ጥበብ ሁለት ናት። የምትዳኘውም በሁለት መንገድ ነው። እሷ ሳይንስም ስሜትም ናት። ጭፍን ብላ በስሜት አትመራም። እውር እንዳትሆን ሳይንስን ትመረኮዛለች። ደግሞ ሕግ ላይ ሙጥኝ ብላ ለዛ እንዳታጣ ሜትን ያዥኝ ትላለች።
አሁን ጥበብ ስሜት በሌለው ማሽን ተሠርታ ስሜት ላለው ሰው እየቀረበች ነው። አንድ ማሽን ፍቅር ሳያጣጥም የፍቅር ግጥም ሲጽፍ፤ ልቡ ሳይሰበር የኀዘን ዜማ ሲያቀናብር እና የእምነት ልምምድ ሳይኖረው የቤተክርስቲያን ስዕል ሲስል አስቡት::
የሰው ልጅ የልብ ትርታ፣ የነፍስ ጭንቀት፣ የህይወት ውጣ ውረድ፣ የህመም ስሜት እና የደስታ እንባ ሳይኖረው ልብን ሰርስሮ የሚገባ ጥበብ የሚያመነጭ ቴክኖሎጂ ዛሬ ላይ ተፈጥሯል::
አሁን ኤ አይ ሙዚቃ ይሠራል:: ስዕል ይስላል:: ፖስተር ይሠራል:: ድርሰት ይጽፋል:: ግጥም ይጽፋል:: ሙዚቃ ያቀናብራል:: ፊልም ይሠራል:: በኪነ ጥበብ ዘርፍ ሁሉንም ተግባራት ያከናውናል:: ይህ አዲስ ክስተት ፈጣሪውን ያስደነገጠ ፍጡር ሆኖ በዓለማችን ላይ ብቅ ብሏል::
የሰው ልጅ ከዘመን ዘመን ሲያሸጋግረው የመጣውን ክቡር የጥበብ ማንነት ማሽኖች በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ተቆጣጥረውታል:: ይህ አስደናቂ እና አስፈሪ ክስተት የሰው ልጅን ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረው ይገኛል::
ቴክኖሎጂ መጀመሪያ ላይ የጉልበት ሥራዎችን ለመተካት የተፈጠረ ነበር:: ትናንት አድካሚ የፋብሪካ ሥራዎችን፣ የሂሳብ ስሌቶችን፣ የግብርና ተግባራትን፣ የመረጃ አያያዞችን እና መሰል የጉልበት ልፋቶችን ሲያቀል የነበረው ማሽን ዛሬ ድንበር ተሻግሯል:: ኮምፒውተር ከማስላት ወደ ማሰብ አልፎም ወደ መፍጠር ተሸጋግሯል::
በጥንት ዘመን የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሰው ልጅ እጅግ የረቀቀ የማሰብ ችሎታ መገለጫዎች ተደርገው ይወሰዱ ነበር:: አንድ ሰዓሊ ስዕል ለመሳል ዓመታት ይፈጅበት ነበር:: አንድ ደራሲ መጽሀፍ ለመጻፍ የህይወት ዘመን ልምዱን ያፈስበት ነበር:: ዛሬ ግን ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሺህ ዓመታት የሰው ልጅ የጥበብ ጉዞን አዋሕዶ በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ እያቀረበው ይገኛል::
ሰው ሰራሽ አስተውሎት አሁን ሁሉም የፈጠራ ቦታ አለ:: በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ የሞቱ ተዋንያንን በድምጽ እና በምስል ህያው አድርጎ ማቅረብ ችሏል:: በሙዚቃው ዓለም የማንንም ድምጻዊ ድምጽ አስመስሎ አዳዲስ ዘፈኖችን ያወጣል:: በስነ ጽሁፍ ረገድ ከመጣጥፍ እስከ ረጅም ልቦለድ ድረስ ያለምንም ስህተት ይጽፋል::
ዋነኛው ስጋት የሰው ልጅ የጥበብ ማንነት መጥፋት፣ የፈጠራ ክህሎት መሞት፣ የእውነተኛ ስሜት መጥፋት፣ የባህል መበረዝ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ነው:: ጥበበኛው የፈጠራ ሥራው ያለ አግባብ በማሽኖች እየተወሰደ በመሆኑ ክፉኛ ተቆጥቷል::
