በዕጅ ያለ እሳት

0
246

የዘመኑ ሰው ከእንቅልፉ ሲነቃ ከሚፈልጋቸው የመጀመሪያ ነገሮች አንዱ የሞባይል ስልኩን ነው፡፡  ከዓለም ጋር የሚገናኝበት መንገድም ተቀይሯል፡፡ ዜናን ለማወቅ፣ ሐሳብን ለመጋራት፣ ከሩቅ ያሉ ወዳጆች ጋር ለመገናኘት እና ዕውቀትን ለማስፋት ማሕበራዊ ሚዲያን የዕለት ተዕለት ኑሮው አካል አድርጓል፡፡

ማሕበራዊ ሚዲያዎች በርካታ ጥቅሞች ቢኖሯቸውም አጠቃቀማችን ከተገቢው መጠን ሲያልፍ በሰው ልጅ የአዕምሮ፣ የስነ-ልቦና እና የአካል ጤና ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳድራሉ፡፡

የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በጤና ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በተመለከተ ታዋቂ የሕክምና ተቋማት፣ ተመራማሪዎች እና ሳይንቲስቶች ያቀረቧቸው ዋና ዋና ግኝቶች እና መግለጫዎች የሚከተሉት ናቸው፦

ታዋቂው የሕክምና ባለሙያ እና የአሜሪካ ዋና የሕዝብ ጤና ጠባቂ መኮንን ዶ/ር ቪቭክ ሙርቲ አ.አ.አ በ2023 ባወጡት ይፋዊ ማሳሰቢያ ማሕበራዊ ሚዲያ ለሕጻናት እና ለታዳጊዎች አዕምሮአዊ ጤና “ከፍተኛ ጉዳት አለው” ብለዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ በቀን ከሦስት ሰዓት በላይ በማሕበራዊ ሚዲያ የሚያሳልፉ ታዳጊዎች ለድብርት እና ለጭንቀት የመጋለጥ ዕድላቸው በእጥፍ ይጨምራል፤ በመሆኑም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የደኅንነት መስፈርቶችን ማጠናከር እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ጤና ትምህርት ቤት በበኩሉ  የማሕበራዊ ሚዲያ  አዕምሮ ውስጥ ለሱስ የሚዳርጉ ኬሚካሎችን እንዲመረቱ በማድረግ ከቁማር ሱሰኝነት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ባሕርይ እንደሚያመጣ በጥናት አረጋግጧል፡፡ “ላይክ” (Like) እና ማሳወቂያዎች (Notifications) አዕምሮ ውስጥ ከፍኛ ዶፓሚን የሚባል አነቃቂ ኬሚካል እንዲለቀቅ በማድረግ  ሰዎች ስልካቸውን ደጋግመው እንዲፈትሹ እንደሚያስገድዳቸው በጥናት ተመላክቷል፡፡

እንደ የአሜሪካ የስነ-ልቦና ማሕበር ግኝት ደግሞ ማሕበራዊ ሚዲያ በራሱ ሙሉ በሙሉ ጎጂ ወይም ጠቃሚ ሊያደርገው የሚችለው አጠቃቀሙ እና የሰዎች የዕድሜ ደረጃ እንደሆነ አብራርቷል፡፡ በተለይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች በማሕበራዊ ሚዲያ ሳቢያ በሚመጣ የአካል ብቃት እና ውበት ንፅፅር ምክንያት የራስ ዕሴትን ማጣት እና የመብላት ፍላጎት መዛባት እንደሚያጋጥማቸው የማሕበሩ የጥናት መረጃ ያመላክታል፡፡

የስነ-ልቦና ተመራማሪ እና ደራሲ የሆኑት ዶ/ር ጄን ትዌንግ አይ ጄን” በተሰኘው ታዋቂ መጽሐፋቸው እና ባደረጉት ሰፊ ጥናት የዘመናዊ ስልኮች እና የማሕበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ከተጀመረበት እ.አ.አ ከ2004 ወዲህ በታዳጊዎች ዘንድ የብቸኝነት እና የድብርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አመላክተዋል፡፡ በስክሪን ፊት የሚያሳልፉት ጊዜ ከእውነተኛው የማሕበራዊ ግንኙነት እና የእንቅልፍ ሰዓት ላይ ስለሚቀንስ ለስነ-ልቦና ቀውስ እንደሚዳርግ አብራርተዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በበኩሉ የማሕበራዊ ሚዲያ እና የስክሪን አጠቃቀም ከእንቅልፍ ማጣት እና ከአካላዊ እንቅስቃሴ አልባነት ጋር ያለውን ቁርኝት በተመለከተ ጥናት አድርጓል፡፡ በጥናቱ እንደተረጋገጠው በምሽት ጊዜ የሚንጸባረቀው ሰማያዊ ብርሃን (Blue Light) የእንቅልፍ ሆርሞን (Melatonin) ምርትን በመግታት እንቅልፍ አልባነትን ያስከትላል፤ ይህም እንደ ስኳር እና የልብ ሕመም ላሉ በሽታዎች ተጋላጭ ያደርጋል፡፡

መፍትሔዎች

የአሜሪካ የስነ-ልቦና ማሕበር እና የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቁት የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወን ያልተገባ የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የሚያስከትለውን የጤና ጠንቅ ለመቀነስ ያስችላሉ፡፡

የጊዜ ገደብን መወሰን፡- በቀን በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ብቻ ማድረግ፡፡ ለዚህም በስልክዎ ውስጥ የሚገኙትን የጊዜ መቆጣጠሪያ መተግበሪያዎችን (ScreenTime) መጠቀም ይቻላል፡፡

