የኢቦላ ጥላ በምሥራቅ አፍሪካ

0
10

ኢቦላ በቫይረሱ አማካኝነት በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ፣ በሰው ኣካል ውስጥ በመባዛት እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ  ነው። ኢቦላ ስሙን ያገኘው ቫይረሱ በ1968 ዓ.ም. መጀመርያ ከተገኝበት ከኢቦላ ወንዝ ዛኢር ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በያዝነው የጥቅምት ወር 2026 እ.አ.አ አንድ ኬኒያዊ ግለሰብ በኢቦላ በሽታ በኬኒያ ሞቷል፡፡ የላብራቶሪ ምርመራው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተቀሰቀሰው ቡንዲቡጎዮ ዝርያ በሆነው ኢቦላ ቫይረስ እንደተያዘ አረጋግጧል።

በኢቦላ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጎዱ አካባቢዎች በአንዱ የቆየው ኬንያዊ ነጋዴ ሕመሙ ከመታወቁ በፊት ወደ ሁለት ተጨማሪ ሀገራት መጓዙ ታውቋል። የ40 ዓመቱ ግለሰብ በጠና ታሞ በናይሮቢ ሆስፒታል ከገባ በኋላ የምርመራው ውጤት  የኢቦላ ቫይረስ መሆኑ ታወቀ፡፡

ቫይረሱ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኙ በርካታ የጤና ተቋማት እና በኡጋንዳ እና ኬንያ ሁለት የአየር ማረፊያ የጤና ምርመራ ጣቢያዎች ሳይለይ መቅረቱ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2026 ብቻ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አራት ሽህ ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም እስካሁን ከተቀሰቀሱ ከባድ ወረርሽኞች ውስጥ ሁለተኛው ገዳይ በሽታ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የኬንያዊ ታማሚ የስድስት ሳምንታት እንቅስቃሴ ተከታትሎ ቫይረሱን ለመለየት በርካታ እድሎች እንዳመለጡ ገልጿል።

የተቋሙ የድንገተኛ በሽታዎች ዳይሬክተር ዶ/ር ውሳም ማንኮላ ነጋዴው ግለሰብ ታማሚ ሆኖ እንዴት በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ሊጓዝ እንደቻለ ግልፅ ስዕል ሰጥተዋል። ማንነቱ ለሕዝብ ይፋ ያልሆነው ግለሰብ ለሰባት ዓመታት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኖረ እና በሦስት ግዛቶች ውስጥ ለንግድ የተጓዘ ነው፡፡ የጤና ሁኔታው ከመባባሱ በፊት በለይቶ ማቆያ እንዲቆይ ከተደረገ ከቀናት በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

የኬንያ መንግሥት ግለሰቡ ሀገር ቤት ከገባ ጀምሮ ንክኪ አላቸው የተባሉ 66 ሰዎች መለየታቸውን አስታውቋል። በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኡጋንዳ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ለመለየት ጥረቱ በመቀጠሉ የዓለም የጤና ድርጅት ይህ ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል  ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ ዘግቧል። የዓለም ጤና ድርጅት “በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ አሳሳቢ ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ” ሲል አውጇል።

ኢቦላ ምንድን ነው? ምልክቶቹስ?

ኢቦላ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ የሆነ ተላላፊ በሽታ ነው። እንደ ሚድስከቨር ሆስፒታል መረጃ ከባድ እና ብዙ ጊዜ ገዳይ በሽታ የሆነው ኢቦላ ኢቦላ በተባለ ቫይረስ ይከሰታል። ይህ ቫይረስ የፊሎቨርዴ ቤተሰብ ሲሆን በሰዎች እና በሌሎች ፍጥረቶች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡

የቫይረሱ ትክክለኛ አመጣጥ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይሆንም ከእንስሳት የተገኘ እና ወደ ሰው ሊተላለፍ የሚችል ነው፡፡ በተለይ የሌሊት ወፎች የቫይረሱ ተፈጥሯዊ ማጠራቀሚያ ተደርገው ይወሰዳሉ በዚህም ምክንያት ቫይረሱን ተሸክመው ወደ ሰዎች ሊያስተላልፉት ይችላሉ፡፡

