የዋጋ ንረት፣ ማኅበራዊ ቀውሱ እና መውጫ መንገዱ

0
393

የዋጋ ንረት ከኪስ አልፎ የቤተሰብን እና የማኅበራዊ ኑሮን መሠረት እየፈተነ ነው። ትናንት የተገዛ ሸቀጥ ዛሬ በዚያው ዋጋ ለማግኘት አይታሰብም። ወርሃዊ ገቢ እና ወጪ የሚመጣጠኑ አይደሉም።
የቤት ኪራይ እና የመሠረታዊ ፍጆታ ወጪዎች ላይ ያለው የተጋነነ ጭማሪ የኑሮ ውድነትን ከምጣኔ ሀብት ችግርነት አልፎ የመኖር እና አለመኖር ጉዳይ አድርጎታል።
በእንጅባራ ከተማ ከ15 ዓመታት በላይ የኖሩት አቶ ዘላለም ታምር የአሁኑን የኑሮ ጫና ሲገልጹ፣ “እንኳን ሰው ጠርቶ ሊያበላ፤ ወልዶ ለማሳደግም የሚያስፈራበት ጊዜ ላይ ደርሰናል” ይላሉ። ይህ አባባል የዋጋ ጭማሪው ከኪስ አቅም እንደወጣ የሚያሳይ ነው።
በእንጅባራ ከተማ የቤት ኪራይ ከዓመታት በፊት ከ200 እስከ 300 ብር የነበረ ሲሆን አሁን በብዙ እጥፍ ጨምሯል። ከዚህ ጋር የውኃ፣ የመብራት እና የሌሎች አገልግሎቶች ወጪ መጨመር የኑሮን ፈተና አባብሶታል።
አቶ ዘላለም እንደሚገልጹት ቀደም ሲል እስከ ሁለት ሺህ የነበረው የበቆሎ ዋጋ በአሁኑ ወቅት ከሰባት ሺህ ብር በላይ ሆኗል። አንድ እንቁላል ደግሞ ከ25 ብር በላይ እየተሸጠ ነው። ሌሎችም በተመሳሳይ በከፍተኛ መጠን ዋጋቸው ንሯል።
በዚህ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በተለይ ቋሚ ደመወዝ እና አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች በእጅጉ ተጎድተዋል። ምክንያቱ ደግሞ ገቢያቸው ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ የዕለት ተዕለት ወጪያቸው ግን በፍጥነት ይጨምራልና ነው።
ሌላዋ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ቃል ኪዳን በሬ ደግሞ የዚህ አብነት ናቸው። አትክልት ገበያ የፍጆታ ምርት ግብይት ሲፈጽሙ አግኝተን ያናገርናቸው ነዋሪዋ የመንግሥት ሠራተኛ እና የሦስት ልጆች እናት ናቸው።
“ተመሳሳይ የወር ገቢ፣ በየዕለቱ የሚጨምር ዋጋ ኑሯችንን ፈትኖታል” የሚሉት ወ/ሮ ቃል ኪዳን ሁለቱ ልጆቻቸው ተማሪዎች ናቸው። በአሁኑ ወቅት ባለው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ግን ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት እንደተቸገሩ ነው ያነሱት። በበዓላት ወቅት ደግሞ የዋጋ ጭማሪው በጣም እንደሚጋነን ነዋሪዋ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ በመጨረሻም በተለይ በበዓል ወቅት እንደ አቅም መኖር እንደሚገባ ገልጸዋል። “እንደ ጎረቤት ሳይሆን እንደ ቤታችን፣ እንደ አቅማችን፣ ነጋችንንም በማሰብ መኖር ይገባል” ብለዋል። ከዚህ ባለፈ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ የእርምት ርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የዋጋ ንረቱ ከየት መጣ?
መሐመድ ዒሳ (ዶ/ር) በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚያስረዱት የኑሮ ውድነት አንድ መንስኤ ያለው አይደለም። የውጭ ምንዛሪ ጫና፣ የብር የመግዛት ዋጋ መዳከም፣ የምርት እና የአቅርቦት ችግር፣ የማጓጓዣ ወጪ መጨመር እና የገበያ ቁጥጥር ክፍተት በተያያዘ መልኩ ለዋጋ ንረቱ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ።
“የኑሮ ውድነት የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የማኅበራዊ ደኅንነት፣ የቤተሰብ አንድነት እና የአዕምሮ ሰላም ቀውስም ጭምር ነው” ብለዋል፡፡
ትናንት የገዙትን ሸቀጥ ዛሬ በዚያው ዋጋ ማግኘት የሕልም ያህል እየራቀ ነው፤ የዋጋ ጭማሪው በዓመታት ሳይሆን በሳምንታት እና በዕለታት የሚከሰት ሆኗል። ይህ በዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የተደቀነው ከባድ የኢኮኖሚ ፈተና ከየት መጣ? መዳረሻውስ ምን ሊሆን ይችላል?
