መግቢያ
የጉዞ ጥማት እና የቱሪዝም ምንነት
የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ አዳዲስ አካባቢዎችን የማየት፣ የመዳሰስ፣ የመረዳት… ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለው። ይህ ጥንታዊ የጉዞ ልማድ ዛሬ ላይ ተቋማዊ ቅርፅ ይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሆኗል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UN Tourism) ቱሪዝምን ሲተረጉመው፤ “አንድ ግለሰብ ከተለመደው የመኖሪያ እና የሥራ አካባቢው ውጭ በመውጣት ለረፍት፣ ለንግድ፣ ለመዝናናት… ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ተከታታይ ጊዜ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና በዚያ ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ድምር ውጤት ነው” ይለዋል።
ቱሪዝም መዳረሻዎችን ብቻ ሳይሆን ሰዎችን፣ ባሕሎችን እና አስተሳሰቦችን የሚያስተሳስር የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ድልድይ እንደሆነም ይጠቅሳል።
የቱሪዝም ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ
ቱሪዝም በኢኮኖሚክስ ሊቃውንት ዘንድ “ጪስ አልባው ኢንዱስትሪ” በመባል ይጠራል። ቱሪዝም ፋብሪካ ሳይተከል እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትን ሳያሟጥጡ የውጭ ምንዛሪን እና ሀብትን ማፍራት የሚያስችል አስደናቂ ዘርፍ መሆኑንም መረጃው አስገንዝቧል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ግኝት እና የሀገር ውስጥ ገቢ (GDP) ዕድገት
የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ምክር ቤት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቱሪዝም ከኮቪድ -19 ወረርሽኝ መከሰት በፊት ከዓለም አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት 10 ነጥብ አራት በመቶውን ይሸፍናል፡፡ በየዓመቱም ከዘጠኝ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝ መረጃው ጠቁሟል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚፈጠሩ 10 የሥራ ዕድሎች መካከል አንዱ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኝ ነው። ዘርፉ ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና አነስተኛ የትምህርት ዝግጅት ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ለሆቴሎች፣ ለአስጎብኚዎች፣ ለአጓጓዦች፣ ለእደ ጥበብ ባለሙያዎች እና ለስጦታ እቃ ሻጮች እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የገቢ ምንጭ ነው።
የተዛማጅ ዘርፎች መነቃቃት
አንድ ቱሪስት ወደ ሀገር ሲገባ የሚከፍለው ገንዘብ ለአየር መንገድ እና ሆቴል ብቻ ገቢ ሆኖ አይቀርም። አርሶ አደሩን፣ ታክሲ አሽከርካሪውን፣ ጫማ አስዋቢውን፣ የባሕል አልባሳት አምራቹን፣ ኪነ-ጥበበኛውን… በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል።
ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርስን መጠበቅ
በቱሪዝም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች እንዲሁም የዱር እንስሳት ዋነኛ የገቢ ምንጮች ናቸው፡፡ በዚህም ማሕበረሰቡ ሀብቶቹን እንዲንከባከብ እና እንዳይወድሙ ጥበቃ እንዲያደርግ ተቋሙ የኢኮኖሚ ማበረታቻ ይሰጣል።
ሌሎች ሀገራት በቱሪዝም እንዴት ተጠቀሙ?
