የክልሉ የኢኮኖሚ ተስፋ

0
194

አርሶ አደር ጋሻዬ እሸቴ ነዋሪነታቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም የቡናን በረከት ሳያውቁ የኖሩበትን ዘመን ዛሬ በቁጭት ያስታውሳሉ።

አቶ ጋሻዬ የዘገዩ ቢመስሉም ዛሬ ላይ ቆመው ወደ ፊት የሚያዩ ባለራዕይ  ናቸው። በአንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸው ላይ የጀመሩት የቡና ልማት ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ ቤተሰቦቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ማስተዳደር  ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ አድማሳቸውንም ቀይሮታል።

ባለፈው ዓመት ከአለሙት ቡና  ያገኙት ውጤት ተስፋ ሰጪ ነበር። ጠንክረው በመሥራታቸውም 30 ኩንታል ቡና በመሰብሰብ ጥሩ ገቢ ማግኘት ችለዋል። በተለያዩ አካባቢዎች  በአገኙት ሥልጠና መሠረት ጉድጓድ ቆፍሮ ኮምፖስት በማዘጋጀት፣ የችግኝ ርቀትን እንደ ዝርያው ጠብቆ በመትከል፣ ውኃ በማጠጣት እንደ ግራር፣ ዋንዛ እና ብርብራ ያሉ የጥላ ዛፎችን በሄክታር እስከ 25 እግር በመትከል ቡናቸውን ይንከባከባሉ። ወቅቱን ጠብቆ አረም በማረም እና የዛፉን ቅርንጫፍ ማሳሳት ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ እንደሆኑም ነግረውናል።

መንግሥት እና የሚመለከታቸው የግብርና ተቋማት የችግኝ አቅርቦትን  ፍላጎት ላላቸው ለሁሉም አርሶ አደሮች ተደራሽ ቢያደርጉ፣ በሽታን የመከላከል ቴክኖሎጂዎችን ቢያስተዋውቁ እና ተገቢውን የኤክስቴንሽን ድጋፍ ቢሰጡ አካባቢው በቡና ምርት የላቀ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ማንኩሳ አብደጎማ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር መንግሥቱ ዓለማየሁ ለበኵር በስልክ እንደገለጹት፤ “ወርቅ የሆነው የአማራ ክልል ቡና የራሱ መለያ (ብራንድ) ሊኖረው ይገባል!” ይላሉ። እርሳቸው ከቀደምት አያት ቅድመ አያቶቻቸው (በዘር ሀረግ) የተረከቡትን የቡና ልማት በዘመናዊ እውቀት እና ቴክኖሎጂ አሻሽለው ዛሬ ላይ የበርካታ አርሶ አደሮች አርአያ ለመሆን ችለዋል፡፡ ለዚህ ተግባራቸውም የሽልማቶች ባለቤት ለመሆን በቅተዋል።

አርሶ አደር መንግሥቱ ቡና በማልማታቸው በከተማ ቤት መገንባትን ጨምሮ ሌሎች ቋሚ ንብረቶችን ማፍራት ችለዋል። ከክረምት ዝናብ በተጨማሪ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን በመጠቀም በመስኖ  ቡና በስፋት በማልማት ላይ መሆናቸውንም ገልጸውልናል።

አቶ መንግሥቱ ዓለማየሁ በመጨረሻም “እኛ በቴክኖሎጂ ታግዘን በጥራት ለማምረት ሌት ተቀን እየደከምን ነው። አሁን የሚቀረው ባለሙያው እና መንግሥት ተባብረው የአማራን ቡና በዓለም አደባባይ የራሱ መለያ እንዲኖረው ማድረግ ብቻ ነው!” በማለት መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ ታመነ ፍቅሬ  እንደገለጹት በዞኑ የቡና ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨባጭ ውጤት እያሳየ ነው፡፡ የአርሶ አደሩ የማልማት ተነሳሽነት እና ቴክኖሎጂን የመቀበል አቅምም እየተሻሻለ መጥቷል።

በዞኑ ባሉ በሁለት የከተማ አስተዳደሮች እና በሰባት የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ቡና ይመረታል፡፡  በተለይ ጃቢ ጠህናን፣ ፍኖተ ሰላም ከተማ፣ የቡሬ ዙሪያ፣ ቡሬ ከተማ፣ ደምበጫ እንዲሁም ወንበርማ ወረዳዎች በቡና ልማት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።

