ነገርም ይላመጣል!

0
110

አሁን ይህን ጽሑፍ እያነበባችሁ  የሆነ ቦታ የሆነ ሰው ስለ እናንተ እያወራ ሊሆን ይችላል:: ምናልባት አብሯችሁ የሚሠራው የቅርብ ባልደረባችሁ አሊያም ትናንትና ረፋድ አብራችሁት ቡና የጠጣችሁት ጓደኛችሁ ሊሆን ይችላል::

አስቡት በሌላ ቦታ ሆኖ እናንተ ማንም እንዲያውቅባችሁ የማትፈልጉትን ሚስጥር ወይም ጭራሹኑ ያልሠራችሁትን ስህተት አጋኖ ለሌላ ሰው በሹክሹክታ እያካፈለ ቢሆንስ? ወዲያውኑ ልባችሁ ይመታል፤ ደማችሁ ይፈላል፤ በድንገት የክህደት እና የመጎዳት ስሜት ውስጥ ትዘፈቃላችሁ::

ይህ ነው የሀሜት አስፈሪው ገጽታ:: ሀሜት ምንም ዓይነት አካላዊ መሣሪያ ሳያስፈልግ ሰዎችን በርቀት ማቁሰል የሚቻልበት አደገኛ አስማት ነው:: አንድም ጠብታ ደም ሳያፈሱ የአንድን ሰው ሰብዕና፣ ስም እና ሞራል መግደል የሚቻልበት ድምጽ አልባ ጦርነት ነው::

ሀሜት ከማህበራዊ ትስስር መፍጠሪያነት አልፎ  ዛሬ ላይ ትዳርን የሚያፈርስ፣ የስራ ቦታን ወደ ጦር አውድማ የሚቀይር እና ማህበረሰብን የሚበላ ካንሰር ሆኗል:: ነገር ግን ይህን የጥፋት ሰንሰለት መበጠስ እንችላለን::

ሰዎች ለምን ያማሉ? ይህ አጥፊ ባህሪ ከየት መጣ? ብለን ስንጠይቅ፣ ሳይንስ እና ታሪክ የሚሰጡን መልስ አስገራሚ ነው::

በታዋቂው የታሪክ እና የሳይንስ ምሁር ዩቫል ኖህ ሀራሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በተነበበው “Sapiens: A Brief History of Humankind” (ሳፒየንስ፡ የሰው ልጅ ዝርዝር ታሪክ) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ “የሀሜት ንድፈ-ሀሳብ” (Gossip Theory) የሚል አስደናቂ ሀሳብ ያነሳል::

ሀራሪ እንደሚያስረዳው ከ70 ሺህ ዓመታት በፊት የሰው ልጅ ቋንቋ የዳበረው ዛፍ እና አውሬን ለመጠቆም ብቻ አልነበረም:: ይልቁንም የሰው ልጅ በቡድን ሆኖ ለመኖር ሲሞክር ማን ማንን እንደሚጠላ፣ ማን ታማኝ እንደሆነ፣ ማን ሸፍጠኛ እንደሆነ ለማወቅ (በሌላ አነጋገር ለማማት) ቋንቋን ተጠቀመበት:: ያኔ በጥንት ዘመን ሀሜት የህልውና (Survival) ጉዳይ ነበር፤ ጠቃሚ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ይረዳ ነበር::

ነገር ግን ዘመናት ተቀየሩ:: ዛሬ አንበሳ እና ነብር አያባርረንም፤ ነገር ግን ያ በጥንት ዘመን ለመትረፍ የረዳን የሀሜት ባህሪ  ዛሬ እርስ በርሳችን ልንጠፋፋበት ወደምንችልበት የጅምላ ጥፋት መሣሪያነት ተቀይሯል:: የጥንቱ ዋሻ ዛሬ በዘመናዊ ቢሮ ተተክቷል፤ የህልውናው ትግል ደግሞ በስራ ቦታ ወደሚደረግ የእርስ በርስ መናቆር አድጓል::

የአሜሪካ ስነ-ልቦና ማህበር  እና የተለያዩ ተግባራዊ የስነ-ልቦና ጆርናሎች ባወጧቸው ጥናቶች መሰረት ሀሜት በነገሰበት የሥራ አካባቢ የሠራተኞች ምርታማነት እስከ 50% ይቀንሳል:: ሠራተኞች ስራቸውን ከመስራት ይልቅ “ማን ምን አለኝ?” በሚል ፍርሃት እና ውጥረት ውስጥ ይወድቃሉ:: ሀሜት በሚታማው ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ድርጅቱ ላይ የስነ-ልቦና ቀውስ፣ ጭንቀት  እና ከባድ የመንፈስ ድባቴ ያመጣል::

