ለሀገር ልማት እና ለሕዝብ እድገት ዋናው ቁልፍ ትምህርት ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ዘርፉ የተፈለገውን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የትምህርት ተቋማት ብቻቸውን የሚያከናውኑት ሥራ በቂ አለመሆኑን፣ የዘንድሮው የትምህርት ዘመን የገጠመው ፈተና እና የቀጣዩ እቅድ በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከሰሞኑ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡
የትምህርቱን ዘርፍ ለማሳለጥ በዋናነት ከሚያስፈልጉ ተቋማት መገናኛ ብዙኃን( ሚዲያዎች) ቀዳሚው ነው፡፡ ሚዲያ በትምህርት ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የተሳካ ተሞክሮን በማስተዋወቅ፣ ወላጆችንና ማኅበረሰቡን ለትምህርት ድጋፍ በማነሳሳት፣ የትምህርት ፖሊሲዎችንና ሪፎርሞችን ለሕዝብ በቀላሉ በማድረስ እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ከመፍትሔ አቅጣጫ ጋር በማቅረብ ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡
ሚዲያ በተለይም በግጭትና በሌሎች ፈተናዎች ምክንያት የተስተጓጎለ የትምህርት ሥርዓት እንደገና እንዲያንሰራራ ማኅበረሰቡን በማነቃቃትና የጋራ ተሳትፎን በማጠናከር የማይተካ ሚና ይጫዎታል፡፡
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር የነገ ሀገር የምትመስለው ዛሬ የሚገነባውን ትውልድ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርስም በችግር ውስጥ ሆኖም በትምህርት ዘርፍ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በእነዚህ ሥራዎች የሚዲያዎች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር በመጥቀስ በተለይ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በክልሉ በግጭት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት እንዲቀጥል ተማሪዎች እና መምህራን በትምሀርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲልኩ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳበረከተ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ሚዲያዎችን ጨምሮ ሁሉም አጋር አካላት በትምህርት ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ ትኩረት የሚሰጠው ለተማሪዎችና ለትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን በመምህራን ሙያዊ አቅም ላይም ነው፡፡
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዓባይ መንግሥቴ በበኩላቸው በዓለም ላይ የበለጸጉ ሀገራት የእድገታቸው መሠረት ትምህርት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያም ዘላቂ ብልጽግናና እድገት ለማረጋገጥ በትምህርት ዘርፍ በጥንካሬ መሥራት እንዳለባት አስገንዝበዋል፡፡ ባለፉት አስርት ዓመታት በትምህርት ሥርዓት፣ በተደራሽነት፣ በፍትሐዊነትና በጥራት ዙሪያ መሠረታዊ ችግሮች እንደ ነበሩ ያስታወሱት ኃላፊው፤ እነዚህን ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ የጸጥታ ችግሮች ተጨማሪ ፈተና መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት የሁሉም ወገን ቅንጅታዊ ርብርብ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሀገር ደረጃም ሆነ በክልሉ ከጥራት፣ ከፍትሐዊነትና ከተሳትፎ አንጻር አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በትምህርቱ ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ ፖሊሲና ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሰሜኑ ጦርነትና በክልሉ የጸጥታ ችግር ምክንያት የትምህርት መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን፣ መምህራንና ተማሪዎችም ለከባድ ቀውስ መዳረጋቸውን አውስተዋል፡፡ ይህን ፈታኝ ሁኔታ በጋራ ለመቀየርም በ2018 የትምህርት ዘመን በትውልድ ንቅናቄ፣ በትምህርት ቤት ምገባ፣ በቅድመ አንደኛ ትምህርት ማስፋፊያና በልዩ ተሰጥኦ ማዕከላት ላይ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