የሰው ልጅ ጥበብን የሚሠራው ከውስጥ በሚመነጭ ስሜት ሲሆን ማሽን ግን የሚያከናውነው በሂሳባዊ ስሌት ነው:: ይህ ሁኔታ የጥበብን እውነተኛ ትርጉም ያጠፋል የሚል ጠንካራ ስጋት አለ::
መላው የጥበብ ቤተሰብ በከፍተኛ የህልውና አደጋ ውስጥ እንዳለ እንረዳለን:: ጥበበኛው ማሽን የሰውን ነፍስ የሌለው ባዶ ምስል እየፈጠረ የጥበብን ክብር እያረከሰ ነው በማለት ይሞግታል:: የኪነ ጥበብ ማህበራት ከፍተኛ ተቃውሞ እና አድማ እያደረጉ መሆኑን እናያለን::
የደራሲያን ማህበራት፣ የፊልም አዘጋጆች ማህበራት፣ የሰዓሊያን ማህበራት፣ የሙዚቀኞች ማህበራት እና የተለያዩ የጥበብ ተቋማት ኤ አይ የሰዎችን ሥራ ያለ ባለቤቶቹ ፍቃድ ለስልጠና እየተጠቀመ ነው በማለት ይከሳሉ:: የሆሊውድ የፊልም ጸሀፊዎች እና ተዋንያን ሥራችንን በማሽን ልንነጠቅ አንችልም በማለት ያደረጉት አድማ ዓለምን ያነጋገረ ነበር:: የቅጂ መብት ጥሰት፣ የፈጠራ ሌብነት፣ የማንነት ስርቆት እና የድምጽ ማስመሰል ክሶች በፍርድ ቤቶች ሞልተዋል::
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ጉዳይ ላይ የየራሳቸው ምልከታ አላቸው:: የዘገባ አቅራቢዎች እና ሚዲያዎች ቴክኖሎጂው እያመጣ ያለውን ፈጣን ለውጥ በግርምት እና በስጋት እየዘገቡት ይገኛሉ:: የመጽሀፍት ደራሲያን ስራዎቻቸው በማሽን ተሰርቀው አዳዲስ መጽሀፍት እየተጻፉባቸው በመሆኑ የሕግ ከለላ ይፈልጋሉ:: ተራው የሰው ልጅ በበኩሉ ሥራዬን አጣለሁ ወይ የሚል ፍርሃት አድሮበታል:: የጥናት እና ምርምር ባለሙያዎች በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጥበብ እና የቢሮ ሥራ በማሽን እንደሚተካ በቁጥር አስደግፈው ያስጠነቅቃሉ::
የሥራ ፈጣሪዎች ግን ይህንን እንደ ትልቅ የንግድ ዕድል አይተውታል:: አዳዲስ የኤ አይ ኩባንያዎችን በመክፈት ቢሊዮን ዶላሮችን እያተረፉ ነው:: የቢሊየነሮችን ሐሳብ ስናይ እጅግ የተራራቀ ሆኖ እናገኘዋለን:: የኦፕን ኤ አይ መስራች የሆነው ሳም አልትማን፣ የማክሮሶፍቱ ቢል ጌትስ እና የማርክ ዙከርበርግ ሀሳብ ቴክኖሎጂው የሰውን ልጅ የፈጠራ አድማስ እንደሚያሰፋው፣ የጥበብን ወጪ እንደሚቀንሰው፣ አዳዲስ ሀሳቦችን በማመንጨት የሰው ልጅን አቅም እንደሚያጎለብተው እና የተሻለ ዓለም እንደሚፈጥር ይገልጻሉ:: በሌላ በኩል እንደ ኢሎን ማስክ እና ጂኦፍሪ ሂንተን ያሉ የዘርፉ አባቶች ቁጥጥር ያልተደረገበት ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰውን ልጅ ህልውና ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ ይችላል በማለት በጥብቅ ያስጠነቅቃሉ::
ወደ ፊት ምን ሊከሰት ይችላል ለሚለው ጥያቄ ምላሹ እጅግ ውስብስብ ነው:: ወደ ፊት ኤ አይ ከዛሬው በበለጠ ተራቆ የሰውን ልጅ ሙሉ በሙሉ በሚመስል መልኩ ድንቅ ፊልሞችን ሊሠራ፣ ተውኔቶችን ሊያዘጋጅ፣ መጽሀፍትን ሊያሳትም፣ የዜና አቅራቢዎችን ሊተካ፣ የፖለቲካ ዘመቻዎችን ሊመራ እና የሰዎችን የዕለት ተዕለት ውሳኔዎች ሊቆጣጠር ይችላል::