የኢቦላ ስርጭት የሚከሰተው በበሽታው ከተያዘ ሰው ወይም ከእንስሳት የሰውነት ፈሳሽ ጋር በቀጥታ ንክኪ ነው፡፡ ይህም ቫይረሱ   በደም፣ ምራቅ ወይም ሽንት ይተላለፋል።

በኢቦላ የተያዘ ሰው መጀመሪያ ላይ የሚያሳየው  ምልክት ከወባ እና ታይፎይድ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው የሚረጋገጠው ግን በቤተ ሙከራ በሚደረግ ምርመራ ብቻ ነው። ዋናዎቹ ምልክቶችም ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ከፍተኛ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም እና ጉሮሮ መከርከር ናቸው።

ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ሲሠራጭ ደግሞ ማስመለስ እና ማስቀመጥ ይከሰታል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሰውነታቸው ውስጥ እና ከሰውነታቸው ውጪ ደም ይፈሳቸዋል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ምልክት የሚያሳዩት በቫይረሱ ከተያዙ ከሁለት እስከ 21 ቀናት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ኢቮላ አምስት ተለይተው የታወቁ የቫይረስ ዝርያዎች ሲኖሩት እነሱም ዛየር፣ ሱዳን፣ ቡንዲቡግዮ፣ ታኢ ደን  እና ሬስቶን ኢቦላ ቫይረስ ናቸው። እያንዳንዱ ዝርያ በጂኦግራፊያዊ ስርጭት፣ በቫይረሱ ዓይነት (በቫይረቴሽን) እና ተያያዥ ወረርሽኞች ምክንያት ይለያያል፡፡

ዛየር ኢቦላ ቫይረስ በአፍሪካ ከተከሰቱ  የኢቦላ ወረርሽኞች መንስኤ የሆነው፣ በጣም የተለመደው እና ገዳይ የሚባለው ዝርያ ነው። በኢቦላ የቫይረስ ዓይነቶች መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት የሚቻለው ወረርሽኙ በሚከሰትበት ጊዜ ውጤታማ የአስተዳደር እና የማቆያ ስልቶችን ለማግኘት ወሳኝ ስለሆነ ነው። እያንዳንዱ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያ ተመሳሳይ ምልክቶችን ሊያስከትል ይችላል፤ ነገር ግን በበሽታው ክብደት ሊለያይ ይችላል፡፡ የዛየር ዝርያ ከፍተኛውን የሞት መጠን አስመዝግቧል።

በሽታው ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የሚወጣ የሰውነት ፈሳሽ ጋር የሚኖር ንክኪ ነው። እነዚህም ደም፣ ምራቅ፣ የወንድ የዘር ፈሳሽ፣ ከሴት ብልት የሚወጣ ፈሳሽ፣ ሽንት፣ ሰገራ እና ላብ ናቸው። ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ የነካቸው ቁሳቁሶችም በሽታውን ያስተላልፋሉ። ዐይን፣ አፍንጫ፣ አፍ እና  ስንጥቅ ያለው የቆዳ ክፍል በመንካት ቫይረሱ ይተላለፋል፡፡

የሌሊት ወፍ፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጃርት እና ድኩላ በሽታውን የሚያስተላልፉ እንሰሳት ናቸው። ለምግብነት የሚታደኑ የዱር እንሰሳት ሥጋ ላይ ቫይረሱ ሊኖር ይችላል። በኢቦላ ሳቢያ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን መንካትም ለበሽታው ያጋልጣል። ዛየር ለሚባለው የኢቦላ ዝርያ ክትባት ተገኝቷል። የሱዳን የኢቦላ ዝርያን ጨምሮ ለሌሎችም የኢቦላ ዓይነቶች ደግሞ ክትባት ወይም መድኃኒት ለማግኘት ሳይንቲስቶች ምርምራቸውን ቀጥለዋል።