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ስንመለከት የተፈጥሮ ሀብት መኖር ብቻውን ዋስትና እንዳልሆነ እና ትክክለኛ ፖሊሲ፣ ሰላም እና መሰረተ-ልማት ወሳኝ መሆናቸውን የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ምክር ቤት መረጃ ያሳያል።
ፈረንሳይ እና ስፔን ምንም እንኳን አዳዲስ የተፈጥሮ ድንቆች ባይኖሯቸውም ጥንታዊ ቅርሶቻቸውን በጥሩ ሁኔታ በመጠበቅ፣ ቀልጣፋ የመጓጓዣ (ትራንስፖርት) መሠረተ ልማት በመዘርጋት እና አይረሴ መስተንግዶ በማድረግ በዓመት ከ80 እስከ 90 ሚሊዮን ቱሪስቶችን በመሳብ ከዓለም ቀዳሚዎች ናቸው።
ኬንያ በበኩሏ የዱር እንስሳት ጥበቃን ከማሕበረሰብ ልማት ጋር በማስተሳሰር በአፍሪካ በሳፋሪ ቱሪዝም (የዱር እንስሳትን በተፈጥሮ መኖሪያቸው ለመጎብኘት እና ፎቶግራፍ ላማንሳት የሚደረግ ጉዞ) መሪ ሆናለች። የማሳይ ማራ ስነ-ምሕዳርን ያለምንም መረበሽ በመጠበቅ በዓመት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ ታገኛለች።
ኮስታሪካም “ፑራ ቪዳ” በሚል መሪ ቃል መላ ሀገሪቱን የኢኮ-ቱሪዝም ማዕከል አድርጋለች። የደን ጭፍጨፋን በማስቆም የተፈጥሮ ሀብቷን ሸጣ ዜጎቿን ከድህነት ያወጣችበት ተሞክሮ ለታዳጊ ሀገራት ትልቅ ትምህርት ነው።
ሌላዋ የዘርፉ ተጠቃሚ ግብፅ ጥንታዊውን የፈርዖኖች ታሪክ ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ግዙፉን የግብፅ ሙዚየም በመገንባት የቱሪዝም ፍሰቷን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጋለች።
የኢትዮጵያ እምቅ አቅም – የሰው ዘር መገኛ
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች አሏት፡፡ በዚህም ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናት። ከሉሲ ቅሪተ-አካል እስከ አክሱም ሀውልቶች፣ ከፋሲል ግቢ እስከ ላልይበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት፣ ከስሜን ተራሮች እስከ ባሌ ብሔራዊ ፓርክ ድረስ ሀገሪቱ ከፍተኛ የባሕል እና የተፈጥሮ ሙዚየም ናት።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ካለው እምቅ አቅም አንፃር ያለበት ደረጃ እጅግ ዝቅተኛ ነው። እንደ ኬንያ፣ ሞሮኮ እና ታንዛኒያ ያሉ ጎረቤት ሀገራት የሚያገኙትን ገቢ ያህል ለማግኘት ብዙ ሥራዎች ይጠበቅባታል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግሥት በኩል የተጀመሩት እንደ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች (ለምሳሌ፦ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ አንድነት ፓርክ) የቱሪዝም መሰረተ-ልማትን በማዘመን አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን ለመፍጠር ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ናቸው። ሆኖም በዘርፉ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ በመሠረተ-ልማት እጥረት እና በሚገባው ልክ ማስተዋወቅ አለመቻል የሚታዩ ድክመቶች ናቸው።
የአማራ ክልል አንጡራ ሀብቶች
የዓለም ድንቅ ቅርሶች፦ ክልሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሀብት መገኛ ነው፡፡ በክልሉ የሚገኙት የላልይበላ ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተፈለፈሉ አቢያተ-ክርስቲያናት እና የጎንደር የፋሲል ግቢ ቤተ-መንግሥታት የሰው ልጅ ጥበብ ከፍተኛ ማሳያዎች ናቸው።
የተፈጥሮ ገነት (ሥነ-ሕይወት)፦ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የራስ ደጀን ተራራ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት (ዋልያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የቀይ ቀበሮ) መገኛ ነው።
ጣና ኃይቅ እና ቅርሶቿ፦ የጣና ሐይቅ እና በውስጡ የሚገኙት ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተገነቡ ጥንታዊ ገዳማት፣ የጥንት ብራናዎች እና የነገሥታት አጽም የበርካቶች ዐይን ማረፊያዎች ናቸው። የዓባይ ፏፏቴም ሌላኛው የተፈጥሮ ድንቅ ነው።
የማይዳሰሱ ቅርሶች፦
