የዘመን አቆጣጠር እና የታሪክ ምዕራፎች አመጣጥ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ከመታዘብ እና አካባቢውን ከመቆጣጠር ፍላጎት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ጥንታውያን ማህበረሰቦች የፀሐይን መውጣት እና መግባት፣ የጨረቃን ቅርፅ መለዋወጥ እንዲሁም የወራት እና የወቅቶችን መፈራረቅ በማስተዋል የመጀመሪያዎቹን የቀን መቁጠሪያዎች ቀረፁ። ኤስ. ኤ. እስተርን “የጥንታውያን ዓለም የዘመን አቆጣጠሮች” (The Calendars of the Ancient World) በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚያስረዱት በጥንታዊት ግብፅ የናይል ወንዝ ሙላት እና የሶቲስ ኮከብ መውጣትን መሠረት ያደረገ የፀሐይ የጊዜ መጠሪያ ወይም ካላንደር ፈጥረዋል፡፡
በሜሶፖታሚያ ደግሞ የጨረቃን ዑደት የተከተለ የዘመን አቆጣጠር ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ተፈጥሮን የማንበብ ጥበብ የሰው ልጅ ግብርናን፣ ንግድን እና ማህበራዊ ህይወቱን በስርዓት ለመምራት ያስቻለው ታላቅ የስልጣኔ መሠረት ነበር። የዘመን አቆጣጠር ማህበረሰቦች ታሪካቸውን፣ በዓላቶቻቸውን እና ወቅታዊ ክስተቶቻቸውን ጠብቀው ለማቆየት የተጠቀሙበት መሠረታዊ መሣሪያ በመሆን አገልግሏል።
በጥንታዊው ዓለም ዋና ዋና የተባሉት የዘመን አቆጣጠሮች የሚከተሉት ናቸው፦
- የግብፅ የዘመን አቆጣጠር፦ በፀሐይ እና በሶቲስ ኮከብ መውጣት ላይ የተመሠረተ ነበር። አንድን ዓመት በ365 ቀናት እና በ12 ወራት (እያንዳንዱ ወር 30 ቀን) ይከፍሉታል። የቀሩትን አምስት ቀናት በዓመቱ መጨረሻ ይጨምሩ ነበር። ይህም ከአሁኑ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ጋር በጣም ይመሳሰላል።
- የባቢሎን/የመሶፖታሚያ የዘመን አቆጣጠር፦ በጨረቃ ዑደት ላይ የተመሠረተ ነበር። አንድ ወር በጨረቃ መታየት የሚጀምር ሲሆን ከፀሐይ ዓመት ጋር ለማስታረቅ በየጥቂት ዓመታት አንድ ተጨማሪ ወር ይጨምሩ ነበር።
- የማያ የዘመን አቆጣጠር ፦ በጥንታዊቷ ማዕከላዊ አሜሪካ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ ሁለት ዋና ዋና ዑደቶች ነበሩት፦ ፆልኪን የተባለው የ260 ቀናት ሃይማኖታዊ አቆጣጠር እና ሃአብ የተባለው የ365 ቀናት የፀሐይ አቆጣጠር።
- የሮማውያን/የጁሊያን የዘመን አቆጣጠር፦ በጁሊየስ ቄሳር አማካኝነት በ45 ዓመተ ዓለም ተሻሽሎ የቀረበ በፀሐይ ላይ የተመሠረተ አቆጣጠር ነው። አንድን ዓመት በ365 ነጥብ 25 ቀናት በመክፈል በየ4 ዓመቱ አንድ ተደራቢ ቀን (የዘመነ ዮሐንስ/የጳጉሜ 6 ጋር ይመሳሰላል) ቀን እንዲኖረው አድርጓል።
- የዕብራውያን/የአይሁድ የዘመን አቆጣጠር፦ በጨረቃ እና በፀሐይ ዑደት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ሃይማኖታዊ በዓላትን እና ወቅቶችን መሠረት በማድረግ የተዋቀረ ነው።
የሰው ልጅ የታሪክ ጉዞ በጽሑፍ ከመመዝገቡ በፊት ያለው ረጅም ጊዜ የዓለም ቅድመ ታሪክ በመባል ይታወቃል። ማክዶጋል ሊቴል “የዓለም ታሪክ፡ የግንኙነት እና የሥርዓት ዘይቤዎች” (World History: Patterns of Interaction) መጽሐፋቸው በዳሰሱት መሠረት ይህ ዘመን በዋናነት መሳሪያዎችን ለመስራት ጥቅም ላይ በዋሉት ቁሳቁሶች እና በቴክኖሎጂ እድገት መሠረት በሦስት ታላላቅ የድንጋይ ዘመናት ይከፈላል። የመጀመሪያው የብሉይ ድንጋይ ዘመን ሲሆን የሰው ልጅ ያልተጠረቡ እና ድንጉዝ የድንጋይ መሳሪያዎችን በመጠቀም በአደን እና ፍራፍሬ በመሰብሰብ ይኖርበት የነበረ ረጅም የታሪክ ምዕራፍ ነው። በዚህ ወቅት የሰው ልጅ እሳት መጠቀምን በመለማመዱ ከቅዝቃዜና ከአራዊት መከላከል ችሏል። ሁለተኛው የማዕከላዊ ድንጋይ ዘመን የሰው ልጅ ይበልጥ የተቀረፁ፣ ስለታም እና አነስተኛ የድንጋይ መሳሪያዎችን የሰራበት፣ የቀስት እና የጦር ፈጠራ የታየበት እንዲሁም የእንስሳት ማርባት የተጀመረበት የሽግግር ወቅት ነው። ሦስተኛው የሐዲስ ድንጋይ ዘመን ደግሞ የግብርና አብዮት የተካሄደበት፣ የሰው ልጅ ዘላንነቱን ትቶ ቋሚ መኖሪያ መንደሮችን የሰራበት፣ እንስሳትን ያላመደበት እና የሸክላ ሥራዎችን የለመደበት ዘመን ነው። ከድንጋይ ዘመናት በኋላ የነሐስ እና የብረት ዘመናት የተተኩ ሲሆን የጽሑፍ ፈጠራ መከሰት ቅድመ ታሪክን አብቅቶ ዘመናዊውን የታሪክ ክፍልፋይ አበሰረ።
የኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዓመታት የታሪክ ጉዞ ደግሞ የሰው ልጅ መገኛ ከመሆን ባሻገር የራሱ የሆነ የጽሑፍ፣ የሕንፃ እና የመንግሥት አስተዳደር ጥበብ ያሳየበት ታላቅ ገድል ነው። የታሪክ ተመራማሪው ዲ. ደብሊው. ፊሊፕሰን “ጥንታዊት ኢትዮጵያ” (Ancient Ethiopia) በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደሚያስረዱት ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጀመሪያው ሺህ ዓመት አጋማሽ የዳዓማት መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ተመስርቶ ነበረ፡፡ የውኃ መስኖን እና የብረት ሥራን ያውቁ ነበር። ከዚህ በመቀጠል በዓለም አቀፍ ደረጃ በኃያልነቱ በወርቅ፣ ብር እና ነሐስ ሳንቲም ህትመቱ፣ በግዕዝ ጽሑፉ እና በትላላቅ የድንጋይ ሐውልቶቹ የሚታወቀው የአክሱም ሥልጣኔ ተስፋፋ። አክሱም በንግድ መስመር የቀይ ባሕርን ቀጠና ይቆጣጠር የነበረ እና ክርስትናን በ4ኛው ክፍለ ዘመን በይፋ የተቀበለ ታላቅ መንግሥት ነበር። በ12ኛው ክፍለ ዘመን የአክሱም ውድቀትን ተክቶ የተነሳው የዛጉዌ ሥልጣኔ ደግሞ ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩትን እና እስካሁንም ዓለምን የሚያስደንዱትን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ውቅር ለዓለም አበረከተ።
በ13ኛው ክፍለ ዘመን ይኩኖ አምላክ የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥትን እንደገና ማገገሙን ማወጁን ተከተሎ የታየው የኢትዮጵያ ታሪክ በታላላቅ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ክስተቶች የተሞላ ነው። ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት “ቤተክርስቲያን እና መንግሥት በኢትዮጵያ” (Church and State in Ethiopia) በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለፁት በ16ኛው ክፍለ ዘመን በኢማም አህመድ እና በክርስቲያኑ መንግሥት መካከል የተካሄደው ረጅም እና አጥፊ ጦርነት የሀገሪቱን ኢኮኖሚና ባህል በእጅጉ ጎድቶታል። በዚሁ ዘመን የተካሄደው የኦሮሞ ሕዝብ ታላቅ የቦታ ሽግግር የሀገሪቱን የማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ካርታ ሙሉ በሙሉ አዲስ መልክ ሰጠው። በመቀጠል በ17ኛው ክፍለ ዘመን በዐፄ ፋሲለደስ የተመሠረተው የጎንደር ዘመን የሕንፃ፣ የስዕል እና የሥነ-ጥበብ መነቃቃትን ያሳየ ቢሆንም በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የነገሥታቱ ሥልጣን ተዳክሞ ሀገሪቱን ወደ ክፍፍልና እርስ በእርስ ጦርነት የከተተው የመሳፍንት ዘመን ተከሰተ።
ታሪክ ጸሐፊው ሃሮልድ ማርከስ “የኢትዮጵያ ታሪክ” (A History of Ethiopia) በሚለው መጽሐፍ እንደሚገልፁት በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የተነሱት ዐፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከመሳፍንት ክፍፍል አውጥተው በማዕከላዊ አስተዳደር ስር ለማስገባት ጥረት ጀምረው በመቅደላ ተሰዉ። በመቀጠል የተነሱት ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ የሀገርን ድንበር ከግብፅ፣ ከሱዳን እና ከጣሊያን ወራሪዎች በቆራጥነት ተከላክለዋል። ዐፄ ምኒልክ ደግሞ የደቡብ፣ የምስራቅ እና የምዕራብ ግዛቶችን በመቀላቀል የዘመናዊቷን ኢትዮጵያ መሠረት ጣሉ። በተጨማሪም በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ጦርነት የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል ድል በማድረግ የኢትዮጵያን ነጻነት አስከብረው ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት እና የኩራት ምልክት ሆኑ።