የመካከለኛዉ ምሥራቅ ዥዋዥዌ

0
116

ከሁለት ወር በፊት ነበር በአሜሪካ እና እስራኤል ጥምረት በኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት የተጀመረው። በአጸፋው ደግሞ ኢራን የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቅሞችን ጨምሮ በባሕረ ሰላጤው ሃገራት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰንዝራለች። ወትሮውንም ግጭት ርቆት የማያውቀው አካባቢው የዓለምን ፖለቲካ የሚዘውሩት ኃያላን ያላቸው ፍላጎት አካባቢያዊ ሰላም እንዲርቀው ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ስለመሆኑ አፍሪካ ኒውስ አስነብቧል።

ዘገባው እንዳመላከተው በቀጣናው በኢራን የሚደገፉ ወታደራዊ ኃይሎችም ተበራክተዋል፤ የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሃውቲ፣ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እና የፍልስጤሙ ሃማስ ተጠቃሽ ናቸው:: የእነዚህ ወታደራዊ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጥቃት ደግሞ በተለይ እስራኤል ረፍት እንድታጣ አድርጓታል:: በመሆኑም ቀጣናው ከግጭት እንዳይወጣ አድርጎታል:: በባላንጣነት የሚተያዩት እስራኤል እና ኢራን በእነዚህ ወታደራዊ ኃይሎች ምክንያት ደግሞ ቅራኔያቸው ወደ ጠላትነት ተሸጋግሯል::

በሌላ በኩል ኢራን ዩራኒየምን በገፍ ማበልጸጓ ከእስራኤል ባለፈ በአሜሪካ በኩልም በስጋት እንድትታይ ማድረጉን ዘገባው አስታውሷል፤ በዚህም ምክንያት ለዓመታት በቃላት ጦርነት ውስጥ ነበር የቆዩት::

ከሁለት ወራት በፊት ግን የቃላት ጦርነቱ ወደ ለየለት ጦርነት ተሸጋግሮ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፤ በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የንግድ መርከቦች የሚተላለፉበት የሆርሙዝ ሰርጥ እንዲዘጋም ምክንያት ሆኗል::

ዓለማችን ብዙ ነገሯ በነዳጅ ላይ ጥገኛ ሆናለች፤ የሚበዛው የነዳጅ ፍላጎት የሚሞላው ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሃገሮች ነው። እነዚህ የባሕረ ሰላጤው ሃገራት ታዲያ በቀን በሚሊዮኖች የሚቆጠር በርሜል ነዳጅን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ፈርጠም ያለ ገንዘብ ያገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ለዘመናት በቃላት ጦርነት የቀጠለው የአሜሪካ እና ኢራን ፍጥጫ ወደለየለት ጦርነት ተሸጋግሮ ከፍተኛ ውድመትን አስከትሏል። ተጽዕኖው ደግሞ የዓለምን ዳርቻ አካልሏል።

ለአብነትም የዓለማችን 20 በመቶ ያህሉ የነዳጅ ግብይት የሚካሄድበት የሆርሙዝ ሰርጥ በመዘጋቱ የዓለም ምጣኔ ሀብት ተናግቷል፤ የኑሮ ውድነቱም ተባብሷል።

ቢቢሲ እንዳስነበበው ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊሸጋገር እንደሚችል የተሰጋውን ጦርነት ለማስቆም ፓኪስታን ለማሸማገል ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። ስጋቱን ባያጠፋም ለቀናት ያህልም ቢሆን የጥይት ድምፅ እንዳይኖር ያደረገ እፎይታን አስገኝቷል።

አልጀዚራ እንደዘገበው ደግሞ በፓኪስታን አደራዳሪነት ሲኬሄድ የቆየው ሽምግልና የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም። ከሁለት ሳምንታት በፊት በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢዝላማባድ ሊካሄድ የነበረው ድርድር ሳይሳካ መቅረቱን በማሳያነት ጠቅሷል። በወቅቱም የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ኢዝላማባድ እንደሚደርሱ ሲጠበቅ የጉዞ ውሳኔው ስለመሰረዙ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል። በዚህ የተበሳጩት የኢራን ተደራዳሪዎች ታዲያ ወደ ሩሲያ በማቅናት ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን ነው የኢራን መንግሥታዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘገበው።

