ውሻን የሚያሳብድ በሽታ:- ከ4ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀው ገዳይ ቫይረስ

0
127

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ (ራቢስ) የሰው ልጅ ከሚያውቃቸው በጣም ጥንታዊ በሽታዎች አንዱ ነው፡፡ የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት(woah.org) እንዳስታወቀው ከአራት ሺህ ዓመታት በፊት የነበረ ነው፡፡ በጥንታዊ ሜሶፖታሚያም በተጻፉ ሕጎች ላይ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ የሚያስከትለውን አደጋ የሚገልጹ መዝገቦች ተገኝተዋል፡፡

ወርልድ ፕረስ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋው አርስቶትል ያበዱ ውሾች ሌሎችን እንስሳትና ሰዎችን በመንከስ በሽታውን እንደሚያስተላልፉ ጽፏል፡፡ እ.አ.አ በ1885 ደግሞ ሉዊስ ፓስተር የመጀመሪያውን የፀረ-ውሻ የሚያሳብድ በሽታ ክትባት በተሳካ ሁኔታ በመፍጠር በዓለም የሕክምና ታሪክ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፡፡

 

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ምንድን ነው?

 

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ በራቢስ ቫይረስ (Rabies virus )የሚከሰት፣ የአንጎልና የነርቭ ሥርዓትን የሚያጠቃ  ነው፡፡ ቫይረሱ በአብዛኛው በቫይረሱ በተያዘ ውሻ ልሃጭ ውስጥ ይገኛል፤ በመሆኑም በውሻው ንክሻ፣ መቧጨር ሲያጋጥም ወይም ሰውነት ላይ ባሉ ክፍት ቁስሎች እንዲሁም ዐይን እና አፍ ውስጥ በልሃጩ አማካኝነት ወደ ሰው ሰውነት ዘልቆ ሊገባ ይችላል፡፡ ቫይረሱ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ በደም ሳይሆን በነርቭ ሥሮች ውስጥ ቀስ በቀስ ወደ አንጎል ይጓዛል፡፡ ይህ ጉዞም ሳምንታት ወይም ወራት ሊፈጅ ይችላል፡፡ አንጎል ላይ ከደረሰ በኋላ ግን ሕመሙ በፍጥነት ይባባሳል፡፡ የዚህ በሽታ አስፈሪ ባሕሪ ምልክቶቹ ከታዩ በኋላ በአብዛኛው ጊዜ ለመዳን የማይቻል መሆኑ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚገልጸው ቫይረሱ አንጎልን ካጠቃ እና  ምልክቶች ከታዩ በኋላ በሽታው  ገዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የሕይወት ማዳኛው ቁልፍ ሕክምና ሳይሆን ቅድመ መከላከል መሆን እንዳለበት ነው መረጃው የጠቆመው፡፡

 

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ምልክቶች፤

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ የሚያስከትለው ቫይረስ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ ወዲያውኑ ለሕመም አይዳርግም፡፡ በአብዛኛው ከአንድ እስከ ሦስት ወራት ውስጥ ምልክቶች ይታያሉ፤ ሆኖም እንደ ንክሻው ቦታ፣ የጉዳቱ ጥልቀት እና የገባው የቫይረስ መጠን ላይ በመመስረት ከጥቂት ቀናት እስከ ብዙ ወራት ወይም አንዳንድ ጊዜ ከአንድ ዓመት በላይም ሊዘገይ ይችላል፡፡ የመጀመሪያ ምልክቶቹ እንደ ጉንፋን ወይም እንደ ቀላል የቫይረስ በሽታ ይመስላል፡፡ ታካሚው ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና በተነከሰበት ቦታ የማቃጠል፣ የማሳከክ ወይም የመጠዝጠዝ ስሜት ሊሰማው ይችላል፡፡

 

ቫይረሱ አንጎልን ካጠቃ በኋላ ግን ሕመሙ በፍጥነት ይባባሳል፡፡ በዚህ ደረጃ የሚታዩ ምልክቶች የነርቭ ሥርዓት መጎዳቱን ያመለክታሉ፡፡ ከእነሱም መካከል ከፍተኛ ጭንቀት፣ ድንጋጤ፣ ቁጣና ጠበኝነት፣ ቅዠት፣ የጡንቻ መኮማተር፣ለመዋጥ መቸገር፣ ብዙ ምራቅ መፍሰስ ወይም የልሃጭ መዝረብረብ፣ የአዕምሮ መረበሽ እንዲሁም ውኃን መፍራት (Hydrophobia) ናቸው፡፡

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ሲጠቀስ ብዙ ሰዎች የሚያስታውሱት “የውኃ ፍርሃትን” ነው፡፡ ይህ ግን ውኃን ማየት መፍራት ብቻ አይደለም፡፡ ቫይረሱ የጉሮሮና የመዋጥ ጡንቻዎችን ስለሚያጠቃ ተጎጅዎች ውኃ ለመጠጣት ሲሞክር እጅግ የሚያሠቃይ የጡንቻ መኮማተር ስለሚገጥማቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ታካሚው ውኃን መጠጣት ይፈራል፤ አንዳንድ ጊዜ የውኃ ድምፅ ወይም የሚፈስ ውኃ ማየት ብቻ እንኳን የጉሮሮ መኮማተርን ሊያስነሳ ይችላል፡፡

ሁሉም ታካሚዎች ግን ጠበኛ ወይም የውኃ ፍርሃት ያለባቸው አይሆኑም፡፡ 20 በመቶ ያህሉ ታካሚዎች ሽባ በሚያደርገው “ፓራሊቲክ ራቢስ”(Paralytic Rabies) በተባለው ዓይነት ይያዛሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ቀስ በቀስ የጡንቻ ድክመት፣ ሽባነት፣ ለመተንፈስ መቸገር እና በመጨረሻ ራሳቸውን ሊስቱ እንደሚችሉ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (CDC)አስታውቋል፡፡

 

በዓለም ላይ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ምን ያህል የጤና ችግር ፈጥሯል?

