በቤት ውስጥ ያለው ቤት

0
20

በክሮሺያ ብራክ በተሰኘች ደሴት በልዩ አሰራሩ ከአንድ ምእተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ በቤት ውስጥ የተገነባን ቤት  ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባስገራሚነቱ ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በአድራቲክ ባህር ዳርቻ  በምትገኘው ብራክ ደሴት ቦል ከተማ መካከል ነው የሚገኘው- በቤት ውስጥ ያለው ቤት፡፡ ህንፃው የተመልካችን ዓይን የሚስብ አይደለም ፡፡ ነገር ግን ቀርቦ ለተመለከተው በአንድ አሮጌ ያልተጠናቀቀ ግዙፍ የቤት ግድግዳ መካከል አነስተኛ መኖሪያ ቤት መኖሩን ይገነዘባል፡፡ አነስተኛው መካከል ላይ ያለው ቤትም በሰፊ ያልተጠናቀቀ የቤተ መንግሥት ግድግዳ ተከቦ የሚታይ ነው የሚመስለው፡፡

በቤት ውስጥ ያለው ቤት ታሪክ በትክክል አይታወቅም ፡፡ ነገር ግን ከትውልድ ትውልድ ተላልፎ ለዛሬ የደረሰው በርካቶች የተስማሙበትን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ቩኮቪች የተባለ ሀብታም የባህር ሀይል ቤተሰብ “ቦል” በተሰኘች ደሴት ላይ በምትገኝ ከተማ ግዙፍ መኖሪያ ለመገንባት ይወስናል፡፡ ቤተሰቡ ለሚገነባው ግዙፍ መኖሪያ ከግለሰቦች ላይ ቤት እና ቦታቸውን በመግዛት ያስነሳቸዋል፤ ከባለይዞታዎቹ  መካከልም አንዱ “ማርኮ” የተሰኘው እምቢተኛ ይሆናል፡፡

ባለሀብቱ መክሮ እና ዘክሮ አማራጭ ሲያጣ በእምቢተኛው “ማርኮ” ቤት ዙሪያ የግዙፉን  ቤት ግድግዳ ርቀቱን ጠብቆ ይገነባል፡፡

ባለሀብቱ ይህን ያደረገው “ማርኮ” – እምቢተኛው ባለንብረት ሲከበብ፣ ዙሪያው ሲታፈን በግድ ይሸጣል ከሚል እምነት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በመጨረሻም የባለሀብቱ ሦስት ቤተሰቦች ግዙፉን ህንፃ ገንብተው ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ለመግዛት በባህር ላይ ሲጓዘ ሞተው ደብዛቸው ይጠፋል፤ ግዙፉ ህንፃም በጅምር ቀርቶ የእምቢተኛው  ቤት ግን ባለበት ለደሴቷ መስህብ መሆኑን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here