ዶን ሚጌል ሩዊዝ የተባሉት ደራሲ “The Four Agreements” (አራቱ ስምምነቶች) በተሰኘው እና በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ባተረፈው መጽሐፋቸው ላይ የሰውን ልጅ የቃላት አጠቃቀም በሚያስገርም ጥልቀት ይተነትናሉ:: ደራሲው በመጀመሪያው እና ትልቁ ስምምነት ላይ “በቃልህ ፍጹም ሁን” ይላሉ::

ሩዊዝ በመጽሐፋቸው ሀሜትን በግልጽ “ጥቁር አስማት” (Black Magic) ብለው ይጠሩታል:: ለምን? ምክንያቱም ቃላት እንዲሁ አየር ላይ የሚረጩ ድምጾች አይደሉም፤ ኃይል አላቸው::

አንድ ሰው ስለሌላው ሰው የሌለበትን ወይም መጥፎ ገጽታውን አጋኖ ለሌላ ሲነግር  በዚያ ሰው ህይወት ላይ የጥፋት መርዝ እየረጨ ነው:: እንደ ኮምፒውተር ቫይረስ ነው:: የሚያማው የሀሜት ቫይረሱን ወደ አድማጩ አእምሮ ያስገባል፤ አድማጩ ደግሞ ስለሚያማው ሰው የነበረው መልካም አመለካከት በቅጽበት ይበከላል::

ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ይህ ጥቁር አስማት የሚጎዳው የሚታማውን ብቻ አለመሆኑ ነው:: ሀሜተኛው በራሱ ልብ ውስጥ ምቀኝነትን እና ጥላቻን ሲያሳድግ አድማጩ ደግሞ የሰው ልጅን የማመን አቅሙን ያጣል:: ሀሜት ሦስቱንም (የሚያማውን፣ አድማጩን እና የሚታማውን) አብሮ የሚያጠፋ መርዝ ነው::

ሁላችንም የዚህ ወረርሽኝ ሰለባ ከሆንን እንዴት ነው ከዚህ የጥፋት አዙሪት የምንወጣው? መቼስ የሰዎችን አፍ በቁልፍ መዝጋት አንችልም::

መልሱ ያለው ከሌሎች ሰዎች አንደበት ላይ ሳይሆን ከራሳችን ጆሮ እና ምላስ ላይ ነው:: ማህበረሰባዊ ለውጥ የሚጀምረው ከግለሰብ ውሳኔ ነው:: ይህን ድብቅ ጦርነት ለማስቆም ሁላችንም በግላችን ልንተገብራቸው የምንችላቸው ሦስት ወርቃማ የመውጫ መንገዶችን እንመልከት::

መፍትሄ 1፡ የሶቅራጠስ ሦስቱ ማጣሪያዎች

ከ2400 ዓመታት በፊት በግሪክ ይኖር የነበረው ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጠስ ዛሬም ድረስ የሚሠራ አንድ ድንቅ ጥበብ ትቶልን አልፏል:: አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ ሶቅራጠስ እየሮጠ መጣና “ሶቅራጠስ! ስለ ወዳጅህ አሁን የሰማሁትን ልንገርህ?” አለው::

ሶቅራጠስም እጁን አነሳና “ቆይ አንዴ… ይህን ነገር ከመንገርህ በፊት በሦስት ማጣሪያዎች ውስጥ እንድናሳልፈው እፈልጋለሁ” አለው::

አንደኛው የእውነት ማጣሪያ ነው:: “ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ ያሰብከው ነገር መቶ በመቶ እውነት መሆኑን በእርግጠኝነት ታውቃለህ?” ሲል ጠየቀው:: ሰውየውም “ኧረ እርግጠኛ አይደለሁም እኔም ከሰው ነው የሰማሁት” አለ::

ሁለተኛው የበጎነት ማጣሪያ ነው::  “እሺ ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ ያሰብከው ነገር ጥሩ እና በጎ ነገር ነው?”  አለው:: ሰውየውም አፍሮ “አይ አይደለም… እንዲያውም መጥፎ ነገር ነው” አለ::

ሦስተኛው የጠቃሚነት ማጣሪያ  ነው:: ሶቅራጠስ በመጨረሻ “እሺ ይህ የምትነግረኝ ነገር ለእኔ የሚጠቅመኝ፣ ህይወቴን የሚያሻሽል ነገር ነው?” ሲል ጠየቀ:: ሰውየውም “አይ አይጠቅምህም” ብሎ መለሰ::