በተለይም ጃቢ ጠህናን ወረዳ እንደ ወይንማ፣  ጂጋ፣ አባሰም፣ ማንኩሳ፣ ዛባ፣ ጓይ የውብሸትና ጎረፍ የመሳሰሉ ቀበሌዎች የዞኑ የቡና እምብርት ሆነው ብቅ ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ቡና ሲነሳ የባከል እና የሸምበቁማ (የፍኖተ ሰላም አካባቢ) ቡና ስም አብሮ ይነሳል። በተለይ በልዩ ጣዕሙና መዓዛው የሚታወቀው የባከል ቡና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ክብር አለው። ሆኖም ይህ የቡና ዝርያ አሁን ላይ እንደ ቀደመ ስሙ ተደጋግሞ አይጠራም።

ቡድን መሪው ለበኵር በስልክ እንደገለጹት የተሻሻሉ አዳዲስ የቡና ዝርያዎች በስፋት እየገቡ በመምጣታቸውና አርሶ አደሩም እነሱን በመተካቱ ምክንያት ነባሩ የባከል ዝርያ ሽፋን እየቀነሰ ይገኛል። “የባከል ቡናን የራሱን ማንነትና ዝርያ አስጠብቆ የብራንድ ማረጋገጫ ሰጥቶ ለዓለም አቀፍ ገበያ ማስተዋወቅ ላይ ክፍተቶች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ዝርያውን ለይቶ ተገቢውን አስተዳደራዊ ድጋፍ ሰጥቶና ከገበያ ጋር አስተሳስሮ በብራንድ ደረጃ የማስቀጠሉ ሥራ ሰፊ ርብርብ ይፈልጋል” በማለት የዘርፉን አሳሳቢነት  ጠቁመዋል።

አርሶ አደሮች በጓሮ፣ በተፋሰስ፣ በክላስተር እና ያረጁ ዛፎችን በአዳዲስ በመተካት እየሠሩ ይገኛሉ። ባለፈው ዓመት መጨረሻም ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ተተክለዋል፡፡ ከጂማ የግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙ ምርጥ ዝርያዎችን በመንግሥት ችግኝ ጣቢያዎች በማባዛት ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።

እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ ባለፈው የምርት ዘመን በዞኑ ውስጥ ከአራት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የቡና ምርት መስጠት ጀምሯል፡፡ አሁን ላይ የዞኑ አጠቃላይ የቡና ሽፋን ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ ደርሷል። በያዝነው ዓመትም ከ30 ሺህ ኩንታል ያላነሰ የቡና ምርት ለገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል። ምንም እንኳ ምርቱ ለሀገር ውስጥ ገበያ በስፋት እየቀረበ ቢሆንም በቀጥታ በኅብረት ሥራ ማህበራትና በዩኒየኖች በኩል ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ረገድ ግን አሁንም ተጨማሪ የቤት ሥራዎች አሉ።

ቡና እንደ ማንኛውም ሰብል በአጭር ጊዜ ብቻ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ቋሚ ተክል በመሆኑ ጥብቅ ክትትልን እንደሚሻ አቶ ታመነ ያስገነዝባሉ። ሌላው ቡና በባህሪው ጥላ ወዳድ ተክል በመሆኑ ሳይንሳዊ የምክር ሐሳብን የተከተለ ተስማሚ የጥላ ዛፍ ከሌለው ጥራቱን እና ምርታማነቱን በዘላቂነት ማስጠበቅ አይችልም።

ዘርፉን ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲለወጥ ከተፈለገ፤ የመስኖ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ በብራንድ ደረጃ ወደ ውጭ ገበያ ማውጣት እና የኤክስፖርት ትስስሩን ማጠናከር የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸው።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሆርቲካልቸርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ መኮንን በክልሉ የቡና ልማት ወቅታዊ ገጽታ፣ ተግዳሮቶች እና የወደፊት የብርሐን ጭላንጭሎች ዙሪያ ለበኵር ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በክልሉ ከ36 ሺህ 137 ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት የተሸፈነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ22 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው ምርት መስጠት ጀምሯል፡፡ በዘንድሮው ዓመትም ከ141 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል።

በዋናነት ምዕራብ አማራ ተብለው በሚታወቁት ስምንት ዞኖች (ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ባሕር ዳር ዙሪያ፣ ሰሜን፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ) ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል።