ዶክተር መሐመድ ዒሳ እንደሚያስረዱት የዋጋ ግሽበቱ ርስ በርስ የተሳሰሩ በርካታ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች ያሉት ነው። ምክንያቶቹንም እንደሚከተለው ነው የጠቀሷቸው፤ የውጭ ምንዛሪ ጫና እና የብር ዋጋ መዳከም፦ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ከውጭ በሚገቡ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒት እና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ ናት። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እና የብር ዋጋ መውረድ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች ዋጋ ጣሪያ እንዲነካ አድርጓል፤ ይህም “የገቢ ግሽበት ነው” ብለዋል።
የምርት አቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል፦ በግብርናውም ሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚመረተው ምርት ከሸማቹ ፍላጎት ጋር አለመመጣጠኑ እና የማጓጓዣ ወጪዎች በየጊዜው ማሻቀባቸው የዋጋ ንረቱን አባብሶታል።
የገበያ ቁጥጥር ክፍተት እና ሕገ -ወጥነት፦ መንግሥት ገበያውን ፍትሐዊ በሆነ አግባብ የመቆጣጠር አቅሙ መዳከሙ እና ሸቀጦችን በመጋዝን የመደበቅ አባዜ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ፈጥሯል። መምህሩ እንዳስገነዘቡት በሰለጠነው ዓለም የአምስት ሳንቲም ጭማሪ ለማድረግ ዐሥርት ዓመታት በሚፈጅበት ሁኔታ በሀገራችን በአንድ ቀን ውስጥ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ መመልከት የተለመደ ክስተት ሆኗል።
ዶክተር መሐመድ እንደሚያስረዱት በሀገሪቱ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች የምርት ሂደቱን ክፉኛ ጎድተውታል። ምክንያቱ ደግሞ ኢኮኖሚ እና ሰላም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸውና።
“ሰላም በሌለበት ገበሬው ማሳውን አያርስም፤ ሰብሉንም በሰላም መሰብሰብ አይችልም። ሰላም ሲታወክ ለምሳሌ በአማራ ክልል የተመረተ እህል ወደ ዋናው የፍጆታ ማዕከል አዲስ አበባ መድረስ አይችልም። መንገድ ሲዘጋ የማጓጓዣ ወጪው ጣሪያ ይነካል፤ ይህም በቀጥታ በሸማቹ ጫንቃ ላይ ይጫናል፤” ይላሉ መምህርና ተመራማሪው።
ከዚህም በተጨማሪ ግጭቶች የኢንቨስትመንት ፍሰትን፣ የቱሪዝም ገቢን እና የኤክስፖርት (የውጪ ገበያ) ዕድሎችን በማዳከም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት አቅም ፈትነውታል።
የኑሮ ውድነት ማኅበራዊ ጠባሳዎች – ከኪስ መጉደል እስከ ሰብዓዊነት መሸርሸር
የኑሮ ውድነት ቁጥር ብቻ አይደለም፤ ደም እና ስጋ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ነው። በተለይ ዝቅተኛ እና ቋሚ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ክፉኛ ተጎድተዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ የምግብ ዋጋ በሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ውስጥ 54 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል። “ይህ ማለት አንድ ተራ ዜጋ ከሚያገኘው ገቢ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለሆድ ፍጆታ ብቻ ያውለዋል” ሲሉ ነው ያስገነዘቡት ተመራማሪው ዶክተር መሐመድ ዒሳ።
የምግብ ዋጋ ሲጨምር ቤተሰቦች፤ የምግብ ጥራትን ይቀንሳሉ (አስፈላጊውን የተመጣጠነ ምግብ አያገኙም)፣ ለትምህርት እና ለጤና የሚያወጡትን ወጪ ይቀንሳሉ፣ እንዲሁም ለከፍተኛ ዕዳ እና ለጭንቀት ይጋለጣሉ። ይህ ሁኔታ በቤተሰብ ውስጥ አለመግባባትን እና ግጭትን በማስከተል የትውልዱን ተስፋ በማጨለም ለስደት እና ፍልሰት በር እየከፈተ ይገኛል።