ሶቅራጠስም ፈገግ ብሎ “እንግዲያው የምትነግረኝ ነገር ‘እውነት’ ካልሆነ፣ ‘በጎ’ ከሌለው እና ለእኔ ‘የሚጠቅም’ ካልሆነ… ለምን ትነግረኛለህ? ለምንስ እሰማሃለሁ?” ብሎ አሰናበተው::

ይህንን የሶቅራጠስ ማጣሪያ በህይወታችን ብንተገብረው የሀሜትን በር 80 በመቶ መዝጋት እንችላለን:: ወሬ ይዘውልን ለሚመጡ ሰዎች እነዚህን ሦስት ጥያቄዎች ማንሳት የሀሜት ቫይረስን የሚያጠፋ ጸረ-ቫይረስ ነው::

መፍትሄ 2፡ ርዕስ መቀየር

ሰዎች ሊያሙን ሲመጡ ፊት ለፊት መጋጨት ላንፈልግ እንችላለን:: በዚህ ጊዜ “የማስቀየስ ስልት” መጠቀም እንችላለን:: አንድ ሰው ስለ ሌላ ሠራተኛ ወይም ጓደኛ መጥፎ ሊያወራ ሲጀምር በዘዴ የዚያን ሰው ጠንካራ እና ጥሩ ጎን በማንሳት ወሬውን ማክሸፍ ይቻላል:: ለምሳሌ፡ “አዎ እሱ በዚያ ጉዳይ ላይ ትንሽ ደከም ሊል ይችላል… ግን ባለፈው ያቀረበው ሪፖርት እኮ በጣም ድንቅ ነበር አይደል?” በማለት አቅጣጫውን ማስቀየር ይቻላል:: ሀሜተኞች አብሯቸው የሚያማ እና የሚያጨበጭብላቸው ካላገኙ ወዲያውኑ ወሬውን ያቆማሉ::

መፍትሄ 3፡ ራስን መመርመር እና ከፍታን መፈለግ

ብዙውን ጊዜ ስለ ሌሎች ሰዎች ክፋት እና ውድቀት ማውራት የሚያስደስተን የራሳችንን ክፍተት እና የህይወት ውድቀት ለመሸፈን ስንሞክር ነው:: በራሱ የሚተማመን እና ራዕይ ያለው ሰው የሌላውን ሰው ስህተት በመለቃቀም ጊዜውን አያጠፋም::

የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ኤሌኖር ሩዝቬልት  የተናገሩት የማይሞት አባባል አለ:: “ታላላቅ አእምሮዎች ስለ ሀሳቦች ያወራሉ፣ መካከለኛ አእምሮዎች ስለ ክስተቶች ያወራሉ፣ ትናንሽ አእምሮዎች ደግሞ ስለ ሰዎች  ያወራሉ”  ብለው ነበር::

እኛ የትኞቹ ነን? ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን ስለ ሰው በማውራት ከምናጠፋ እንዴት አዳዲስ ሀሳቦችን እናመንጭ? ህይወታችንን እንዴት እንቀይር? በሚለው ላይ ብንወያይ ማህበረሰባችን የት በደረሰ ነበር!

ሀሜት ልክ እንደ ሰደድ እሳት ነው:: ጫካውን፣ ንብረቱን፣ አልፎም ህይወትን ሊያቃጥል እና አመድ ሊያደርግ ይችላል:: ነገር ግን እሳቱ ከእኛ አልፎ ወደ ሌላው እንዳይዛመት መወሰን የምንችለው እኛው ነን:: እኛ የእሳት መከላከያ ግንብ መሆን እንችላለን::

በሚቀጥለው ጊዜ አንድ ሰው ወደ እናንተ ጠጋ ብሎ ድምጹን ዝቅ አድርጎ “ስማ/ስሚ… የሆነ ነገር ልንገርህ…” ሲላችሁ በዚያች ቅጽበት ትልቅ ምርጫ ፊት ትቆማላችሁ::

የጥፋት፣ የስም ማጥፋት እና የጥቁር አስማቱ አካል ትሆናላችሁ? ወይስ የሶቅራጠስን ማጣሪያ ተጠቅማችሁ እሳቱን በማጥፋት የሰላም ምንጭ ትሆናላችሁ?

ቃላቶቻችንን እንጠብቅ፤ ጆሮዎቻችንን እናጥራ:: ዛሬ በሰው ላይ የምንወረውረው መርዛማ ቃል ነገ የራሳችንን የማንነት ቤት የምንገነባበት ጡብ ነውና::

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here