የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን “ሙስና ከድህነት የበለጠ አደገኛ ነው። ድህነት ሰዎችን ሲያደቅቅ፣ ሙስና ግን የኅብረተሰቡን ሞራል እና ተስፋ ይገድላል” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ በተመሳሳይ የነጻነት አባት በመባል የሚታወቁት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ሙናን “የሕዝብ ሀብትን መስረቅ የሰዎችን ህይወት ከመስረቅ ጋር እኩል ነው” ሲሉ ነው የሙስናን አስከፊነት የገለጹት፡፡
ሙስናን መዋጋት ላይ ትኩረቱን በማድረግ መረጃዎችን የሚያጋራው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ደግሞ “ሙስና በሰዎች ወይም በተቋማት የተሰጠን ሕጋዊ ስልጣን፣ ኃላፊነት ወይም አደራ ለግል፣ ለቤተሰብ ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል ከሕግ ውጭ ማዋል ነው” ሲል ይተረጉመዋል። ጉቦ መቀበል ወይም መስጠት፣ የሕዝብን ሀብት መዘረፍ ወይም ማባከን፣ ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም እና በዘመድ አዝማድ መጠቃቀም ደግሞ ዋና መገለጫዎቹ እንደሆኑ ነው ያመላከተው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀጣይ አምስት ዓመታት “ሙስናን ለማጥፋት መረር ያሉ እርምጃዎች ይወሰዳሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስጠንቅቀዋል፤ የኢትዮጵያ አዲሱ የመንግሥት ዘመን ሲጀመር፣ የሙስና ትግል ዳግም የፖለቲካው መድረክ ትኩረት ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በመስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የሁለተኛ የሥራ ዘመናቸውን ሲጀምሩ፣ ከመንግሥት መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ጎን ለጎን በሙስናና በዘመድ አዝማድ አሠራር ላይ የተጠናከረ ተቋማዊ ርምጃ እንደሚወሰድ ቃል ገብተዋል። የሕዝብ ወጪ ቁጥጥርና የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያም የዚሁ ቃል ኪዳን አካል ሆነው ተጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት ሙስናን፣ ሌብነትን፣ የዘመድ አሠራርን እና ወገንተኝነትን ለማስወገድ መረር ያሉ እርምጃዎች ይወሰዳሉ።
በተመሳሳይ ሙስናንና ሌብነትን የሚጸየፍ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ ብልሹ አሠራርን በመታገል ተቋማትን በጥንካሬና በቁጥጥር ሥርዓት ለማጠናከር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አስታውቀዋል።
ይሁንና፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፀረ-ሙስና ንግግሮችንና ዘመቻዎችን ሲሰማ የመጀመሪያው አይደለም። ፈተናው ያለው ቃሉ ላይ ሳይሆን፣ቃሉ ወደ መሬት ወርዶ በተቋማዊ አሠራር ሲመዘን ነው፡፡
የችግሩ ሥረ-መሠረት፡ ግለሰብ ወይስ ሥርዓት?
