“ሚዲያ የሕዝብ አዕምሮን ለመቀየር ታላቅ ኀይል አለው።” አፓርታይድን በይቅርታ የገረሰሱት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ አባባል ነው። በተመሳሳይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጄፈርሰን “መንግሥት ያለ ጋዜጣ ከሚኖር፣ ጋዜጣ ያለ መንግሥት ቢኖር እመርጣለሁ” በሚል ንግግራቸው ይታወቃሉ። ይህም ሚዲያ በማስተማር፣ በማሳወቅ፣ በማዝናናት…ያለውን ዘርፈ ብዙ ሚና ያሳያል። በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውል አይተኬ ሚና እንደሚጫወትም ያመላክታል። የዚህ ሁሉ መሠረታዊው ምክንያት ደግሞ ተደራሽነታቸው ለብዙኃኑ በመሆኑ ነው።
በሌላ በኩል ሚዲያዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋሉና በትክክል ካልተመሩ አፍራሽነታቸውም የዚያኑ ያክል ከፍተኛ ነው። በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ አፍራሽ መረጃዎች ደግሞ የዚህ ማሳያዎች ናቸው።
ጣሊያናዊው ፈላስፋ ኡምቤርቶ ኤኮ “ማሕበራዊ ሚዲያ በፊት የማይታወቁ ድምፆችን አበርክቷል፣ ነገር ግን አሁን ማንኛውም ሰው እንደ ባለሙያ እንዲናገር ዕድልን ሰጥቶ ውድቀት አመጣ።” ሲል ነው የሚናገረው። በመሆኑም በኃላፊነት ስሜት በመሥራት፣ ለሙያዊ መርህ እና ሥነ ምግባር በመገዛት እንዲሁም ትክክለኛ የጋዜጠኝነት መገለጫዎችን በመተግበር ሕዝብን ከጥፋት መታደግ እንደሚገባ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚመክሩት።
ከዚህ ጋር በተገናኘ ከሰሞኑ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከዲ ኤስ ደብሊው ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ምክክር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በዚህም ማሕበራዊ አንቂዎችን ጨምሮ ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹ እንዳሉት ሰላምን በጽኑ ለመገንባት ዕውነትን፣ ሰላምን እና ፍትሕን ማስተማር ብዙኃን መገናኛዎች አይተኬ ሚና አላቸው። ይህን ሚናቸውንም በግንባር ቀደምነት መፈጸም ይገባቸዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ኘሬዝዳንት አማረ ደጉ ሀሠተኛ መረጃዎች ሀገርን የሚያናጉ እና ለግጭት የሚዳርጉ መሆናቸውን አንስቷል። በመሆኑም ለእውነት ዘብ ለመቆም ትክክለኛ የመረጃ ምንጮችን መጠቀም እንደሚገባ ነው የጠቆመው። ወጣቶች ከስሜት በፀዳ መንገድ የሰላም አምባሳደር መሆን እንደሚገባቸውም ተናግሯዋል።
ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ የአሚኮ ጋዜጠኛ ትርሲት አሰፋ ብዙኃን መገናኛዎች ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ በማድረግ የሰላም ዘማሪዎች መሆን እንደሚገባቸው ነው የገለጸችው። ይህ ሲሆን ደግሞ በመንግሥት እና በሕዝብ መካካል የድልድይነት ሚናን ለመወጣት ያስችላሉ። በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሕዝብን ለአደጋ የሚጥሉ መረጃዎችን ከማሰራጨት መቆጠብ እንደሚገባቸውም ጠቁማለች። ባለሙያዎችም “ገለልተኛ በመሆን ለሰላም እና ለልማት ግንባታ መሥራት ይገባቸዋል” በማለት ጠቁማለች።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም አረጋ እንደተናገሩት የዴሞክራሲ ሥርዓትን በማጽናት የሀገርን ሰላም ለማረጋጋት ብዙኃን መገናኛዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው። ይሁን እንጂ በአግባቡ ካልተመሩ አደጋው የከፋ ነው። ምክክሩም የተዘጋጀው በዘርፉ የተሰማሩት ሁሉ አደጋውን በመገንዘብ ለሰላም እና ዴሞክራሲ ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ይበልጥ ግንዛቤን ለማሳደግ ነው።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ኢሳያስ ገብረሚካኤል ብዙኃን መገናኛዎች እውነትን፣ ሰላምን እና ፍትሕን በአግባቡ ከሰበኩ ሰላምን ማጽናት እንደሚቻል ጠቁመዋል። ባለሙያዎችም ይህን መንገድ ተከትለው ከሠሩ እንደ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር መፍታት እንደሚቻልም ነው ያነሱት።
አቶ ኢሳያስ እንዳሉት ኃላፊነት በጎደላቸው ብዙኃን መገናኛዎች የሚተላለፉ የተዛቡ መልዕክቶች እና የሀሰት ትርክቶች ወጣቶችን ወደ አልተፈለገ ተግባር እንዲገቡ እያደረገ ነው። ችግሩን በአግባቡ መረዳት እንደሚገባ በማንሳት “ይህንን የሚቀለብስ ኃላፊነት የሚሰማው ብዙኃን መገናኛ ያስፈልጋል” በማለትም አስገንዝበዋል።
ወጣቶች በግጭት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስባቸው ያነሱት ደግሞ የዲ ኤስ ደብሊው ኢትዮጰያ ካንትሪ ዳይሬክተር ፈየራ አሰፋ ናቸው። ድርጅቱ ታዲያ ችግሩን በመገንዘብ “ወጣቶችን የሰላም አሸናፊዎች ለማድረግ እየሠራ ነው” ብለዋል።
ለስኬቱ የብዙኃን መገናኛዎች ሚና አይተኬ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ወጣቶችን የልማት ባለቤት እና የሰላም አምባሳር ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
መረጃ
የመገናኛ ብዙሀን ዋና ዋና ተግባራት ዝርዝር፡-
- መረጃ ማድረስ (Information): ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና የተሟላ መረጃ ለኅብረተሰቡ ማድረስ።
- ማስተማርና ማወቅ (Education): በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ መፍጠር።
- ማዝናናት (Entertainment): የሙዚቃ፣ የፊልም፣ የስፖርት እና ሌሎች የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በማቅረብ የመዝናኛ አገልግሎት መስጠት።
- የህዝብ አስተያየት መድረክ መሆን (Public Forum): የኅዝብ ድምፅ የሚሰማበት፣ የተለያየ ሀሳብ የሚንሸራሸርበት እና የውይይት መድረክ መሆን።
- የመንግሥት ሥራ ተቆጣጣሪ (Watchdog): የመንግሥትን ሥራ በመከታተል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን መጋለጥ።
- ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ: የሀገርን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የማህበረሰቡን ሚና ማጎልበት።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር በኲር የሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