የኢቦላ ሕክምና በዋነኝነት የሚያተኩረው ምልክቶችን እና ችግሮችን ለመቆጣጠር በድጋፍ ሰጪ እንክብካቤ ላይ ነው። በሆስፒታሎች ውስጥ ሐኪሞች ለሕሙማን ድጋፍ ይሰጣሉ። የውኃ ጥምን መቁረጥ ፣ እንደ ሶዲየም፣ ፖታሽየም፣ ካልሽየም እና ማግኒዥየም ያሉ ንጥረ ነገሮችን ማመጣጠን  እንዲሁም ደም በመለገስ በሕይወት የመትረፍ ዕድልን መጨመር ከሕክምናዎቹ መካከል ይገኙበታል። በተጨማሪም የስነ ልቦና ድጋፍ እና ምክር ህሙማንን እና ቤተሰቦቻቸው የበሽታውን ስሜታዊ ተፅእኖ እንዲቋቋሙ በመርዳት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በኢቦላ ጉዳዮች ላይ ውጤቱን ለማሻሻል ቀደም ብሎ ማወቅ እና ህክምናውን በፍጥነት መጀመር አስፈላጊ መሆናቸውን የድርጅቱ መረጃ አስገንዝቧል፡፡

የኢቮላ ቫይረስን  እንዴት መከላከል ይቻላል?

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ወይም ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተጠረጠሩ ሰዎች ጋር አካላዊ ንክኪ አለማድረግ፣የተጋለጡት ለዛየር የኢቦላ ዝርያ ከሆነ ክትባት መውሰድ፣ ወረርሽኙ በተነሳበት አካባቢ የሚኖሩ ከሆነ እጅን አዘውትሮ መታጠብ፣ሥጋን በአግባቡ አብስሎ መመገብ፣ በኢቦላ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን አለመንካት፣ ኢቦላ ከያዛቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ከተፈጠረ ወደ ሕክምና ተቋም ማምራት ይገባል፡፡

ጤና አዳም

የቫይረስ ትኩሳት ዓይነቶች

የቫይረስ ትኩሳት ዓይነቶች በተለያዩ ሁኔታዎች እንደ የመተላለፊያ ዘዴ፣የበሽታው ክብደት፣ የተጎዳው የሰውነት አካል፣ ወዘተ ይወሰናል፡፡

  • የመተንፈሻ የቫይረስ ትኩሳት- ይህ የቫይረስ ኢንፌክሽን እንደ ሳል፣ ጉንፋን፣ የጉሮሮ መቁሰል፣ ትኩሳት ወይም የሰውነት ህመም ካሉ ከጉንፋን መሰል ምልክቶች ጋር የተያያዘ ነው። ለምሳሌ በጋራ ጉንፋን፣ አዴኖቫይረስ፣ የመተንፈሻ አካላት ሲንሳይያል ቫይረስ ኢንፌክሽን፣ ከባድ አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት ቫይረስ፣ የኮቪድ-19 ቫይረስ እና የፓራ ኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ኢንፌክሽን ይገኙበታል።
  • የጨጓራና ትራክት የቫይረስ ትኩሳት- ይህ የቫይረስ ኢንፌክሽን ከጨጓራና ትራክት መዛባቶች ጋር ተያይዞ እንደ ተቅማጥ፣ የሆድ ህመም፣ ማስታወክ እና የመሳሰሉት ናቸው።
  • ውጫዊ የቫይረስ ትኩሳት- ይህ የቫይረስ ኢንፌክሽን ከቆዳ ሽፍታ እና ከቆዳ ፍንዳታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምሳሌዎች ኩፍኝ፣ ቺኩንጉኒያ፣ ፈንጣጣ፣ ወዘተ ያካትታሉ።
  • ሄሞራጂክ የቫይረስ ትኩሳት- ይህ የቫይረስ ኢንፌክሽን በደም ዝውውር ስርዓት ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምሳሌዎች ኢቦላ፣ ላሳ ትኩሳት፣ ቢጫ ወባ፣ ወዘተ
  • ኒውሮሎጂካል የቫይረስ ትኩሳት- ይህ የቫይረስ ኢንፌክሽን በነርቭ ሥርዓት ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ የእብድ ውሻ በሽታ፣ ፖሊዮ፣ የቫይረስ ኢንሴፈላላይትስ እና የቫይረስ ገትር በሽታ። አብዛኛዎቹ እነዚህ ምልክቶች  በመከላከል እና በህክምና አማራጮች ላይ የህክምና ባለሙያዎቻችንን በማማከር መታከም ይችላሉ።

ምንጭ- ዮሺዳሆስፒታል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት  9  ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here