ሙስና በአብዛኛው የሚመነጨው ከአንድ ባለሥልጣን የግል ስግብግብነት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም አሠራሩ በሚፈጥርለት ክፍተት ነው።
ደካማ ቁጥጥር፣ የግልጽነት እጥረት፣ የተዘጋ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እና “ማን ይጠይቀኛል?” የሚል የዳበረ የድፍረት ስሜት ሲጣመሩ፣ ሙስና እንደ ሸረሪት ድር ተቋማትን ይጠቀልላል።
በተለይም የዘመድ አዝማድ አሠራር የሙስናው ዋነኛ በር ከፋች ነው። አንድ ተቋም ብቃትንና ዕውቀትን ወደ ጎን ትቶ በዝምድና፣ በቡድንተኝነት ወይም በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ የሚመራ ከሆነ፣ ተቋሙ ራሱን ለሌብነት እያዘጋጀ ነው ማለት ነው።
በችሎታው ሳይሆን በግንኙነቱ ሹመት ያገኘ ግለሰብ፣ ለተቋሙ ራዕይ ሳይሆን ላሾመው አካል ወይም ለግል ከረጢቱ ማደሩ የማይቀር የተፈጥሮ ሕግ ነው።
ሙስና ሀገርን የሚጎዳው በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ስለሚመዘበር ብቻ አይደለም። ትልቁ ኪሳራ ‘የሕዝብ አመኔታ’መሸርሸሩ ነው። የሕዝብ ሀብት ከልማት ወደ ጥቂቶች ኪስ ሲገባ፤ ብቃትና ተሰጥዖ ያለው ወጣት በዘመድ አዝማድ አሠራር ምክንያት የሥራ ዕድል ሲነፈግ፤ እንዲሁም ፍትሕ በገንዘብ ሲገዛ፣ ዜጎች በሀገራቸውና በመንግሥት ተቋማት ላይ ያላቸው ተስፋ ይጨልማል።
ከሁሉ በላይ አደገኛው ደግሞ፣ ሙስና እንደ “ብልጠት” መታየት መጀመሩና ሐቀኛ ዜጎች እንደ “ሞኝ” የሚቆጠሩበት የሞራል ውድቀት ባህል መፈጠሩ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ የሙስና ትግል ቃል ኪዳን አልፎ እውነተኛ ለውጥ እንዲያመጣ፣ የተወሰኑ “ሙሰኞችን” በማሰር በሚደረግ የሚዲያ ዘመቻ ላይ ብቻ መቆም የለበትም። ትኩረቱ ሙስናን በሚያመነጩ የሥርዓት ክፍተቶች ላይ ሊያነጣጥር ይገባል ተብሏል።
የአማራ ክልል የፍትሕ እና ሕግ ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) ሙስናን ለማድረቅ በርካታ ተግባራት መከናወን አለባቸው። ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማትን ማነጽ፣ የዲጂታልና ግልጽ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት፣ የጥቅም ግጭትን በሕግ መዝጋት፣ ሹመትና ቅጥር በግልጽ የብቃት መመዘኛ ላይ መመሥረት እና ሙስና ጠቋሚዎችን መጠበቅ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
እንደ ዶ/ር ደሴ ማብራሪያ የፀረ-ሙስና ተቋማት የፖለቲካ ጫና ሳያርፍባቸው፣ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ሳይቀር ምርመራ የማድረግ ሙሉ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል። ሕግ ለታችኛውም ለላይኛውም እርከን በእኩል መሥራት አለበት። ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማትን ማነጽ ነው።
ትልቁ የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት የሚመዘበረው በግዥና በጨረታዎች ላይ ነው። እነዚህ አሠራሮች ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነና ማንም ዜጋ ሊከታተለው በሚችል ዲጂታል ሥርዓት መመራት አለባቸው። ባለሥልጣናት ሀብታቸውን የማስመዝገብና ከጥቅም ግጭት ነፃ መሆናቸውን የማረጋገጥ ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪም ሙስናን የሚያጋልጥ ዜጋ ከበቀል የሚጠበቅበት ጠንካራ የሕግ ከለላም ያስፈልጋል።
የውጭ ሀገራት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ ቃላት ተቋማትን አይገነቡም፤ ተግባር እንጂ። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያሳየው ሲንጋፖር ሙስናን ታሪክ ያደረገችው ከባድ ቅጣት በመጣል ብቻ አይደለም። የፀረ-ሙስና ቢሮ በተቋማት ውስጥ ያለውን የሥርዓት ክፍተት እያጠና የሚያስጠግን ጠንካራ አሠራር ስለዘረጋ ጭምር ነው።