“ከሁሉም በላይ የሚያሳስበው ደግሞ የማኅበራዊ ካፒታል መሸርሸር ነው” ነው የሚሉት ተመራማሪው ኢትዮጵያውያን ተካፍለው በመብላት፣ በመረዳዳት እና በመጠያየቅ የሚታወቁ ቢሆንም የኑሮ ጫናው ሕዝቡን ወደ ግለኝነት እና “እኔ ብቻ ልኑር” ወደሚል አስተሳሰብ እየገፋው መሆኑን ይገልጻሉ።
ከሸማቹ ምን ይጠበቃል? ስንልም ለተመራማሪው ጥያቄ አቅርበንላቸዋል፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዜጎች ራሳቸውን ከከፋ ቀውስ ለመጠበቅ የሚከተሉትን ተግባራዊ የፋይናንስ ስልቶች እንዲከተሉ ዶክተር መሐመድ ይመክራሉ።
ጥብቅ የወር በጀት ማበጀት፦ ወጪዎችን በዝርዝር መመዝገብ “የግድ የሚያስፈልጉ” እና “ቢቀሩ የማይጎዱ” ወጪዎችን በጥብቅ መለየት ይገባል።
የጅምላ እና የቡድን ግዢ፦ በተናጠል ከችርቻሮ ከነጋዴ ከመግዛት ይልቅ ተደራጅቶ ከጅምላ አቅራቢዎች ወይም ከሸማች ማኅበራት በጋራ መግዛት ከፍተኛ ወጪን ያድናል።
ብክነትን ማስወገድ፦ የምግብ እና የኃይል ብክነትን መቀነስ፤ የቤት ውስጥ ፍጆታን በአግባቡ ማስተዳደር ችግሩን ያቃልላል፡፡
ከፍተኛ ወለድ ካላቸው ዕዳዎች መራቅ፦ ላልተገባ ፍጆታ የሚወሰዱ እና የመክፈል አቅምን ያላገናዘቡ ውድ ብድሮችን አለመውሰድም የችግሩ ማቃለያ መንገድ ነው፡፡
ተጨማሪ የገቢ ምንጮችን መፈለግ፦ በትርፍ ጊዜ ሕጋዊ የሆኑ ተጨማሪ የገቢ ማመንጫ መንገዶችን መፍጠር ይገባል።
ዘላቂው መውጫ መንገድ፦ ለመንግሥት የቀረበ የቤት ሥራ
ምንም እንኳ መንግሥት ግሽበቱን ከነበረበት 30 በመቶ በላይ ወደ አነስተኛ ቁጥር ለማውረድ ጥረት ቢያደርግም አሁንም የፖሊሲ ማሻሻያዎች የግድ እንደሆኑ ተመራማሪው ያብራራሉ። ለዚህ ደግሞ የአጭር እና የረዥም ጊዜ መፍትሔዎችን መተግበር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የአጭር ጊዜ መፍትሔ
ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረገውን የታለመ ማኅበራዊ ድጋፍ ማጠናከር፣ ገበያውን ከደላሎች እና ከሕገ-ወጥ አጽድቶ ጥብቅ ተቋማዊ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል።
የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ
የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፦
ዝናብ ጠባቂነትን በመስኖ እርሻ መተካት፣ የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ምርት ማሳደግ ያስፈልጋል።
የወጪ ንግድን (Export) ማሳደግ፦ ሀገሪቱ በቡና እና በቆዳ ላይ ብቻ ተወስና ሳትቀር ሌሎች የኢንዱስትሪ እና የግብርና ውጤቶችን በስፋት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ አቅሟን ማጎልበት ያሻል።
የተረጋጋ የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲ፦ የገንዘብ አቅርቦትን እና የመንግሥት ወጪን ከሀገሪቱ እውነተኛ የምርት ዕድገት ጋር ማመጣጠንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳል።
ዘላቂ ሰላም፦
የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች ፍሬ እንዲያፈሩ በሀገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም መስፈን ቀዳሚው ቅድመ ሁኔታ ነው።
የኑሮ ውድነት ማዕበል የሀገራችንን ኢኮኖሚ እና የሕዝባችንን ማኅበራዊ መስተጋብር እየፈተነ ይገኛል። ይህንን ማዕበል በብልሃት ለማለፍ የሸማቹ ብልህ የፋይናንስ አስተዳደር እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግሥት ቁርጠኛ የፖሊሲ እርምጃ፣ ጥብቅ የገበያ ቁጥጥር እና ለዘላቂ ሰላም የሚደረግ ትጋት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ።

(መልካሙ ከፋለ እና ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የመስከረም  4  ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here