀን ይግባ” ተብሎ በኅብረት የሚጸለይበት የተቀደሰ የኅሊና ልደት ሆኖ ተሥሏል፡፡
- 3. የማዕድ ድምቀት፣ የስሜት ሕዋሳት ተሞክሮ እና ማኅበራዊ ልግስና
መስከረም የብቸኝነት ወር ሳይሆን የኅብረትና የአብሮነት ማሳያ ነው፡፡ በዜማዎቹ ግጥም ውስጥ የአውደ ዓመቱ ድባብ በስሜት ሕዋሳት ሕያው ሆኖ ይቀርባል፤ የተቆረሰው የድፎ ዳቦ፣ የሚንተከተከው የዶሮ ወጥ መዓዛ፣ ኩልል ያለው ጠላ እና የተዘረጋው የቄጠማ ሳር የፍቅር ማዕድ መገለጫዎች ሆነው ይወደሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ማዕዱ ለግል እርካታ ብቻ የተዘረጋ አይደለም፤ መስከረም የተራበው የሚጠግብበት፣ ደሀና ሀብታም በአንድነት የሚበሉበት የልግስና ወር ነው፡፡ በስደትና በሩቅ ያሉ ወገኖች ወደ እናት አገራቸው ጉያ የሚመለሱበት፣ አረጋውያን አባቶችና እናቶች ለትውልዱ የበረከት ምርቃት የሚያዘንቡበት ወቅትም ነው፡፡
- 4. የትውልድ ቅብብሎሽ፣ ፍቅር እና የወጣቶች ባሕላዊ ትውፊት
የመስከረም አውደ ዓመት ትውልድ ከትውልድ ጋር የሚገናኝበት የባሕል ማስተላለፊያ ድልድይ ነው፡፡ የልጃገረዶች “አበባየሆሽ” ጨዋታ፣ የወጣቶች ቺቦና ደመራ፣ እንዲሁም ነጭ የጥበብና የጃኖ አልባሳት የመስከረምን ባሕላዊ ውበት ያደምቁታል፡፡
ልጆች አደይ አበባ ይዘው በየደጃፉ እየዘፈኑ የኪስ ስጦታ ሲቀበሉ፤ አረጋውያን “ለዓመቱ በሰላም ያድርሳችሁ፣ የከርሞ ሰው ይበለን” እያሉ የሚመርቁበት ፍሥሐ የትውልድ ቅብብሎሽን ያጸናል፡፡
መስከረም የተፈጥሮ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የልብ ፍቅር የሚፈነዳበት ወቅት ነው፡፡ አደይ አበባ ሲፈነዳና ልጃገረዶች በአውደ ዓመት ወግ ሲደምቁ የተፈጥሮ ውበት ከፍቅር ጋር ተጣምሮ የሚደነቅበት አዲስ የልብ ቃል ኪዳን ይታደሳል፡፡
- 5. ብሔራዊ ሕብረ ቀለም እና መንፈሳዊ ምስጋና
በሙዚቃዎቻችን ውስጥ የሚታየው ሌላው ታላቅ እሴት መስከረም የአንድ አካባቢ፣ የአንድ እምነት ወይም የአንድ ወገን ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡
በወሎ፣ በጎንደር፣ በሸዋ፣ በጎጃም፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በጉራጌ እና በመላው የአገሪቱ ማዕዘናት ድንበር ሳይገድበው የሚዘልቅ ብሔራዊ ድልድይ ሆኖ ቀርቧል፡፡
ክርስቲያኑም ሙስሊሙም በየቤቱ የሚያከብረው የጋራ በዓል ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የሰው ልጅ ከክረምቱ ፈተና፣ ከጎርፉና ከመከራው ወጥቶ አዲሱን ዓመት እንዲያይ የፈቀደው ፈጣሪ መሆኑን በማሰብ፣ “በቸር አክርሞ ላሳየን ጸጋ… ለአሸጋገረን ዘመን በአደይ…” እያሉ ምስጋና የሚያቀርቡበት የተቀደሰ ወቅት ነው፡፡
- 6. የስደት ናፍቆት እና የአገር ፍቅር ጥሪ
በበዓል ሙዚቃዎቻችን ውስጥ የሚታየው ሌላው ልብ የሚነካ ውክልና መስከረም ለስደተኛው ወገን የሚፈጥረው ናፍቆት ነው፡፡
በባዕድ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአደይ አበባውን ውበት፣ የድፎ ዳቦውን መዓዛና የቤተሰቡን ሙቀት ሲያስታውሱ አንጀታቸው ይላወሳል፡፡
“ዘመን ቆጥሬ አገሬ ልግባ… እናት ኢትዮጵያ ለውዷ እናቴ…” እንዲሁም “በሀገር ቤትም በስደትም ያላችሁ… አውዳመት ደረሰ…” እያሉ የሚያዜሙት ድምፃውያን መስከረም የትም ቢሄድ ከኅሊና የማይፋቅ የአገር ፍቅር መግለጫ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
ወሩ የተራራቁትን የሚጣራ፣ ናፍቆትን የሚሰብርና ወደ እናት ምድር ጉያ የሚስብ ውብ ማግኔት ነው፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በኢትዮጵያ የበዓል ዜማዎች ውስጥ መስከረም ተራ የቀን መቁጠሪያ ሽግግር ሳይሆን የሰው ልጅ ከራሱ፣ ከተፈጥሮና ከፈጣሪው ጋር የሚታረቅበት ድንቅ የብርሃን መድረክ ነው፡፡
ሙዚቀኞቻችን እንደሚያስተምሩን የመስከረም እውነተኛ ድምቀት በሜዳው ላይ በሚፈነዳው ቢጫው አደይ አበባ ብቻ አይወሰንም፤ በልባችን በሚበቅለው የይቅርታ፣ የፍቅርና የአንድነት አበባ ጭምር እንጂ፡፡
ክረምቱ አልፎ ሰማዩ እንደጠራው ሁሉ፣ እኛም የቂም እርሾን አስወግደን በንጹሕ ልብ ስንቆም አዲሱ ዘመን እውነተኛ በረከት ይሆናል፡፡
ሙዚቀኞቻችን በስንኞቻቸው ያስቀመጡልን አደራ እጅግ ግልጽ ነው፤ የመስከረም እውነተኛ ድምቀት በሜዳው ላይ በሚፈነዳው አደይ አበባ ብቻ ሳይሆን በልባችን በሚለመልመው የይቅርታ፣ የዘላቂ ሰላምና የአንድነት ፍሬ ይረጋገጥ ዘንድ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!
ማረፈያ
ዘመን ሲታደስ
እኛ እኮ ለዘመን
ክንፎቹ አይደለንም ሰንኮፍ ነን ለገላው
በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው፡፡
በዕውቀቱ ሥዩም
(አቢብ በዓለሜ)
በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