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን የዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የትምህርትና ዘመናዊነት መስፋፋትን ታይቷል፡፡ የፋሺስት ጣሊያን የአምስት ዓመት ወረራን ተቋቁሟል። በመቀጠል በ1966 ዓ.ም የተካሄደው የሕዝብ አብዮት የንጉሡን ሥርዓት ገርስሶ የደርግ ወታደራዊ ሥርዓትን አመጣ። የደርግን ውድቀት ተከትሎ የመጣው የኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ የፌደራሊዝም ሥርዓትን በመዘርጋት የኢትዮጵያን ዘመናዊ የታሪክ አቅጣጫ የቀረፁ ዋና ዋና ምዕራፎች ናቸው።
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የአዲስ ዓመት አከባበር አመጣጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ረጅም ታሪክ ያለው ሲሆን መነሻውም ከጥንታዊቷ ባቢሎን አኪቱ በዓል ጋር ይያያዛል። ባቢሎናውያን የፀደይ ወቅት ሲጠባ የተፈጥሮን መታደስ እና የመኸርን መባረክ በማሰብ አዲስ ዓመትን ለ12 ቀናት ያከብሩ ነበር። በጥንቷ ሮም ደግሞ ጁሊየስ ቄሳር የጁሊያን ካላንደርን ሲቀርፅ ጥር አንድን የዓመቱ መጀመሪያ አድርጎ ወስኗል። በኢትዮጵያ ደግሞ የመስከረም ወር የክረምቱ ከባድ ዝናብና ጭጋግ አልፎ፣ አዴይ አበባ ፈክቶ፣ ምድር በብርሃን የምታጥለቀልቅበት ወቅት በመሆኑ አዲስ ዓመት የሕይወት መታደስ፣ የተስፋ፣ የፍቅር እና የሰላም መበሰሪያ ተደርጎ በጥንታዊው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር መሠረት በመስከረም አንድ ቀን በተለየ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ድምቀት ይከበራል።
ሳምንቱ በታሪክ
የንጉሱ ከሥልጣን መውረድ
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የታሪክ ሂደት ውስጥ እጅግ አጣብቂኝ እና መሠረታዊ የፖለቲካ ምዕራፍ የተከፈተበት ታሪካዊ ቀን ነው። በወቅቱ የተነሳውን ሕዝባዊና የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተከተሎ የመጣው ማዕበል ዐፄ ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን ያወረደ ነበር፡፡ ይህም ለአያሌ ዓመታት የቆየውን እና በሀገሪቱ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ላይ የበላይነት የነበረውን የዘውድ ሥርዓት በይፋ አብቅቶለታል። ንጉሠ ነገሥቱ ከቤተ መንግሥታቸው ተወስደው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሺህ ዓመታት ታሪክ የነበረው የሰሎሞናዊው አገዛዝ ተከታታይነት እንዲቋረጥ ያደረገ አብዮታዊ ክስተት ነበር።
ይህ የንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን መውረድ የሀገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ በመቀየር ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሥልጣን እንዲጨብጥ መንገድ ከፍቷል። ከዚህ ክስተት በኋላ በኢትዮጵያ አዳዲስ የመሬት አዋጆች፣ የማኅበራዊ መዋቅር ለውጦች እና የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም መስፋፋት ተከናውነዋል፡፡ ሀገሪቱም ወደ አዲስ የወታደራዊ አገዛዝ እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ምዕራፍ እንድትሸጋገር ምክንያት ሆኗል። ስለሆነም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የቆየው ሥርዓት አብቅቶ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አዲስ እና ውስብስብ የታሪክ መስመር የያዘችበት ቀን ተደርጎ ይጠቀሳል ሲል በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የተጻፈው “የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ” የተሰኘው መጽሐፍ ያስረዳል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


