የዘንድሮዉ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጥጫ

0
28

ይህ የአውሮፓ ግዙፉ የእግር ኳስ መድረክ ነው፡፡ በውስጥ ሊጎቻቸው ምርጥ ጊዜን ያሳለፉ የኃያላን ክለቦች የፍልሚያ አውድማም ጭምር ነው፡፡ በመድረኩ መሳተፍ እና ማሸነፍ ደግሞ የበርካታ ተጫዋቾች እና ክለቦች ትልቁ ህልም እንደሆነ ይነገራል፡፡ የ2026/27 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በሰላሳ ስድስት ክለቦች መካከል የሚደረገውን የሊግ ምዕራፍ በይፋ ጀምሯል፡፡ጨዋታዎቹ አሁን በከፍተኛ ሙቀት እየተካሄዱ ይገኛሉ፤ ይህ የውድድር ዘመን የተጀመረው በሰሜን አሜሪካ ምድር የተካሄደው አድካሚው የ2026 የዓለም ዋንጫ በተጠናቀቀ ማግስት ነው፡፡ ተጫዋቾች ከዓለም ዋንጫው ድካም ሳያገግሙ ወደ አውሮፓ መድረክ ገብተዋል፡፡

አንጋፋው አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ “የዘንድሮው አዲስ የውድድር መዋቅር የተጫዋቾችን አቅም እስከ መጨረሻው የሚፈትን ጨካኝ አሰራር ነው” በማለት ገልጸውታል፡፡ የክለቦች እግር ኳስ ታላቁን ክብር ለመጎናጸፍ የሚደረገው ይህ እልህ አስጨራሽ ጉዞ በመጪው ግንቦት በማድሪድ ከተማ በሚካሄደው ፍልሚያ ፍጻሜውን ያገኛል፡፡

አዲሱ የሊግ ቀመር ዘንድሮ ሦስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የተለመደው የምድብ ድልድል ሙሉ በሙሉ ቀርቷል፡፡ እያንዳንዱ ቡድን ስምንት የተለያዩ ጨዋታዎችን ያደርጋል፡፡ አራቱ በሜዳው ሲከናወኑ አራቱ ከሜዳ ውጪ ይደረጋሉ፡፡ የግብ ልዩነት የክለቦችን እጣ ፈንታ በቀጥታ ይወስናል፡፡

ነጥቦች እኩል የመሆን ዕድላቸው እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ክለቦች ተጫዋቾችን የማሳረፍ ምንም ዓይነት ዕድል አላገኙም፡፡ ከሃያ አምስተኛ እስከ ሰላሳ ስድስተኛ ያጠናቀቁት ክለቦች ወደ ዩሮፓ ሊግ ሳይወርዱ ሙሉ በሙሉ ይሰናበታሉ፡፡

የፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ፓሪስ ሴንት ዠርመን ለተከታታይ ሦስተኛ ዓመት ዋንጫውን የማንሳት  ታላቅ  ግብ  ይዞ  ውድድሩን ጀምሯል፡፡ አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ስብስባቸውን ለታላቅ ድል አብቅተዋል፡፡ የፓሪሱ ክለብ በውርርድ ድርጅቶች ዘንድ ቀዳሚ ተገማች መሆኑን ቢቢሲ ስፖርት አመልክቷል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ያለው ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል፡፡ ተጫዋቹ ሚስተር ሻምፒዮንስ ሊግ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል፡፡ በግራ መስመር በሁለቱም እግሩ አደጋ የመፍጠር ብቃቱ ለባሎን ዶር ክብር በዋነኝነት ከታጩት ተጫዋቾች አንዱም አድርጎታል፡፡ ነገር ግን የእግር ኳስ ተንታኙ ጁሊየን ሎረንስ “በቡድንህ ውስጥ እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያለ ተጫዋች ከሌለህ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ዋንጫ ማንሳት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው” በማለት ለሪፓሪሱ ክለብ የተሰጠውን ግምት አጣጥሎታል፡፡ፒኤስጂ የውድድር ዘመኑን ባልተረጋጋ ሁኔታ መጀመሩን ያስረዳው የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ጊለም ባላጌ ነው፡፡ አዲሱ የሊግ ምዕራፍ ለሁለተኛው አጋማሽ ቡድንን ለማዘጋጀት እና አዳዲስ ሙከራዎችን ለማድረግ የሚረዳ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እስከ ጥር ወር ድረስ ያልተጠበቁ ውጤቶች ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብሏል፡፡ ኦፕታ ለፒኤስጂ የሰጠው ግምት አራተኛ ደረጃን ይዞ ይጨርሳል የሚል ነው፡፡

