መከባበር

0
93

የአብሥራ ክንዴነው በሰላም አርጊው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት፤ መከባበር ምን ማል እንደሆነ ጠየቅናት፤ መከባበር ማለት ለሌላው ማሰብ፣ አክብሮት መስጠት ነው ትላለች፡፡ ልጆች የአብሥራ  ትክክል ናት አይደል? መከባበር ማለት የሌሎችን ሰዎች ስሜታቸውን እና ሀሳባቸውን በጥሩ ሁኔታ ማድነቅ እና ዋጋ መስጠት ማለት ነው።

እኛ ሁላችንም የተለያየን ሰዎች ነን፤ የተለያየ መልክ፣ ፍላጎት እና ባህሪ ሊኖረን ይችላል። ይህ ልዩነታችን ግን አንዱ ከአንዱ እንደሚበልጥ ሳይሆን ልክ እንደተለያዩ ውብ አበቦች በአንድ ላይ ሆነን ዓለማችንን እንደምናስውባት የሚያሳይ ነው። ሌሎችን ስናከብር እነሱም ለእኛ ያላቸው ፍቅር እና አክብሮት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።

በቤታችን እና በትምህርት ቤታችን ውስጥ መከባበርን የምናሳየው በጣም በቀላል ነገሮች ነው። ለምሳሌ ጓደኞቻችን ወይም ወላጆቻችን ሲናገሩ ሳናቋርጥ በጥሞና ማዳመጥ ትልቅ የአክብሮት መገለጫ ነው። እንዲሁም “እባክህ! እባክሽ!” እና “አመሰግናለሁ!” የሚሉትን ጣፋጭ ቃላት መጠቀም፣ የሌሎችን ሰዎች ዕቃዎች ያለፈቃድ አለመንካት እና በጨዋታ ጊዜ ተራን መጠበቅ መከባበርን በተግባር የምናሳይባቸው መንገዶች ናቸው። እነዚህ ትናንሽ ድርጊቶች በሰዎች መካከል ሰላም እና ደስታን ይፈጥራሉ።

መከባበር ሰዎችን ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ያሉትን እንስሳት፣ ዕፅዋት እና ተፈጥሮንም ያጠቃልላል። የምንኖርባትን ምድር ንፅህና መጠበቅ፣ ቆሻሻን በተገቢው ቦታ መጣል እና አበቦችንና ዛፎችን  አለመቅጠፍ ተፈጥሮን ማክበር ነው። እንስሳትን አለማስፈራራት እና በጥሩ ሁኔታ መንከባከብም የእኛ የልጆች ትልቅ ተግባር ነው። በዙሪያችን ያሉትን ህይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ስናከብር ተፈጥሮም ለእኛ ውብና ምቹ መኖሪያ ትሆንልናለች።

መከባበር በሁሉም ቦታ ላይ ፍቅርንና አንድነትን የሚዘራ መልካም ነገር ነው። ልጆች ገና ከልጅነታቸው ጀምረው ትላልቆችን በመታዘዝ፣ እኩዮቻችንን በመውደድና የተቸገሩትን በመርዳት መከባበርን የዕለት ተዕለት ልምዳቸው ሊያደርጉት ይገባል። መከባበር ባለበት ቦታ ሁሉ ጠብና ጭቅጭቅ አይኖርም፤ ይልቁንም ዓለማችን በሰላምና በደስታ ትሞላለች። ስለዚህ ሁልጊዜ አክባሪና ተወዳጅ ልጆች ለመሆን መጣር አለብን።