በተመሳሳይ ጆርጂያ እ.አ.አ ከ2003 በኋላ በሙስና ላይ ድል የተቀዳጀችው፣ ሙሰኞችን ከማሰርባለፈ የተወሳሰቡ የቢሮክራሲ አሠራሮችን በማቃለል የሙስና መፈጸሚያ ቀዳዳዎችን በመድፈኗ ስለመሆኑ ነው የመረጃ ምንጩ የሚያብራራው።
ኢትዮጵያም የምትፈልገው ይህንኑ ሥር ነቀል የተቋም ለውጥ ነው። ይህንን ስር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት፣ ሙስናን ለመከላከልና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ተቋማት እንዴት መገንባት እንዳለባቸው ዶ/ር ደሴ ጥላሁን ሐሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ ሙስናን ከምንጩ ለማጥፋት “የሚከተሉትን መሠረታዊ ሐሳቦች መተግበር አለባቸው” ይላሉ ዶ/ር ደሴ፡፡
በብቃት ላይ የተመሠረተ አስተዳደር (ሜሪቶክራሲን) መገንባት ይገባል። ሙስናን ለማጥፋት ዋነኛው መፍትሔ ቢሮክራሲውንና ተቋማትን ከዘመድ አዝማድና ከፖለቲካ ታማኝነት ማጽዳት ነው።
ዶ/ር ደሴ አክለው እንዳስገነዘቡት ወደ ሲቪል ሰርቪሱና አመራርነት የሚመጡ ሰዎች በዘር፣ በዝምድና ወይም በፖለቲካ አገልጋይነት ሳይሆን በዕውቀትና በብቃት ብቻ መመደብ አለባቸው። ተቋማት በፖለቲካ ታማኞች ብቻ ከተሞሉ ብቃት አልባነት ይነግሣል። ይህ ደግሞ ሙስናን ስር እንዲሰድ በማድረግ ሀገርን እስከማፍረስ ሊደርስ የሚችል መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።
ተቋማትም የሙስና መፈጸሚያ እንዳይሆኑ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆን አለባቸው። የትኛውም ተቋም ውሳኔ ሲያሳልፍ በፖለቲካዊ ጫና ሳይሆን በሕግ፣ በዕውቀትና በሙያዊ ብቃት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል።
ያልተገደበ ሥልጣን ሙስናንና አምባገነንነትን እንደሚወልድ የጠቀሱት ዶ/ር ደሴ ይህን ችግር ለማስቀረት ደግሞ የሥልጣን ክፍፍልና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ስለዚህ ሙስናን ለመከላከል ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው እና ሕግ ተርጓሚው ተቋም አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበትና ሚዛን የሚጠብቅበት አሠራር መገንባትም አለበት።
እንደ ዶ/ር ደሴ ማብራሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስናን ለማስወገድ የምርጫ (ዴሞክራሲ) ጉዳይ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ምርጥ አዕምሮዎችን እና ብቃትን የተላበሱ፣ በሕግ እንጂ በፖለቲካ ጫና የማይዘወሩ ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት ግድ ይላል።
ስለዚህ መንግሥት የቱንም ያህል ጠንካራ ሕግ ቢያወጣ፣ ዜጋው ሙስናን እንደ “መደበኛ የሕይወት አካል” ከተቀበለው ትግሉ ከንቱ ነው። ሙስናን ለማሸነፍ ተቋማዊ ሪፎርም እና የዜጎች የባሕል ለውጥ በአንድነት መጓዝ አለባቸው። ዜጋው ጉቦ ከመስጠትና ከመቀበል መቆጠብ፣ የተሳሳቱ አሠራሮችን አለመተባበርና የሕዝብ ሀብትን መታደግ የዘወትር ኃላፊነቱ ሊያደርግ ይገባል።
ስንት የሙስና ቀዳዳ ተዘጋ? ስንት ተቋም ግልጽ አሠራር ዘረጋ? የዜጎችስ አመኔታ ምን ያህል ተመለሰ? የሚሉትን ነጥቦች በተግባር መመለስ ሙስናን ለመዋጋት ለሚደረገው ትግል መሠረት ይሆናሉ። የመንግሥት ቃል በተግባር ሚዛን ሲለካ ውጤቱ የሚያምር እንዲሆን፣ ትግሉ ከዘመቻ ወደ ሥርዓት ግንባታ መሸጋገር አለበት። የተገባው ቃል ይህንን ተቋማዊ ሐቅ ካረጋገጠ ደግሞ የሙስናው አዙሪት ታሪክ ሆኖ ይቀራል።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