ፓሪሳውያኑ በጥርጣሬ የታጀበ ጅማሮ ባደረጉበት በዚህ ወቅት ዙፋኑን ለመንጠቅ ሁለት ክለቦች በከፍተኛ የታክቲክ ብስለት ብቅ ብለዋል፡፡ የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ፒኤስጂን ከዙፋኑ ለማውረድ ከፍተኛ ዕድል እንዳለው ጎል ዶት ኮም አስነብቧል፡፡ ባርሴሎና በክረምቱ የዝውውር ወቅት ስብስቡን በከፍተኛ ደረጃ አጠናክሯል፡፡ ክለቡ ሮድሪን ከማንቸስተር ሲቲ በማስፈረም የመሀል ሜዳውን አስተማማኝ አድርጎታል፡፡ሮድሪ የተጋጣሚን የማጥቃት መስመር አስቀድሞ በማቋረጥ እና የጨዋታውን ፍጥነት በመቆጣጠር ለሃንሲ ፍሊክ ስልት ትልቅ እፎይታ ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም አንቶኒ ጎርደን እና ካሪም አዴዬሚ ቡድኑን ተቀላቅለዋል፡፡ ወጣቱ ኮከብ ላሚን ያማል በከፍተኛ ወኔ ታጅቦ አስደናቂ እንቅስቃሴ እያሳየ ይገኛል፡፡ አሰልጣኝ ፍሊክ “ቡድናችን ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር እና በስሜት የተሞላ አጨዋወትን ይዞ ወደ አውሮፓ የበላይነት እያመራ ነው” በማለት እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባርሴሎና አሁንም ተጨማሪ ሁነኛ የመሀል ተከላካይ እና  ዘጠኝ ቁጥር አጥቂ ይፈልጋል፡፡ ባርሴሎና በውርርድ ተቋማት ሁለተኛው ለዋንጫ የታጨ ክለብ ሆኗል፡፡ ጊለም ባላጌ ባርሴሎና ቢያንስ እስከ ግማሽ ፍጻሜው ድረስ የመጓዝ ሰፊ ዕድል እንዳለው መስክረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በፍጻሜው ጨዋታ በፒኤስጂ በመለያ ምት የተሸነፈው አርሴናል ዘንድሮ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅቷል፡፡ መድፈኞቹ በኦፕታ የኮምፒውተር ትንበያ መሰረት የዘንድሮውን ዋንጫ የማሸነፍ ሃያ ነጥብ አራት በመቶ ሰፊ ዕድል አግኝተዋል፡፡ በዚህም ስሌት መሰረት የሰሜን ለንደኑ ክለብ የመድረኩ ቁጥር አንድ ተገማች መሆናቸውን ኦፕታ ይፋ አድርጓል፡፡

