በክረምቱ የግብርና ሥራዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል

0
198

የዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ በኤልኒኖ ክስተት አማካኝነት በየጊዜው  ይናወጣል። የኤልኒኖ ክስተትም በየዘመኑ በመቀያየር በተፈጥሮ ላይ  ከፍተኛ  ችግሮችን ይፈጥራል። የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ተጽእኖም ከፍተኛ ሲሆን የሙቀት መጨመር፣ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ያልተለመደ ዝናብ፣ የሰብል ምርት መቀነስ እና በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ችግር መፍጠር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች አማካኝነት የሚከሰት ሲሆን ዘርፈ ብዙ ችግሮችንም ያስከትላል።

ከችግሮች መካከልም  የዝናብ ስርጭትን ማዛባት ዋነኛው ሲሆን  የዝናብ ስርጭቱን በመቀነስ ለድርቅ እንዲሁም ዝናቡን  በማብዛት ለከፍተኛ ጎርፍ እና የሙቀት መጠንን በመጨመር  የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ይቀይራል፡፡  የዚህ ውጤትም በአንዳንድ ሀገራት ድርቅን ሲያባብስ፣ በሌሎች ደግሞ ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍን ያስከትላል።

በኢትዮጵያም የዘንድሮው የዝናብ መጠንና ስርጭት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር በግብርና፣ በውኃ ሀብት እና በምግብ ዋስትና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል  የምሥራቅ አማራ የሜትሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል አስታውቋል።

የማዕከሉ  ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይመር መሐመድ ለአሚኮ እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን የክረምት ትንበያ መሠረት በማድረግ፣ ወቅቱ ተመሳሳይ የአየር ባሕርይ ከነበራቸው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1997 እና 2023 ተከስቶ ከነበረው  ጋር ተመሳሳይነት ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት የሁለቱም ዓመታት የዝናብ መጠን መደበኛና ከመደበኛ በታች እንደነበርም የተመዘገበው መረጃ ያሳያል፤ በዚህም  በዘንድሮው ክረምት (2018/19) ወደ 90 በመቶ ገደማ የኤልኒኖ ባሕርይ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ማዕከሉ ባደረገው የትንበያ ግምገማ መሠረት በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች በአጠቃላይ መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት ይኖራል። ይሁን እንጂ የዝናብ መከሰት ዕድሉ በየዞኖቹ ልዩነት አለው። በዚህም  ሰሜን ሸዋ  45በመቶ መደበኛ፣ 35በመቶ ከመደበኛ በታች እና 20በመቶ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከሌሎች የምሥራቅ አማራ አካባቢዎች በተሻለ መደበኛ ዝናብ የማግኘት ዕድል ይኖረዋል፡፡

በአንጻሩ ሰሜን እና  ደቡብ ወሎ እንዲሁም  የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ምሥራቃዊ ክፍሎች የዝናብ ስርጭታቸው 55 በመቶ ከመደበኛ በታች፣ 35በመቶ መደበኛ እና 10በመቶ ከመደበኛ በላይ የመሆን ዕድል እንደሚኖራቸው  ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል።

ዋግኽምራ እና የወሎ  ምዕራባዊ አካባቢወች ደግሞ 45በመቶ መደበኛ፣ 40በመቶ ከመደበኛ በታችና 15በመቶ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የዘንድሮው ክረምት  የዝናብ ሁኔታ በአገባቡ መደበኛ እና ወቅቱን የተከተለ ቢሆንም አርሶ አደሮች የሰብል መበላሸት እንዳያጋጥማቸው በተከታታይ ሦስት ቀናት  በቂ ዝናብ መዝነቡን አረጋግጠው መዝራት እንዳለባቸው አቶ ይመር አሳስበዋል። በተለይ በሰሜን ሸዋ ዞን እንደ ምንጃር ሸንኮራ ያሉ ምርታማ አካባቢዎች ዝናቡ ቀድሞ የመግባት ዕድል ስላለው በቂ ርጥበት ሲገኝ መዝራት ይመረጣል ብለዋል።

በሌላ በኩል ክረምቱ  ቀድሞ ሊወጣ እንደሚችል የሜቲሮሎጂ ትንበያው ያመላከተ መሆኑንና በተለይም ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ የዝናብ መጠን የመቀነስና ከመስከረም ቀድሞ የመቋረጥ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ ይህ ሁኔታ በመስከረም ወር  የርጥበት እጥረት ሊያስከትል እንደሚችልና ከዚህ በተጨማሪም በክረምቱ መካከል ደረቅ ቀናት ሊበዛ ስለሚችሉ የተዛባ የዝናብ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል ትንበያው ማመላከቱን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በመሆኑም ይህን ክስተት ለመቋቋም እና መፍትሄ ለማስቀመጥ ያመች ዘንድ የአየር ትንበያዎችን በቅርብ መከታተልና በተለይም በግብርና ዘርፍ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ የኤልኒኖን ተጽዕኖ ለመቀነስ ጠቃሚ መሆኑ ተጠቁሟል።