 

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ  ሙሉ በሙሉ በክትባት መከላከል የሚቻል ቢሆንም አሁንም በ159 ሀገራት በየዓመቱ 50ሺህ ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ከዚህም  95 በመቶ ያህሉ በአፍሪካና በእስያ ይከሰታሉ፡፡ ከሟቾቹ መካከል 40 በመቶው   የሚመዘገበው ከ15 ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት ነው፡፡ ሰዎች ሊሞቱ የቻሉት የውሾች ክትባት አነስተኛ በመሆኑ፣ ለተነከሱ ሰዎች ክትባት በፍጥነት አለመድረሱ እና በገጠር አካባቢዎች የጤና አገልግሎት ውስን በመሆናቸው ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ ሁኔታ

ኢትዮጵያ  ውሻን በሚያሳብድ በሽታ ምክንያት በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካለባቸው ሀገራት መካከል እንደምትገኝ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡ በበርካታ  ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች የጎዳና ውሾች ቁጥር መጨመር፣ የውሾች ክትባት ዝቅተኛ መሆን እና ከንክሻ በኋላ ወዲያውኑ ሕክምና አለማግኘት በሽታውን እንዲቀጥል ያደርገዋል፡፡ በሀገሪቱ  የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የፀረ-እብድ ውሻ ክትባት እንደሚወስዱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በብዙ ገጠራማ አካባቢዎች የሟቾች ቁጥር  ስለማይመዘገብ ትክክለኛውን መጠን ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን   ነው መረጃዎች የጠቆሙት፡፡

የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት (ከሀምሌ-ታሕሳስ)ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ ያላቸውን የሕብረተሰብ ጤና ችግሮች ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ በመግለጫውም  ከመስከረም እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ሊከሰት ስለሚችል  ማሕበረሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡ በዚህም ‎በክልሉ ውሻን የሚያሳብድ በሽታን በዘላቂነት ለመፍታት ባለቤት የሌላቸውን ውሾች መቆጣጠር የሚያስችል አዲስ  ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡን ተጠቁሟል፡፡

እንዴት እንከላከል፡-

ዓለም ውሻን የሚያሳብድ በሽታን ለመከላከል እና ለማጥፋት ትልቅ ርብርብ ላይ ትገኛለች፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)፣ የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት (WOAH)፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) እና ግሎባል አሊያንስ ፎር ራቢስ ኮንትሮል(Global Alliance for Rabies Control) በመተባበር ዚሮ ባይ ሰርቲ(“Zero by 30”) የተባለ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ ዓላማው እ.አ.አ እስከ 2030 ድረስ በውሻ ንክሻ የሚከሰት የሰዎችን  ሞት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ነው፡፡ ይህ የሚሳካው ደግሞ ቢያንስ 70 በመቶ ውሾችን በየዓመቱ መከተብ ፣ ለተነከሱ ሰዎች ክትባትን በነጻ ወይም በቀላሉ እንዲያገኙ ፣ ማሕበረሰቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው እንዲሁም የሰውና የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች በአንድነት እንዲሠሩ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

 

መረጃ

ውሻን የሚያሳብድ በሽታ (ራቢስ) ያለበት ውሻ የሚያሳያቸው ምልክት በየደረጃው ይለያያል፡፡

 

  1. የመጀመሪያው ደረጃ (Prodromal stage) ባሕሪው የሚቀየር ሲሆን ማለትም ዝምተኛ የነበረ ውሻ ጨካኝ ሊሆን ይችላል፤ ጨካኝ የነበረ ውሻ ደግሞ ዝምተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ እረፍት ማጣት፣ መደበቅ ወይም ብቻውን መሆን፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ያጋጥመዋል፡፡

 

  1. ጨካኝ (Furious rabies) ደረጃ ሰዎችን፣ ውሾችን ወይም ሌሎች እንስሳትን መንከስ ያለምክንያት ጥቃት መፈጸም፣ በቀላሉ መበሳጨት በጣም መጮህ ወይም ድምፁ ይቀየራል፤ ያለማቋረጥ ይሮጣል፣ የማይበሉ ነገሮችን (ድንጋይ፣ እንጨት፣ አፈር) በመንከስ ብዙ ልሃጭ ይዝረበረባል፡፡

 

3.የሽባ (Paralytic/Dumb rabies) ደረጃ አገጩ ይንጠለጠላል፣ ምግብና ውኃ መዋጥ ይቸገራል፤ልሃጩ በብዛት ይዝረበረባል፣ ድምጹ ይቀየራል፣ የኋላ እግሮቹ ይዝላል፣ ሙሉ ሰውነቱ ሽባ ይሆናል፤ ከነዚህ ምልክቶች በኋላም በጥቂት ቀናት ውስጥ ይሞታል፡፡ ልብ ማለት የሚገባው አንዳንድ ውሾች እነዚህ ምልክቶች ሳይታይባቸው በሽታውን ማስተላለፍ ሥለሚችሉ መጠንቀቅ ግድ ይላል፡፡

 

 

ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት፣ የአሜሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል(CDC)

(ሳባ  ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here