አርሴናል በአውሮፓ እጅግ ጥብቅ እና አነስተኛ የግብ ዕድል የሚቆጠርበት የኋላ ክፍል ገንብቷል፡፡ምንም እንኳ ዊሊያም ሳሊባ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ቢርቅም አዲሱ ፈራሚ ኢዝሪ ኮንሳ እና ጋብሬል ማጋልሄስ ከዲክላን ራይስ ጋር ተጣምረው ቡድኑ ያለምንም  ስጋት  እንዲጫወት    አስችለውታል፡፡ የተከላካይ ክፍሉ ተጋጣሚዎች የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ  በማድረጉ ረገድ ወደር የለውም፡፡ ጁሊየን ሎረንስ “አርሴናል በአውሮፓ እጅግ ምርጡ የኋላ ክፍል አለው፤ ዋንጫ የሚያስገኙትም እንደዚህ ዓይነት ጥንካሬዎች ናቸው” በማለት መስክረዋል፡፡አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ ከጉዳቱ አገግሞ መሪነቱን በመረከቡ ቡድኑ በነጻነት እና በተረጋጋ መንፈስ መጫወት ጀምሯል፡፡ አርሴናል ከቋት አንድ ሪያል ማድሪድ እና ባየር ሙኒክ ቢደርሱበትም ዝቅተኛ ደረጃ ካላቸው ሳባህ እና ስሎቫን ብራቲስላቫ ጋር በመደልደሉ በአንጻራዊነት ምቹ መርሃ-ግብር ማግኘቱን ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡

አስራ አምስት ጊዜ ዋንጫውን ያነሳው ሪያል ማድሪድ አንጋፋውን አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆን ከረጅም ዓመታት በኋላ በድጋሚ ቀጥሯል፡፡ ሞሪንሆ ውድድሩን ሁለት ጊዜ ያሸነፉ ቢሆንም የመጨረሻው ድላቸው ከአስራ ስድስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ጁድ ቤሊንግሃም በሞሪንሆ ስር በአስር ቁጥር  ሚናው ላይ በከፍተኛ ደረጃ ደምቆ እየታየ ነው፡፡ ቤሊንግሃም ከጥሩ የዓለም ዋንጫ ቆይታ በኋላ በርካታ ግቦችን እንደሚያስቆጥር ተጠብቋል፡፡

ነገር ግን ጁሊየን ሎረንስ “በሆዜ ሞሪንሆ እና ሪያል ማድሪድ ፕሮጀክት ላይ ሙሉ እምነት የለኝም” በማለት ጥርጣሬያቸውን አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም የቪኒሲየስ ጁኒየር ብቃት የሁለት ተቃራኒ ገጽታዎች ድምር ሆኖ ቀርቧል፡፡ በአንድ በኩል ቪኒሲየስ በሁለት የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜዎች ላይ ወሳኝ ግቦችን ያስቆጠረ እና በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወደር የማይገኝለት አደገኛ አጥቂ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ተጫዋቹ ጥብቅ መከላከል ሲገጥመው ኳሶችን ያለ አግባብ የማባከን እና ስሜቱን መቆጣጠር ያለመቻል ክፍተቶች ይታዩበታል፡፡ ተከላካዮችን ለማገዝ ወደ ኋላ ባለመመለሱም የማድሪድን የተከላካይ ክፍል ለከፍተኛ አደጋ ያጋልጣል፡፡

ብዙዎች ለቪኒሲየስ የሚሰጡት የላቀ ግምት ከእውነተኛው የሜዳ ላይ አስተዋጽኦ ጋር እንደማይገናኝ የስፖርት ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ማድሪድ በመሀል ሜዳው ላይ የነበሩትን መሪዎች ማጣቱ ክፍተት ፈጥሮበታል፡፡

የእንግሊዙ ኃያል ማንቸስተር ሲቲ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ክለቡን ለቀው መውጣታቸው እና ወሳኙ አማካይ ሮድሪ ወደ ባርሴሎና ማምራቱ ቡድኑን ክፉኛ ጎድቶታል፡፡ ሲቲ በአዳዲስ ፈራሚዎች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ቢያወጣም በውርርድ ተቋማት በሻምፒዮንስ ሊጉ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ እንደሚያጠናቅቅ ዘ ቴሌግራፍ አስነብቧል፡፡