የሰው ልጅ እና የማሽን ድንበር እስከማይታወቅ ድረስ ሊደበዝዝ ይችላል:: መፍትሄው ቴክኖሎጂውን ማቆም ሳይሆን አብሮ መኖርን መማር ነው:: ቴክኖሎጂውን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም:: መውጫ መንገዱ ማሽኑን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ኃይለኛ የጥበብ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ነው:: መንግሥታት የጥበብ ሰዎችን መብት የሚያስጠብቁ፣ የፈጠራ ሥራዎች በማሽን ሲወሰዱ የካሳ ክፍያ የሚፈጸምባቸውን፣ የኤ አይ ኩባንያዎች ካገኙት ትርፍ ለዋናው የጥበብ ባለቤት ግብር የሚከፍሉበትን፣ የቅጂ መብትን የሚያከብሩ፣ የሰውን ልጅ ደህንነት የሚያስቀድሙ እና የፈጠራ ባለቤትነትን የሚጠብቁ አዳዲስ ሕጎችን ማውጣት ይጠበቅባቸዋል:: ትምህርት ቤቶችም አዲሱን ትውልድ ከኤ አይ ጋር አብሮ መስራት እንዲችል፣ ጥያቄ መጠየቅን እንዲያውቅ፣ ሰዋዊ እሴቶችን እንዲያዳብር እና የፈጠራ አድማሱን እንዲያሰፋ ማሰልጠን ይኖርባቸዋል::
ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የሰው ልጅ አብረው የሚሠሩበት አዲስ የጥበብ ዘመን መፈጠር አለበት። ማሽን የቱንም ያህል ቢራቀቅ የሰው ልጅ የሚሰጠውን ጥሬ መረጃ ተጠቅሞ ነው የሚሠራው:: ስለዚህ የሰው ልጅ ከመቼውም ጊዜ በላይ የራሱን ልዩ ሰዋዊ ማንነት ማጎልበት አለበት:: ማሽኖች ድካም የሚጠይቁ የጥበብ ስራዎችን ሲሰሩ የሰው ልጅ ደግሞ የጥበቡን ነፍስ፣ መንፈስ፣ ስነ ምግባር እና የህይወት ፍልስፍና ይዘውራል::
ቴክኖሎጂው እንደ አንድ ብሩሽ፣ ካሜራ፣ ፒያኖ፣ የፊደላት ገበታ፣ ቀለም እና ሸራ ሆኖ ማገልገል አለበት:: ማሽኑ የሰውን ልጅ አእምሮ ሊተካ ይችላል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ ልብ ሊተካ አይችልም:: የችግሩ መውጫ መንገድ የሰውን ልጅ ከማሽን ጋር ማወዳደር ሳይሆን የሰው ልጅን ልዩ የሚያደርጉትን ስሜቶች ማክበር ነው::
የቱንም ያህል ቴክኖሎጂ ቢራቀቅ የሰውን ልጅ ሙሉ በሙሉ ሊተካው አይችልም:: ቴክኖሎጂው የቴክኒክ ድካምን ሲያቀል የሰው ልጅ ደግሞ ለማሽኑ ስሜትን፣ እሴትን፣ ፍቅርን፣ ህመምን እና ነፍስን መዝራት ይኖርበታል:: ማሽኑ እጅግ የረቀቀ ኮድ፣ አልጎሪዝም፣ መረጃ፣ የሂሳብ ስሌት፣ ብሩሽ፣ ቀለም፣ ሸራ፣ ካሜራ፣ ዜማ እና እውቀት ሊኖረው ይችላል::
ስለዚህ ኤ አይ የቱንም ያህል ቢራቀቅ የሰውን ልጅ እውነተኛ የጥበብ ዙፋን አይነቀንቀውም:: ማሽን ጥበብን ይኮርጃል እንጂ አይኖረውም:: ይልቁንም የሰው ልጅ ጥልቅ ስሜቱን የሚያጎላበት አዲስ መሣሪያ ሆኖ የጥበብን ማማ ወደ ሰማይ ከፍ ያደርገዋል:: ጥበብ ህይወት ነው:: ህይወት ደግሞ በኮድ አይጻፍም::
ማረፊያ
የእግዜር ቅኔ
እግዜር ቅኔ ሲቀኝ
በሰው ልጅ ፍጥረት፤
ብዙ ሰምተህ
ጥቂት አውራ ለማለት፤
አፍን አንድ አረገው
ጆሮን ግን ሁለት፡፡
ናትናኤል ግርማቸው፡፡
(አቢብ በዓለሜ)
በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


