የሰንደቁ ታሪክ

0
10

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከቀለማት ስብስብ ወይም ከተራ ጨርቅ በላይ የሕዝቦች ሉዓላዊነት፣ የነፃነት፣ የክብር እና የጽናት ሕያው ማኅተም ነው።  የሰንደቅ ዓላማን ዓለም አቀፋዊ አመጣጥ፣ በኢትዮጵያ ያለውን የዘመናት ጉዞ፣ በተለያዩ ነገሥታት የነበሩትን ዓይነቶች እና ቀለማቱ ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ያለውን ጥልቅ ትርጉም በዝርዝር እንመለከታለን።

የሰንደቅ ዓላማ አጠቃላይ አመጣጥ

“ሰንደቅ ዓላማ” የሚለው ስያሜ ከሁለት ቃላት የተመሠረተ ነው፤ “ሰንደቅ” ማለት በዘንግ ላይ የሚሰቀል ባለቀለም ጨርቅ ሲሆን “ዓላማ” ደግሞ መስቀያውን ወይም በውስጡ የያዘውን ዓርማ እና መርህ ያመለክታል። በቋንቋ ጥናት መሠረት “ሰንደቅ” የሚለው ቃል “ሳንጃክ” ከሚለው የቱርክኛ ቃል የመጣ ሲሆን “ባንዲራ” የሚለው ደግሞ “ባንዲየራ” ከተባለው የጣልያንኛ ቃል በመውረስ ከአድዋ ጦርነት በኋላ በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል።

በጥንታዊው ዓለም ሰንደቅ ዓላማዎች በዋናነት በጦርነት ወቅት መረጃ ለመለዋወጫ እና የወታደሮችን አሰላለፍ ለመምራት ያገለግሉ ነበር። በኋላ ግን የሀገር፣ የሕዝብ ማንነት እና የነፃነት መገለጫ ምልክቶች ሆነው ቀጥለዋል።

በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መቼ እና እንዴት ተጀመረ?

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ረጅም ዘመናትን ወደኋላ የሚቆጥር ነው። በታሪክ እና በሃይማኖታዊ ትውፊት መሠረት ኢትዮጵያውያን የሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን (አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ) ከኖኅ የቃል ኪዳን ቀስተ ደመና ጋር ያያይዙታል።

በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገሥታት በጦርነት እና በነገሥታት ጉዞ ወቅት በዘንግ ላይ የተሰቀሉ ደማቅ ሐርና የቅዱስ ጊዮርጊስ ምስል ያለባቸውን ዓርማዎች ይጠቀሙ ነበር። የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ከመንግሥት መለያነታቸው በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ በንዋየ ቅድሳት ደረጃ (ለምሳሌ በበዓላት ወቅት በታቦት ፊት በሚሄዱ የሐር ጨርቆችና ጥላዎች) ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።  የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ገና በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ አውሮፓውያን የጂኦግራፊ ሊቃውንት በሳሏቸው ካርታዎች ላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሪባን ወይም ጨርቅ በራሳቸው ላይ ያስሩ እንደነበር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “ኢትዮጵያዊያን፡- ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ያስረዳሉ።

በተለያዩ ነገሥታትና ሥርዓታት የነበሩ የሰንደቅ ዓላማ ዓይነቶች

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማቱ ላይ ብዙ ለውጥ ባያደርግም በውስጡ የሚቀመጡት ዓርማዎች ግን እንደየዘመኑ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ ተለዋውጠዋል።

  • የዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን፡ በዚህ ዘመን የነበረው ሰንደቅ ዓላማ ሦስቱን ቀለማት የያዘ ሆኖ በመካከሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ መስቀል ወይም ምስል ነበረው። ይህ ምልክት ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ሀገር ጠባቂነትን እና ሉዓላዊነትን የሚያመለክት ነበር።
  • የዐፄ ምኒልክ ሁለተኛ ዘመን : በዘመናዊ መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅምት 6 1897 እ.አ.አ የመጀመሪያው ይፋዊ ሰንደቅ ዓላማ ታወጀ። በወቅቱ ቀለማቱ በተለያዩ ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው ፌስታሎች (ፔናንት) ይወከሉ ነበረ፤ በቢጫው ቀለም ላይ የዐፄ ምኒልክ ስም መጀመሪያ ፊደል (“ም”) በግዕዝ ተጽፎበት ነበር ሲሉ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል “ዝክረ ነገር”በሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል።
  • የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን: ቀለማቱ አግድም ወጥ በሆነ አራት ማዕዘን ቅርጽ የተስተካከሉ ነበሩ፤ በመካከሉ “የይሁዳ አንበሳ” ዓርማ (በትረ መስቀል እና የሰንደቅ ዓላማ ሪባን የያዘ አንበሳ) ተቀመጠበት። ይህ ዓርማ ንጉሣዊውን የሰሎሞናዊ ሥርወ-መንግሥት እና የሉዓላዊነት ትስስርን የሚያሳይ ነበር። (እስከ 1906 ዓ.ም ድረስ ቀዩ ቀለም ከላይ፣ አረንጓዴው ከታች ነበረ፤ በኋላ ግን አረንጓዴው ከላይ፣ ቢጫው ከመሃል፣ ቀዩ ከታች እንዲሆን ተደርጓል)።
  • የደርግ ሥርዓት: ወታደራዊው ሥርዓት ሥልጣን ሲይዝ የይሁዳ አንበሳ ዓርማን በማንሳት መጀመሪያ ላይ ያለ ዓርማ ሰንደቅ ዓላማን ተጠቀመ። በኋላ ግን በ1979 ዓ.ም የኢሕዲሪ መንግሥት ሲመሠረት የጋሻ፣ የጦር መሣሪያ፣ የፀሐይና የኮግ (ማሽን) ምስል ያለበትን የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የሚያንጸባርቅ ዓርማ በመሃሉ አደረገ፤ ግን ይሄ የፓርቲ አርማ ብቻ ነበር።
  • የኢፌድሪ ሥርዓት: በጥር 1988 ዓ.ም በታወጀው አዋጅ መሠረት የሰንደቅ ዓላማው ቀለማት ምጥጥን 1፡2 ሆነ። በመካከሉ ክብ ሰማያዊ መደብና እኩል ርቀት ያላቸው የወርቅ መስመሮች የሠሩት ኮከብ (ብሔራዊ ዓርማ) ተቀመጠ።

የሰንደቅ ዓላማው ትርጉም ለኢትዮጵያውያን

ለኢትዮጵያውያን ሰንደቅ ዓላማ በደም የተጻፈ የማንነት ውል ነው። ቀለማቱ በሕግ እና በትውፊት የሚከተሉትን ትርጉሞች ይዘዋል፡

  1. አረንጓዴ: የሥራ፣ የልምላሜ፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የዕድገት ምልክት።
  2. ቢጫ: የተስፋ፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የደመቀ አበባ እና ፍሬ መገለጫ።
  3. ቀይ: ለሀገር ነፃነት፣ ለሉዓላዊነት እና ለእኩልነት ሲባል የፈሰሰ የጀግኖች አባቶች ደምና የመስዋዕትነት ምልክት።

በአሁኑ ሕገ መንግሥታዊ ዓርማ ላይ ያለው ሰማያዊ መደብ ሰላምን፤ እኩል መስመሮቹ የብሔር ብሔረሰቦች እና የሃይማኖቶች እኩልነትን፤ ኮከቡ ደግሞ በመፈቃቀድ የተመሠረተውን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ብሩህ ተስፋን ያመለክታል። በዓድዋ ጦርነት እና በተለያዩ ወራሪዎች ላይ የተገኘው ድል ሁሉ የተመዘገበው በዚህ ሰንደቅ ሥር በመሰብሰብ በመሆኑ ለዜጎች የአንድነት እና የኩራት ዓርማ ነው።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለፓን አፍሪካኒዝም ያለው ትርጉም