እንደ ፊንላንድ፣ ሲንጋፖርና ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት ሚዲያን እንደ ዋና የልማት አጋር በመጠቀም የትምህርት ሥርዓታቸውን እንዳጠናከሩ ኃላፊው የለአብነት የጠቀሱ ሲሆን በአማራ ክልልም ሚዲያዎች በትምህርት ጥራትና ተሳትፎ ላይ የጀመሩትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ የቢሮው የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል፣ በጀትና ሀብት ማፈላለግ ዳይሬክተር አቶ ዘመነ አበጀ በ2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ የትምህርት ልማት ሥራዎችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በገጠር አካባቢዎች 147 አዳዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን፣ በፌዴራልና በክልል ቅንጅት ደግሞ 308 ተጨማሪ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ መጀመሩን እንዲሁም ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለምገባ መርሐግብሩ አንድ ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የሦስት አዳሪና የአራት ሞዴል ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አዳሪ ትምህርት ቤቶቹን በቅርቡ አጠናቆ ለማስመረቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ ከሰባት ሺህ በላይ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት እና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማሟላት፣ የትምህርት ተሳትፎን ማሳደግ፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የትምህርት ቤት ምገባን ማስፋፋትና አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ዋና ትኩረቶች እንደሚሆኑ ነው የተናገሩት፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ትኩረታቸውን ከትምህርት ሊያሰናክሉ ከሚችሉ የንግድና ሌሎች አላስፈላጊ ተጽዕኖዎች የራቁ ምቹ የመማሪያ አካባቢዎችን ለመፍጠር ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በተለይም በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች በኪራይ ሕንፃዎች ውስጥ በመስራታቸው ምክንያት የሚጠበቁባቸውን መሠረታዊ መስፈርቶች ማሟላት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታትም ትምህርት ቤቶቹ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ የተለያዩ የድጋፍና የክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁሉንም ለማስተካከል ባይቻልም በተወሰነ ጊዜ ገደብ ውስጥ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው፡፡
ከፍተኛ ጉድለት በታየባቸው ትምህርት ቤቶች ላይም እስከ መዝጋት የሚደርሱ የማስተካከያ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ አቶ ዘመነ ያስታወቁት፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በቀጣይም ለግል ትምህርት ቤቶች ከፋይናንስ አስተዳደር ጀምሮ እስከ አጠቃላይ የትምህርት አሰጣጥና አስተዳደር ድረስ የሚያስተካክል አዲስ መመሪያና ደንብ ተዘጋጅቷል፡፡ መመሪያውን ሥራ ላይ በማዋል የግል ትምህርት ቤቶች በተቀመጡ የጥራት መስፈርቶች መሠረት እንዲተዳደሩ እና ጉድለት በሚታይባቸው ተቋማት ላይ ተገቢው የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ ግልጽ የአሠራር ሥርዓት ይፈጠራል፡፡
በመድረኩ የተሰጡ መልዕክቶች በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፉን ከነባሩ ፈተናዎች ለማላቀቅ የሚዲያዎች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የማኅበረሰብና የልማት አጋሮች የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ያሳዩ ነበሩ፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ የምትገነባው ዛሬ ለትውልዱ በሚደረገው የትምህርት ኢንቨስትመንትና በኃላፊነት በሚሠራ ሚዲያ መሆኑን አጽንኦት የሰጡበት ነበር፡፡
መረጃ
ሚዲያ ለትምህርት መሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ከነዚህም ውስጥ፡-
ትምህርትን በተለያዩ ሚዲየሞች ተደራሽ ማድረግ
አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን እና ልምዶችን በማስተዋወቅ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል ያደርጋል
ስለ ትምህርት ፖሊሲዎች፣ፈተናዎች፣ምዝገባዎች እና ትምህርታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ግንዛቤ ይፈጥራል
የስኬታማ ተማሪዎችን እና መምህራንን ታሪኮች በማቅረብ ተነሳሽነት ይፈጥራል
በዘርፉ ያሉ ችግሮችን እና ስኬቶችን በማቅረብ ተጠያቂነትን ያጠናክራል
የልምድ ልውውጦችን ያጠናክራል
የወላጅ እና የማህበረሰብ ተሳትፎ እንዲያድግ የማበረታታት ስራን ይሰራል
የምርምር እና የፈጠራ ባህልን ያበረታታል እነዚህን እና ሌሎችም በርካታ አስተዋጽኦዎችን ያደርጋል፡፡
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