ኢራን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ይበልጥ ለማጠናከር ፊቷን ወደ ሩሲያ እና ቻይና አዙራለች። ኢራን በየቀኑ ለዓለም ገበያ ከምታቀርበው ከአንድ ሚሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ ውስጥ 90 በመቶው መዳረሻው ቻይና መሆኗን ልብ ይሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን ከምድረ ገጽ ትጠፋለች!” ሲሉ መዛታቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቦ ነበር። ኢራን በምላሿም “እስካሁን ያልተሞከረ የቅጣት ዱላዬን አሳርፍብሻለሁ!” በማለት ነው ቁጣዋን የገለጸችው።

በሁለቱ ሀገራት ዛቻ ይበልጥ ውጥረት ውስጥ ገብቶ የሰነበተው አካባቢውም በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል ከፍተኛ የሚሳዔል ተኩስ ልውውጥ መደረጉን  አልጀዚራ ዘግቧል። ይህም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ፍጻሜ ሊሆን እንደሚችል እና ውጥረቱም ወደ ለየለት ጦርነት እንዳይሸጋገር ተሰግቶ ነበር።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ከኢራን በተተኮሱ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ጥቃት እንደደረሰባት አስታውቃለች። በጥቃቱም የነዳጅ ማከማቻ ስፍራዋ መመታቱን ነገር ግን በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስታውቃች። በዚህም ፉጃይራህ ፔትሮሊየም ኢንዱስትሪ ዞን ጉዳት ደርሶበታል። የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው የፔትሮሊየም ኢንዱስትሪ ዞኑ ከዚህ በፊትም ጥቃት ደርሶበት ነበር።

በቀን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የሚያስተላልፍ መስመር የተዘረጋለት ግዙፍ መስመር ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙት የነዳጅ ማስተላሌፊያ መስመሮችም ዋነኛው ስለመሆኑ ነው ዘገባው ያመላከተው።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ሴንቲኮም አሜሪካ ስድስት የኢራን ጀልባዎችን መትቶ ማስመጡን አስታውቋል። ኢራን ግን አስተባብላለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ነጻነት ፕሮጀክት (ፕሮጀክት ፍሪደም) በሚል ኢራን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ለመሰንዘር ጦራቸው በተጠንቀቅ ላይ ነበር። ይሁንና ይህን ባሉ 48 ሰዓታት ሳይሞላው ደግሞ  በኢራን ላይ ሊደረግ የታሰበው መጠነ ሰፊ ጥቃት መቆሙን ትሩዝ በተሰኘው የማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። ለዚህ ደግሞ በኢራን በኩል ገንቢ ምላሽ እንደተሰጣቸው ነው ያነሱት።

ሮይተርስ እንደዘገበው በሆርሙዝ ሰርጥ ዉስጥ መንቀሳቀሻ አጥተው የቆሙትን መርከቦች አጅበው ለማስወጣት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይዘውት የነበረውን ዕቅድ ለጊዜው ገታ አድርገውታል። ኢራን በበኩሏ መርከቦች በሰርጡ በኩል ማለፍ የሚችሉት በእርሷ ፈቃድ ብቻ መሆኑን አስታውቃለች። በሰርጡ ለማለፍ ፈቃድ በማይጠይቁት ላይ “ወሳኝ እርምጃ እወሰዳለሁ” ስትልም ነው ያስጠነቀቀችው።

በሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ምክንያት የ87 ሃገራት ዜጎች 22 ሺህ 500 ባሕርተኞች እና አንድ ሺህ 550 የንግድ መርከቦች መንቀሳቀሻ አጥተው መቆማቸውን ዘገባው አመላክቷል። ተግባራዊ ሊደረግ የነበረው፣ ለጊዜው እንዲቆም የተወሰነው ነጻነት ፕሮጀክትም እነዚህን ሰዎች እና መርከቦች ነጻ ለማውጣት ያለመ ስለመሆኑ አሜሪካ አስታውቃ ነበር::

እንዲህ እንደ ዥዋዥዌ የሚለዋወጠው የመካከለኛወው ምሥራቅ ፖለቲካ የዓለምን ትኩረት እንደሳበ ቀጥሏል፤ መግለጫዎች በተሰጡ ቁጥር የዓለም የነዳጅ ዋጋ አብሮ ላይ እና ታች እያለ ነው ::

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here