ተረት

አንበሳዉ እና ትንሹ ጥንቸል

በአንድ ትልቅ ጫካ ውስጥ ሁሉንም እንስሳት የሚያስፈራራ እና በጉልበቱ የሚመካ አንድ ትልቅ አንበሳ ይኖር ነበር። አንበሳው በየቀኑ ጫካ ውስጥ ያሉትን እንስሳት እያደነ ያስጨንቃቸው ስለነበር እንስሳቱ ተሰብስበው አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ወደ አንበሳው ሄደውም “ንጉሥ ሆይ! በየቀኑ እኛን እያሳደድክ ከምታስፈራራን እኛ ራሳችን በየተራችን በየቀኑ አንድ እንስሳ ምግብ እንዲሆንህ እንልክልሃለን” አሉት። አንበሳውም በሀሳቡ ተስማምቶ የሚላኩለትን እንስሳት እየጠበቀ መብላት ጀመረ።

አንድ ቀን ተራው ለአንዲት ብልህ ጥንቸል ደረሰ። ጥንቸሏ ወደ አንበሳው የሄደችው በጣም አርፍዳ እና ዘግይታ ነበር። አንበሳው በረሃብ ተቆጥቶ “ለምን ዘገየሽ?” ሲል ጮኸባት። ጥንቸሏም እየተንቀጠቀጠች “ንጉሥ ሆይ! እኔ እኮ ቀድሜ እየመጣሁ ነበር፤ ነገር ግን በመንገድ ላይ ሌላ በጣም ትልቅ እና አስፈሪ አንበሳ አጋጥሞኝ እሱ ሊበላኝ ሲል አምልጬ ነው” አለችው። አንበሳው በጫካው ውስጥ ሌላ ንጉሥ መኖሩን ሲሰማ በቅናትና በንዴት ጥርሱን አፋጨ። “የት ነው ያለው ያ አንበሳ? አሁኑኑ አሳዪኝ!” አላት።

ብልህዋ ጥንቸል አንበሳውን እየመራች በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ ጥልቅ እና ንጹሕ ውኃ ወዳለው የውኃ ጉድጓድ ወሰደችው። “ንጉሥ ሆይ! ያ አስፈሪ አንበሳ ያለው እዚህ ጉድጓድ ውስጥ ነው” አለችው። አንበሳው ወደ ጉድጓዱ ጎንበስ ብሎ ሲመለከት በውኃው ላይ የራሱን ጥላ አየ። ጥላው ሌላ ተቀናቃኝ አንበሳ መስሎት ክፉኛ አገሳ፤ በውኃው ውስጥ ያለው ጥላውም መልሶ ያገሳ መሰለው። በጥንቸሏ ታሪክ የተሸወደው አንበሳ ጥላውን ለመቅጣት እና ለመዋጋት ራሱን ወደ ጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ወረወረ። ውኃው ውስጥ ከገባ በኋላ መውጣት አቅቶት እዚያው ቀረ።

እንስሳቱ ሁሉ ጥንቸሏ በጉልበት ሳይሆን በብልሃት እና በዕውቀት ካመጣችላቸው ነፃነት የተነሳ ታላቅ ደስታ አደረጉ። ካለ አግባብ በጉልበት መመካት መጨረሻው ውድቀት መሆኑን፣ ብልሃት እና ማስተዋል ደግሞ ሁልጊዜ እንደሚያሸንፉ ተማሩ።

ምንጭ፡- የኤዞፕ ተረቶች

ሞክሩ

  1. ጥቁር አዞ ተጠማዞ ምንድን ነው?
  2. ጨረቃ ብርሃኗን ከምን ታገኛለች?
  3. ጉንዳን ስንት እግር አላት?

መልስ

  1. አስፋልት
  2. ከፀሐይ
  3. ስድስት እግሮች

ነገር በምሳሌ

ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ፡- አንድን ነገር በደንብ ማሰላሰል እና ማወቅ እንደሚያስፈልግ ይልጻል፤

የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ፡- ተቻኩለው ያደረጉት ነገር ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፤

አስተውሎ የሚጓዝ ብዙ ርቀት ይጓዛል፡- በማስተዋል የሠራነው ነገር ውጤታማ ይሆናል፡፡።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here