ሲቲ ከባርሴሎና እና ከፒኤስጂ በተጨማሪ ከቋት ሦስት ናፖሊ ጋር በመደልደሉ እጅግ ከባድ ፈተና ገጥሞታል፡፡በአንጻሩ በቪንሰንት ኮምፓኒ የሚመራው ባየር ሙኒክ በኦፕታ ትንበያ ሃያ በመቶ ዕድል በማግኘት ከአርሴናል ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ አጥቂው ሃሪ ኬን የባሎን ዶር ክብሩን ለማሸነፍ በከፍተኛ የግብ ጥማት ውስጥ ይገኛል፡፡ ጊለም ባላጌ “ሃሪ ኬን የባሎን ዶር ሽልማትን ለማሸነፍ በዘመቻ ላይ ይገኛል፤ የሙኒክ አጨዋወት ስለሚስማማው ብቃቱ ይወርዳል ብዬ አልጠብቅም” በማለት አረጋግጠዋል፡፡ ሙኒክ በውርርድ ድርጅቶች ዘንድ አራተኛ ተገማች ክለብ ሆኗል፡፡ ጁሊየን ሎረንስ ግን ባየር ሙኒክን የፍጻሜ ተፋላሚ አድርገው መርጠዋቸዋል፡፡

ከእነዚህ ታላላቅ ክለቦች ባሻገር የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን በሦስት ተከላካዮች በሚገነባው ጥብቅ ዲሲፕሊን የታጀበ እጅግ አደገኛ ቡድን ሆኖ ቀርቧል፡፡ ኢንተር ሚላን በውርርድ ተቋማት ለዋንጫ ብዙ ግምት ያልተሰጠው ክለብ ቢሆንም ታላላቆቹን ክለቦች የመጣል ልዩ ታክቲካዊ ጥልቀት ግን እንዳለው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድም በዲያጎ ሲሞኔ ስር የተለመደውን እልህ አስጨራሽ የመከላከል ጥንካሬ ይዞ ቀርቧል፡፡ አትሌቲኮ ማድሪድም ልክ እንደ ጣሊኑ ክለብ ለዋንጫ ይደርሳል ተብሎ ግምት አልተሰጠውም፡፡አምስቱም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ወደ አስራ ስድስቱ የማለፍ ከሃምሳ በመቶ በላይ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ሊቨርፑል ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና አስቶን ቪላም  በፋይናንስ አቅማቸው እና ባላቸው የስብስብ ጥልቀት አማካኝነት በውድድሩ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡

በሴስክ ፋብሪጋስ የሚመራው የጣሊያኑ ኮሞ ዘንድሮ በዚህ በታላቁ መድረክ ልዩ ትኩረት ስቧል፡፡ ወጣቱ አማካይ ኒኮ ፓዝ በቡድኑ ውስጥ አስደናቂ ክህሎቱን እያሳየ ይገኛል፡፡ ጊለም ባላጌ “ሴስክ ፋብሪጋስ በኮሞ እያደረገ ያለውን ሥራ አደንቃለሁ፤ የጥሎ ማለፉን ደረጃ ይቀላቀላሉ ብዬ እጠብቃለሁ” በማለት አስረድተዋል፡፡ የኦስትሪያው ላስክ ሴልቲክን ጥሎ በማለፍ ጥሩ ብቃት አሳይቷል፡፡ የአዘርባጃኑ ሳባህ የተደራጀ መዋቅር ቢኖረውም ከአርሴናል እና ከባርሴሎና ጋር መደልደሉ ከባድ ፈተና ሆኖበታል፡፡

የኖርዌዩ ቫይኪንግም ወደ ጥሎ ማለፉ የማለፍ ዕድል እንዳለው ተነግሯል፡፡ፒኤስጂ እና ባርሴሎና ቢያንስ እስከ ግማሽ ፍጻሜው እንደሚጓዙ ይጠበቃል፡፡ ጁሊየን ሎረንስ ግን የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በአርሴናል እና በባየር ሙኒክ መካከል ሊደረግ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ሎረንስ “ውድድሩን ማን ያሸንፋል? ለሚለው ጥያቄ መልሴ አርሴናል ነው” በማለት ጽኑ አቋማቸውን አስቀምጠዋል፡፡ መድፈኞቹ ባለፈው ዓመት ያጡትን ዋንጫ ዘንድሮ በማድሪድ ከተማ በድል ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here