የአየር ሁኔታ ተፅዕኖን ለመቋቋም አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ድርቅን መቋቋም የሚችሉና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የሰብል ዝርያዎችን መምረጥ እንዳለባቸውም ኃላፊው መክረዋል፡፡ የረጅም ጊዜ ትንበያው ለዕቅድ የሚያገለግል በመሆኑ አርሶ አደሮች የ10 ቀንና የዕለታዊ አጫጭር የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን በመከታተል እና የመዝሪያ ቀናትን ማስተካከል ይኖርባቸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የርጥበት ማቆያ ሥራዎችን ማጠናከርና የዝናብ ውኃ አሰባሰብ ስልቶችን መተግበር አስፈላጊ ሲሆን በእንዲህ አይነት ወቅት  ማለትም ደረቅና ዝናባማ ቀናት ተቀላቅለው በሚመጡበት ወቅት የተባይና የበሽታ መከሰት ዕድል ከፍተኛ ስለሚሆን የማሳዎችን ሁኔታ በቅርበት መከታተል ያስፈልጋል።

በተያዘው የምርት ወቅት  ምናልባት የአዝመራ መጨናገፍ የሚከሰት ከሆነ የሚተኩ ሰብሎችን  አስቀድሞ ማዘጋጀትም ተገቢ ይሆናል ፡፡

የምሥራቅ አማራ ሜቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ይህንን መረጃ ተደራሽ ለማድረግ በየሦስት ቀኑ፣ በየ10 ቀኑ እና በየወሩ መረጃዎችን በተለያዩ አማራጮች ለሁሉም ሴክተሮችና ለአርሶ አደሮች እያደረሰ እንደሆነ ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮም ችግሩን አስቀድሞ ለመቋቋም ያስችለው ዘንድ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ማንደፍሮ አስላከ /ዶ.ር/ ለበኩር ተናግረዋል፡፡

የዝናብ እጥረት ወይም መዘግየት የሰብል ልማትን እንዳያስተጓጉል ችግሩ ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው በተለዩ ወረዳዎች ላይ የተቀናጀ የሥራ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራም ተገብቷል። በዚህም የአካባቢውን ሁኔታ በመገምገም የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው የሚከሰተውን ጉዳት ለመቀነስ እየሰሩ ነው።

እንደ ዳይሬክተሩ  ማብራሪያ ቢሮው በተለይ በሦስት ዋና ዋና አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡ የመጀመሪያው ቀድመው የሚደርሱና ድርቅን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን መለየትና ለአርሶ አደሮች ማቅረብ ሲሆን ይህ አካሄድ የዝናብ ጊዜ ቢያጥርም ሰብሎቹ እድገታቸውን አጠናቀው ምርት እንዲሰጡ ያግዛል። ሌላው  ደግሞ ያለውን ርጥበት በአግባቡ በመጠቀም በወቅቱ መዝራትን ማበረታታት እንዲሁም  በማሳ ላይ የሚወርደውን ዝናብ እንዳይባክን በማቆር ማስቀረትና የእርጥበት ጥበቃ ሥራዎችን ማስፋፋት ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ችግሩ ሊገጥማቸው በሚችሉ አካባቢዎች ያሉ የመስኖ ልማትን ወደ ሙሉ ስራ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡  በተለይም ሰብሎች በአበባና በፍሬ የእድገት ደረጃ ላይ ሲሆኑ የውሃ እጥረት እንዳይጎዳቸው በመስኖ ማገዝ በቅድሚያ ከተያዙ ስራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ  እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በዘንድሮው ክረምት  የድርቅ አደጋ ሊያጋጥማቸው በሚችሉ 51 ወረዳዎች ላይም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር እንዲሁም ከምስራቅ ጎጃም የተወሰኑ አካባቢዎች በእቅዱ ተካተዋል። ለእነዚህ አካባቢዎችም ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ፣ ከ1 ሺህ ኩንታል በላይ የሩዝ፣ 700 ኩንታል ጤፍ፣ ከ500 ኩንታል በላይ በቆሎና ሌሎች ዘሮች እየተሰራጩ መሆኑ የቅድመ ዝግጅቱ ተግባራዊ መሆንን ያሳያል።