ሆኖም አሃዞቹ ተስፋ ሰጪ ቢመስሉም የምርታማነት መጠኑ ግን አሁንም ገና ነው። በአሁኑ ወቅት አማካይ ምርታማነቱ በሄክታር ስድስት ኩንታል ብቻ ነው። ይህ አሃዝ ከሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ አንጻር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ዘመናዊ የአመራረት ቴክኖሎጂዎችን፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን እና የተጠናከረ የሰብል እንክብካቤን በአግባቡ ባለመተግበር የሚመነጭ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። እነዚህን ዞኖች ወደ ምርት ቀጣናነት ለመቀየር የተነደፉት ዋና ዋና ስልቶችም የክላስተር እርሻ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎች፣ ቴክኖሎጂ፣ የተሟላ እንክብካቤ እና ተጓዳኝ ሰብሎች ናቸው።

የአማራ ክልል ቡና ከዚህ ቀደም የውጭ ገበያን የማያውቅ አልነበረም። ከ2009 እስከ 2016 ዓ.ም አየሁ እርሻ ልማት እንዲሁም በአማራ ቡና ዩኒየን አማካኝነት ለዓለም ገበያ ቀርቦ ነበር። ይሁን እንጂ በክልሉ በነበሩ አለመረጋጋቶች እና በበጀት እጥረት  የወጭ ንግዱ ተቋርጦ ቆይቷል።

በዘንድሮው ዓመት (2019 ዓ.ም) ይህንን የታመቀ አቅም ዳግም እንዲያንሰራራ  ከስድስት ሺህ 800 ኩንታል በላይ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። ሆኖም ለዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የብራንዲንግ ስራ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ተነስቷል። እንደ ባከል እና  ዘጌ ያሉ በአጠቃላይ  የጎጃም እና የጎንደር ቡና ዝርያዎች የየራሳቸው የሆነ ልዩ መዓዛና ጣዕም ያላቸው ቢሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባቸውን ስያሜና የባለቤትነት መታወቂያ አላገኙም።

በዚህ ዓመት ብቻ ክልሉ 30 ሚሊዮን የቡና ችግኞችን አፍልቶ 12 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ለመሸፈን አቅዷል። ለዚህም የሚያስፈልገውን 97 ኩንታል የቡና ዘር የማዘጋጀት ሥራ ተጠናክሮ እስካሁን ከ63 ኩንታል በላይ ዘር ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።

“ቡና አንዴ ተክለው የሚተውት ሳይሆን ልክ እንደ ሕጻን ልጅ በየዕለቱ ክትትልና እንክብካቤ የሚፈልግ ተክል ነው” ያሉት  አቶ አበበ የቡና ልማቱ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር የግብርና ቢሮ፣ የመንግሥት፣ የምርምር ተቋማት እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝ መሆኑም አመላክተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት የየአካባቢውን ዝርያዎች በጥናት ለይተው፣ የጥራት ደረጃቸውን ፈትሸውና ብራንድ አውጥተው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

 

መረጃ

በክልሉ የቡና ምርታማነትን ለመጨመር የተነደፉት ዋና ዋና ስልቶች፡-

የክላስተር እርሻ፦ አርሶ አደሩ ቡናን በተበታተነ ማሳ ከማምረት ወጥቶ በአንድ ቀበሌ ከ20 እስከ 100 ሄክታር በሚደርሱ ሰፋፊ ክላስተሮች ተደራጅቶ እንዲያለማ ማድረግ፤

የተሻሻሉ ዝርያዎች እና ቴክኖሎጂ፦ የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል ያወጣቸውንና በሄክታር እስከ 27 ኩንታል የሚሰጡ ከፍተኛ ምርታማ የድቃይ ዝርያዎችን ማስፋፋት፤

የተሟላ እንክብካቤ፦ አግሮ-ኢኮሎጂን የጠበቀ የጥላ ዛፎች ተከላ (እንደ ኮባና ሰስባኒያ ያሉ ጊዜያዊ እና ቋሚ ዛፎች) እንዲሁም ጥብቅ የአረምና የኩትኳቶ ሥራዎችን ማከናወን፤

ተጓዳኝ ሰብሎች፦ ቡናው ሙሉ ምርት እስኪሰጥ ባሉት የመጀመሪያ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት አርሶ አደሩ በስሩ አትክልቶችንና የጓሮ ሰብሎችን በማልማት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ማስቻል ናቸው።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here