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከአንድ ሀገር መገለጫነት አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት፣ የጽናት እና የትግል ዓለም አቀፋዊ አርማ ነው።  ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ዘመን የአውሮፓ ወራሪዎችን (በተለይም ጣሊያንን በዓድዋ ጦርነት) ድል በማድረግ ነፃነቷን እና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ መኖሯ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ለነበሩት ወንድም የአፍሪካ ሕዝቦች ትልቅ የተስፋ ብርሃን ሆኖላቸዋል። በዚህም ምክንያት እንደ ዊሊያም ዱቦይስ  እና ማርከስ ጋርቬይ ያሉ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አባቶች የኢትዮጵያን የድል መንፈስ እና ቀለማት የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ምልክት አደረጉት።

በ1950ዎቹና 60ዎቹ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ ለአክብሮት እና ለነፃነት ተምሳሌትነት የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት በራሳቸው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ውስጥ አካተዋል። ዛሬ ላይ ከ20 በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት (ለምሳሌ ጋና፣ ካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ ማሊ፣ ቶጎ፣ ጃማይካ ወዘተ) እነዚህን “የፓን አፍሪካኒዝም ቀለማት” በተለያየ ቅርጽ ይጠቀሙባቸዋል። በተጨማሪም የራስ ተፈሪያውያን  እምነት እና ባህል ተከታዮች ሰንደቁን የጥቁር ሕዝቦች መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ነፃነት መግለጫ አድርገው ያከብሩታል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ትናንት የነፃነት ፋና ወጊ፣ ዛሬ የሉዓላዊነት እና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መግለጫ፣ ነገ ደግሞ የጋራ እድገት እና የከፍታ ራዕይ ማሳያ ነው። ይህ ሰንደቅ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የተከፈለው የጀግኖች አጥንት እና ደም እያንዳንዱ ትውልድ ሀገራዊ ኃላፊነቱን በታማኝነት እንዲወጣ የሚያሳስብ ሕያው የቃል ኪዳን ማኅተም ነው።

ሳምንቱ በታሪክ

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጉዞ

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሰሜኑ የጦር ግንባር ያደረጉት ጉዞ ጥቅምት 10 ቀን1928 ዓ.ም ተጀመረ፤ ይህም የፋሺስት ጣሊያንን ወረራ ለመመከት የተከናወነ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ በአዲስ አበባ ሆነው ከመምራት ይልቅ ራሳቸው ግንባር ድረስ በመሄድ የሠራዊቱን ወታደራዊ ሞራል ለመገንባት እና የጦር አዛዦችን ስትራቴጂ ለማስተባበር በመወሰን መጀመሪያ የጦር ማዘዣ መሥሪያ ቤታቸውን በደሴ ከተማ አደረጉ። ይህ ጉዞ የጣሊያን አውሮፕላኖች ዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለውን  መርዝ ጋዝ እና ቦምብ በየመንገዱ ይረጩ ስለነበር እጅግ አደገኛ እና በአብዛኛው በምሽት ብቻ የሚደረግ ነበር።

ሁኔታዎች ይበልጥ እየተበላሹ ሲሄዱ ንጉሠ ነገሥቱ የራሳቸውን የክብር ዘበኛ ጦር ይዘው ወደ ማይጨው ግንባር በመጓዝ የመጨረሻውን ታላቅ ውጊያ በግንባር ቀደምትነት መርተዋል። ይህ የጦር ግንባር ጉዞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተደረገ ታላቅ የጀግንነት ጥረት ቢሆንም በዘመናዊ የጦር መሣሪያ እና በጋዝ የታገዘው የጣሊያን ጦር ባሳየው የበላይነት ምክንያት የኢትዮጵያ ጦር በከፍተኛ ኪሳራ ለማፈግፈግ ተገዷል ሲል አዶልፍ ፓርላሳክ “የሐበሻ ጀብዱ” በሚለው መጽሐፉ አትቷል።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here