ይሁን እንጅ ችግሩን በዘር ስርጭት ብቻ መፍታት አይቻልም።

የአየር ንብረት ለውጥ በየዓመቱ የዝናብ ባህሪን እየቀየረ በመሆኑ፣ የውሃ አስተዳደር፣ የአፈር ጥበቃ፣ የመስኖ ሽፋን ማስፋፋት፣ የአየር ትንበያን በመረጃ የተደገፈ የእርሻ ሥርዓት መጠቀም እና የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማሳደግ እኩል ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በመሆናቸው  የዝናብ እጥረትን መቋቋም የግብርና ቢሮ ብቻ የሚሰራው ተግባር ሳይሆን፣ የአመራሩ፣ የባለሙያዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ የአጋር ድርጅቶችና ከሁሉም በላይ የአርሶ አደሩ የተቀናጀ ተሳትፎ የሚጠይቅ ሀገራዊ ጉዳይ ነው። የድርቅ አደጋ ከተከሰተ በኋላ ከመሮጥ ይልቅ ከመከሰቱ በፊት በመዘጋጀት የሚደረግ ሥራ ውጤታማ በመሆኑ በብዙ ሀገራት ተረጋግጧል።

በመሆኑም የክልሉ ግብርና ቢሮ የጀመረው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መረጃዎችን በወቅቱ በመለዋወጥ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ አርሶ አደሮችም የባለሙያዎችን ምክር በመከተል፣ ድርቅን የሚቋቋሙ ዘሮችን በመጠቀም፣ የዝናብ ውሃን በማቆርና በመስኖ አጠቃቀም ላይ ትኩረት በመስጠት የሚመጣውን አደጋ ወደ ዕድል መቀየር ይችላሉ። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዛሬ የሚደረገው የቅድመ ዝግጅት ነገ የሚገኘውን ምርት የሚወስን ወሳኝ ምክንያት መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።

የአየር ትንበያዎችን በመከታተል እና የቅድመ ጥንቃቄወችን በማከናወን ረገድም  ፔሩ፣ ቬትናም እና ፊሊፒንስ በኤልኒኖ ተፅዕኖን በመቋቋም በዓለም ላይ ተጠቃሽ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው። በተለይ በ2017 የተከሰተው “Coastal El Niño” ከፍተኛ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የግብርና ጉዳት አስከትሎ ነበርና ከዚያ በኋላ አገራቱችግሩን የሚቃቃም ልዩልዩ  ዘዴዎች በመተግበር የመቋቋም አቅማቸዉን አጠናክረዉ ተጠቅመዉበታል።

ሃገራቱ ከተጠቀሙበት ዘዴዎች መካከልም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን አጠናክሮ የአየር ሁኔታና የውሃ መረጃዎችን በፍጥነት ለህብረተሰቡ ማድረስ፣ የወንዝ ዳርቻዎችን ማጠናከር፣ የጎርፍ መከላከያ ግንቦችን መገንባት፣ የውሃ ማፍሰሻ መስመሮችን ማስፋፋት፣ ድርቅና ጎርፍን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን ማስፋፋት፣ የመስኖ ስርዓቶችን ማሻሻል፣የአደጋ ስጋት ቅነሳን በልማት እቅዶች ውስጥ ማካተት፣ ከፍተኛ አደጋ ያለባቸውን አካባቢዎች ካርታ ማዘጋጀትና ህዝብን ከአደጋ ቀጠናዎች ማስወጣት እና የመሳሰሉትን ዘዴወች ተግብረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከአርሶ አደሮች ጋር በቅርበት በመስራት የአየር ትንበያን መሠረት ያደረጉ የመዝሪያ ጊዜና የሰብል ምርጫ ምክሮችን መስጠት፣ የውሃ ማከማቻን ማሳደግ፣ ውሃን በቁጠባ መጠቀም፣ ድርቅን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎችን ማስፋፋት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን ማጠናከር እና ለገበሬዎች ፈጣን ድጋፍ በመስጠት ጥሩ ውጤት አሳይተዋል።

ከእነዚህ ሃገራት ተሞክሮዎች ለኢትዮጵያ የሚወሰዱ ዋና ዋናወቹ  የቅድመ ማስጠንቀቂያን ማጠናከር፣ የውሃ ሀብትን በተቀናጀ መንገድ ማስተዳደር፣ የአየር ንብረትን የሚቋቋሙ የግብርና ስርዓቶችን ማስፋፋት፣ የአደጋ ስጋት ቅነሳን በልማት እቅዶች ውስጥ ማካተት እና በማህበረሰብ ደረጃ የዝግጁነት አቅምን ማጠናከር ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ስራዎች ናቸው።

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሰኔ 29   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here