ስክሪን አልባ ቀጣናዎችን መፍጠር (Tech-Free Zones):- በመመገቢያ ጠረጴዛ ላይ እና በመኝታ ክፍል ውስጥ ስልክ አለመጠቀም፤ በተለይም ከእንቅልፍ በፊት ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ስክሪን አለመመልከት የእንቅልፍ ሆርሞን (Melatonin) ምርት እንዳይስተጓጎል ይረዳል፡፡

የዲጂታል እረፍት ማድረግ (Digital Detox):- በሳምንት አንድ ቀን (ለምሳሌ እሁድ) ወይም በወር ጥቂት ቀናትን ከማሕበራዊ ሚዲያ ሙሉ በሙሉ በመራቅ ጊዜን ለአካላዊ እረፍት እና ለቤተሰብ መስጠት፡፡

ማሳወቂያዎችን (Notifications) ማጥፋት:- የስልክ ማሳወቂያዎች ሲመጡ የሚፈጠረውን የማየት ጉጉት ለመቀነስ ከአስፈላጊ የመልዕክት መተግበሪያዎች ውጭ ያሉትን ማሳወቂያዎች ማጥፋት የስክሪን ላይ ቆይታችንን ይገታልናል፡፡

የአዕምሮ እና የስነ-ልቦና ጥበቃ ስልቶች የሚከታተሏቸውን መለያዎች ማጣራት:- ጭንቀት፣ የባዶነት ስሜት ወይም የራስን ዕሴት ዝቅ አድርገው እንዲመለከቱ የሚያደርጉ ገጾችን ከመከተል መቆጠብ (Unfollow)፤ ይልቁንም የሚያስተምሩ እና የሚያበረታቱ ይዘቶችን መምረጥ፡፡

ያለ ዓላማ ስልከ የመነካካት ልማድን ማስወገድ: – ስክሪን ወደ ላይ እና ወደ ታች ከመጎተት ይልቅ፣ ማሕበራዊ ሚዲያን ለተወሰነ ዓላማ ብቻ (ለምሳሌ ከወዳጅ ጋር ለመወያየት ወይም መረጃ ለመፈለግ) መጠቀም፡፡

እውነታውን መገንዘብ:- ሰዎች በማሕበራዊ ሚዲያ የሚያጋሩት የሕይወታቸውን ምርጥ እና የተመረጠ ክፍል እንጂ ሙሉ እውነታውን እንዳልሆነ ዘወትር ማስታወስ እና የራስን ሕይወት ከሌሎች ጋር አለማወዳደር እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ እና የእውነተኛ ሕይወት ግንኙነቶችን ማጠናከር ይገባል፡፡

የፊት ለፊት ግንኙነትን ማደስ:- ከጓደኞች እና ከቤተሰብ ጋር በቀጥታ በመገናኘት፣ አብሮ በመጫወት እና በመወያየት የሚገኘውን ማሕበራዊ ትስስር ማጠናከር፡፡

አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ:- በቀን ከ20 እስከ 30 ደቂቃ የሚደረግ ስፖርት፣ የእግር ጉዞ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማሕበራዊ ሚዲያ ምክንያት የሚመጣን የአንገት እና የጀርባ ሕመም መቀነስ ብቻ ሳይሆን የደስታ ሆርሞኖችን በመጨመር ጭንቀትን ያጠፋል፡፡

አዳዲስ ልምዶችን ማዳበር:- በስክሪን ፊት የሚጠፋውን ጊዜ መጽሐፍ በማንበብ፣ አዳዲስ ክህሎቶችን በመማር ወይም በመዝናኛ እንቅስቃሴዎች በመተካት አዕምሮን በበጎ ነገር መሙላት ተገቢ ነው፡፡

መረጃ

*ማሕበራዊ ሚዲያን አላግባብ በመጠቀም ምክንያት የሚከሰቱ የጤና እና የሥነ-ልቦና እክሎችን የሚያሳዩ ጥናታዊ መረጃዎች፦

በቀን ከ3 ሰዓት በላይ በማሕበራዊ ሚዲያ የሚያሳልፉ ታዳጊዎች ለዕእምሮ ጤና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው 50 በመቶ እንደሚጨምር ተረጋግጧል፡፡

*በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ ጊዜ የሚያሳልፉ ወጣቶች የማሕበራዊ ሚዲያ ከማይጠቀሙ  ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ የብቸኝነትና የመገለል ስሜትን  የማየት እድላቸው ሁለት  እጥፍ ይበልጣል፡፡

*32 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ሴቶች በማሕበራዊ ሚዲያ (በተለይ ኢንስታግራም) ምክንያት ስለ ሰውነታቸው ቅርፅና መልክ ያላቸው አመለካከት እንደሚበላሽና የበታችነት ስሜት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡

*ከመተኛታቸው ከ1 ሰዓት በፊት ማሕበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ሰዎች በቂ እንቅልፍ የማጣት እድላቸው በ1 ነጥብ 5 እጥፍ ይጨምራል፡፡ ይህ የሚሆነው ከስክሪን የሚወጣው ሰማያዊ ብርሃን ሜላቶኒን (Melatonin) የተባለውን የእንቅልፍ ሆርሞን ምርት ስለሚቀንስ ነው፡፡ (ምንጭ፦ Sleep Health Journal/National Sleep Foundation) ከ5 እስከ 10በመቶ የሚሆኑ የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ክሊኒካዊ መስፈርትን የሚያሟላ የቁጥጥር ማጣት እና የማሕበራዊ ሚዲያ ሱስ ባሕሪ ይታይባቸዋል፡፡

* ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ የዲጂታል ስክሪን አዘውታሪዎች ለዓይን ድካም፣ ለዓይን መድረቅ እና ለአንገትና የጀርባ ሕመም ይጋለጣሉ፡፡

(ምንጭ፦ U.S. Surgeon General Advisory፣ American Journal of Preventive Medicine

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here