እንደ ጥምቀት፣ መስቀል፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ቡሄ እና ሶለል ያሉ ደማቅ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የዓለምን ትኩረት የሚስቡ ናቸው።
ተግዳሮቶች
ምንም እንኳን ክልሉ ወደር የሌለው የቱሪዝም ሀብት ቢኖረውም ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙት የሰላም እጦት ዘርፉን ጎድቶታል። በዚህም የቱሪስቶች ፍሰት ቀንሷል፣ የሆቴሎች እና የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በገበያ ማጣት ሠራተኞች ተበትነዋል… በዚህም ክልሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ አሳጥቶታል።
የነገው ተስፋ
የጎርጎራ ፕሮጀክት መጠናቀቅ፣ የማሕበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም በስሜን ተራሮች አካባቢ መጀመሩ…የነገ ተስፋዎች ናቸው። በእነዚህ እና በቆዩት ሀብቶች በቀጣይም ዘርፉን በከፍተኛ ፍጥነት ያሳድጉታል።
የመፍትሔ አቅጣጫዎች
ቱሪዝም የቅንጦት ዘርፍ ሳይሆን የህልውና እና የብልጽግና መሰረት ነው። ኢትዮጵያም ሆነች የአማራ ክልል ከዚህ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ ሰላም ለቱሪዝም የመጀመሪያውና ዋናው መሰረተ-ልማት በመሆኑ ሁሉም ለሰላሙ ተሳታፊ መሆን፣ ክልሉ ሀብቱን ዓለም የደረሰበትን የዲጂታል ሚዲያ በመጠቀም ሀገሪቱንና ክልሉን በአዎንታዊ መልኩ ለዓለም ማስተዋወቅ፣ ወደ መስህብ ስፍራዎች የሚወስዱ መንገዶችን፣ ንፁህ የውኃ እና የመብራት አቅርቦትን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ማረፊያዎችን ማስፋፋት፣ በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ከቱሪዝሙ ገቢ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ካልሆነ ቅርሶቹን የመጠበቅ ተነሳሽነቱ ስለሚቀንስ የዘርፉ ዋነኛ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
ጭስ አልባ የሚል ስያሜ የተሰጠው ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም የቱሪዝም ቀን በየዓመቱ በፈረንጆች አቆጣጠር መስከረም 27 ቀን በኢትዮጵያ አቆጣጠር ደግሞ መስከረም 17 ቀን ይከበራል። ቀኑ በይፋ መከበር የጀመረው እ.አ.አ በ1980 በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UN Tourism) አማካኝነት ሲሆን ቀኑ የተመረጠበት ዋና ምክንያት እ.አ.አ በ1970 የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ የፀደቀበት ዕለት በመሆኑ ነው።
መረጃ
የቱሪዝም ዓይነቶች በጨረፍታ
ባህላዊ እና ታሪካዊ ቱሪዝም፦ ጥንታዊ ቅርሶችን፣ ታሪካዊ ከተሞችን፣ ሙዚየሞችን እና የሕዝቡን አኗኗር መጎብኘት።
ኢኮ-ቱሪዝም፦ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳርን፣ የተከለሉ ፓርኮችን እና የዱር እንስሳትን በተፈጥሯዊ አካባቢያቸው መጎብኘት።
ሃይማኖታዊ (መንፈሳዊ ቱሪዝም)፦ ወደ መንፈሳዊ ቦታዎች የሚደረግ ጉዞ ነው።
የስብሰባ እና ኮንፈረንስ ቱሪዝም፦ ለንግድ፣ ለዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እና አውደ-ርዕዮች የሚደረግ ጉዞ።
የጀብዱ ቱሪዝም ፦ ተራራ መውጣት፣ በበረሃ ጉዞ ማድረግ እና ፈታኝ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን።
የስፖርት ቱሪዝም፦ ትልልቅ የስፖርት ውድድሮችን ለመመልከት የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡
የትምህርት ቱሪዝም፦
አዳዲስ ነገሮችን ለመማር፣ ቋንቋ ለማጥናት ወይም ጥናት እና ምርምር ለማድረግ ወደ ሌላ ሀገር/አካባቢ የሚደረግ ጉዞ ነው።
የግብርና ቱሪዝም፦ ከከተማ ጫጫታ ርቆ የገጠር አኗኗርን፣ እርሻን፣ የእንስሳት እርባታን እና የግብርና ሥራዎችን በቅርበት ለማየት እና ለመለማመድ የሚደረግ ጉብኝት ነው።
እነዚህ እና መሰል የቱሪዝም አይነቶች ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት፣ የሥራ እድል በመፍጠር እና የሀገርን ገፅታ በመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው። ፡፡
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


