ሴኔጋላውያን  ያወደሱት የባሕርዳር ስታዲየም

0
191

የደረጃ የማሻሻያ ግንባታዎችን ሲያከናውን የቆየው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያ እና ሴኔጋልን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታን ለማስተናገድ ከካፍ ጊዜያዊ ፈቃድ ሲሰጠው  የመጫወቻ ሜዳው አሁን በሚገኝበት የጥራት ደረጃ ይሆናል ብሎ የገመተ አልነበረም።

ሆኖም የኢትዮጵያ እና ሴኔጋል ጨዋታ ከመደረጉ አንድ ቀን በፊት ለልምምድ ወደ ባህርዳር ስታዲየም ያመሩት የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አባላት ከዋና ከተማይቱ ርቆ በሚገኝ ከተማ ውስጥ በላቀ የደረጃ ጥራት የደረጃ ያን የመሰለ ስታዲየም እና አስደናቂ የመጫወቻ ሜዳ ይገነባል ብለው  እንዳልጠበቁ ከልምምድ መርሃ ግብራቸው በፊት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የብ/ቡድኑ አባላት የመጫወቻ ሜዳው ከዚህ በፊት በሌላ ሀገር ሲጫወቱ ከተመለከቷቸው ሜዳዎች በእጅጉ የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አአሰልጣኝ ፓትሪክ ቬራ ተናገሯል። ይህ ልብ የሚያሞቅ አስተያየት ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማያውቅ በመሆኑ የሜዳ ችግር ገጥሞት ለማንከራተት ፌዴሬሽን እና ብሄራዊ ቡድን ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር ስታዲየሙን እየገነቡ ለሚገኙት አካላት ትልቅ ደስታ የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል።

የባሕርዳር ዓለም አቅፍ ስታዲየም የደረጃ ማሻሻያ ግንባታ ሲያከናውን ከሌሎች ግንባታዎች ጎን ለጎን የመጫወቻ ሜዳው ብቻውን ባለፉት ሁለት አመታት በልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደ አዲስ ሲገነባ ከዚህ ቀደም ከሚነሱበት የጥራት መጓደል ጥያቄዎች ጋር በተገናኘ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መገንባቱ ችግሩን እንደ ቀረፈው የክልሉ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ተናግሯል።

 

በሌላ በኩል ደግሞ ይህን የመጫወቻ ሜዳ በዚህ የጥራት ደረጃ ልክ የገነባው ግሪጎሪ የተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ ሲሆን ከ50 ዓመታት በላይ በአፍሪካ መሰል የመጫወቻ ሜዳዎችን በመገንባት ልምድ ያካበተ ሲሆን የመጫወቻ ሜዳው አፍሪካ ውስጥ በካፍ ፈቃድ የተሰጠው የመጀመሪያው ስታዲየም ይህ ሜዳ ስለመሆኑ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አብደራዛቅ ካሲ ለአሚኮ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ከሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት የመጫወቻ ሜዳው ሳሩን ጨምሮ የውሃ ማጠጫው እና የተዘረጋው የተፋሰስ ስርአቱ በጥንቃቄ በመገንባቱ አሁን ሜዳው ብዙዎች የወደዱትን የጥራት ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ተናግረዋል።

የግሪጎሪ ኩባንያ የኢትዮጵያ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አብዱራዛቅ ካፊ ሲቀጥሉ የባሕርዳር ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳው ቀላሉ የግንባታ እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል። ሆኖም ከባዱ፣  ልዩ ክትትል የሚፈልገው ጉዳይ በቀጣይ የሚደረግለት እንክብካቤ እና ጥገናው ልዩ ትኩረት የሚፈልገው ጉዳይ ነው ብለዋል።

የመጫወቻ ሜዳው በቀን ሁለት ጊዜ ውሃ ይጠጣል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ሜዳው ከጨዋታ እና ልምምድ ካከናወነ በኋላ ወዲያውኑ ጥገና ማድረግ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል። የመጫወቻ ሜዳው ክትትል ይፈልጋል፤ መብላት፣ መጠጣት እረፍት እንክብካቤ እና ልዩ ክትትል የሚደረግለት ህጻን ልጅ ቶሎ እንደሚያድግ ሁሉ ይህ ሜዳም ተመሳሳይ ነገር ይፈልጋል ሲሉ ነበር አብዱራዛቅ ካፊ የገለጹት።

በካፍ ግምገማ መሰረት የበርካታ የአፍሪካ ስታዲየሞች ችግር ለሜዳው የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ያስረዳል። እንዲያውም አንድ ስታዲየም ጣራ እና ወንበር ባይኖረው እንኳን የመጫወቻ ሜዳው ደረጃ የተሻለ ሆኖ ከተገኘ በካፍ በኩል ይሁንታ እንደሚሰጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የባሕርዳር ስታዲየም በካፍ የተጠየቁት መስፈርቶች እየተሟሉ ሲሆን የካፍ ገምጋሚ ልዑክ በድጋሚ መጥተው ስታዲየሙን የተመለከቱ በመሆናቸው ከደረጃ ሦስት ወደ ደረጃ አራት ከፍ ያለ ፈቃድ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም  የሀገራችን ስታዲየሞች የሌላቸውን ጥራቱን የጠበቀ የመጫወቻ ሜዳ አሟልቶ የያዘ በመሆኑ ለብዙዎች አስተማሪ ስለመሆኑ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

አሁን ይህ ሜዳ ከካፍ ሌላ መልካም ዜና እየጠበቀ ይገኛል።አሁን ላይ በካፍ እውቅና ደረጃ ሦስት ይሰጠው እንጅ በአጭር ጊዜያት ደረጃ አራት ያገኛል ተብሎም ይጠበቃል።ይህ እንዲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከካፍ ጋር ተቀናጅቶ እየስራ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተናግሯል።

የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ምስክር ሰውነት በሰጡት አስተያየት ስታዲየሙ በተለይም የመጫወቻ ሜዳው በሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና አባላት ዘንድ አድናቆት ያገኘው ክልሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ነው ነበር ያሉት።

አንድ ስታዲየም ሲገነባ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ሥራዎች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው የመጫወቻ ሜዳ ነውና ከዓመታት በኋላ አሁን ላይ በባሕርዳር ስታዲየም  የተገነባው የመጫወቻ ሜዳ በልዩ ትኩረት እና በእንክብካቤ ሊያዝ እንደሚገባ ሀሳብ የሰጡት ሜዳውን እየገነባ የሚገኘው የፈረንሳዩ ኩባንያ  የግሪጎሪ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አብዱራዛቅ ካፊ ናቸው።

 

(መልሰው ጥበቡ)

በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here