ጮቄ ተራራ

0
18

የጮቄ ተራራ ከአዲስ አበባ 300 ኪሎ ሜትር፣ ከምሥራቅ ጐጃም ዞን ዋና ከተማ ደብረማርቆስ ደግሞ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በብዝሃ ህይወት ሀብት የበለፀገ ቀጣና ነው፡፡ “የጐጃም ጣሪያ ” የምሥራቅ አፍሪካ “የውኃ ማማ” በሚል የሚጠራው የጮቄ ተራራ የ59 ወንዞች እና የ273 ጅረቶች መፍለቂያ ነው፡፡ ስፋቱም 53, 358 ሄክታር ተለክቷል፡፡

የጮቄ ተራራ ከፍተኛው ጫፍ 4100 ሜትር ዝቅተኛው በዐባይ ወንዝ ሸለቆ 1000 ሜትር ከመሬት ወለል በላይ ተለክቷል፡፡ በጮቄ ተፋሰስ ከምሥራቅ ጐጃም – ደጀን፣ አዋበል፣ ቢቸና እና ደባይ ጥላት ግን ወረዳዎች ተካተዋል፡፡ ተፋሰሱ ለ150 ሺህ በከብት እርባታ እና በእርሻ ለሚተዳደሩ በቀጣናው ለሚገኙ ዜጐችም መኖሪያ ነው፡፡

በዓየር ንብረቱ ሞቃታማው የዓባይ ሸለቆ ቀዝቃዛው የተራራው ጫፍ 4100 ሜትር  መሆኑ ነው የተጠቀሰው፡፡

የጮቄ ተራራ በመልካምድራዊ አቀማመጡ ሦስት ጫፎች አሉት -ገማሴ አምባ፣ ቁሊት እና ሌማት አምባ ሲሆኑ ከነዚሁ አናት ሌሎቹን ዝቅ ያሉትን መቃኘት ያስችላሉ፡፡

በእፅዋት ሀብትም ቀጣናው 85 ዝርያዎች ያሉት ሲሆን ቁጥቋጦ ለበስ ጅብራ የሚታይበት የሳር ምድር ሰፊውን ቀጣና አልብሶት ይታያል፡፡

ከአጥቢ እንስሳት 16 ዝርያዎች፤ ከዓእዋፍ ደግሞ 41 ዝርያዎች መኖራቸው ተረጋግጦ በድረ ገፆች ሰፈሯል፡፡

በ2022 እ.አ.አ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የቱሪዝም ድርጅት የጮቄ ተራራ “ኢኮ ቪሌጅ”ን ምርጥ የቱሪዝም መንደር በሚል ሰይሞታል፡፡

ለተፋሰሱ ዘላቂነት ወይም ተጠብቆ መዝለቅ ልቅ ግጦሽ፣ የአፈር መሸርሸር፣ የደን መመንጠር ስጋቶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ለስጋቶቹ በአቅራቢያው የሚገኘው የደብረማርቆስ የኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት ለኗሪዎቹ አማራጭ መተዳደሪያ እንዲፈጠርላቸው የመፍትሄ ሀሳብ ጠቁሟል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት አክሽንቱር ኢትዮጵያ፣ ቪዚት ኢትዮጵያ፣ ወርቅ አምባ ቱር ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሰኔ 29  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here