በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 92 እንደተደነገገው ሁሉም ዜጋ ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አለው። ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መብት ለማስከበር የወጣው አዋጅ ደረቅ ቆሻሻን ለሰውና ለአካባቢ ጉዳት የሚያደርስ ማንኛውም ፈሳሽ ያልሆነ ተረፈ ምርት በማለት ይተረጉመዋል። የሲጋራ ቁርጥራጭ፣ የሶፍት ወረቀት፣ ፌስታል፣ የፍራፍሬ ተረፈ ምርቶች፣ የፕላስቲክ እቃዎች፣ የውኃ ማሸጊያዎችና ሌሎች ተመሳሳይ ቁሳቁሶች በዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታሉ።
ቆሻሻን እንደ ሀብት በመመልከት መልሶ በመጠቀም ወደ ምርት በመቀየር የሥራ ዕድልና የኢኮኖሚ ጥቅም ማስገኘት እንደሚቻልም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ባለመሆኑ ግን በፈጣን የከተሞች እድገት፣ በሕዝብ ብዛት መጨመርና በፍጆታ ባህል ለውጥ ምክንያት በመንገድ እና በሌሎችም አካባቢዎች የሚጣሉ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ዛሬ ለከተሞች ከትልልቅ ፈተናዎች አንዱ ሆኗል። ቆሻሻን በአግባቡ አለመሰብሰብ፣ አለመለየትና በየመንገዱ መጣል የአካባቢ ብክለትን ከማባባስ ባለፈ በሰው ጤና፣ በከተማ ውበትና በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰም ይገኛል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ስለ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ከተሞችን ንጹህ፣ ጤናማና ውብ ለማድረግ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ አውጥቷል። ሆኖም የአዋጁ ዓላማ በሙሉ እንዲሳካ የመንግሥት፣ የግል ተቋማትና የሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው።
የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ልማት፣ ጽዳትና ውበት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ሙኔ ስለደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ለበኵር እንደተናገሩት አዋጁ በሦስት ዋና መርሆዎች ይመራል። የመጀመሪያው ቆሻሻን ከምንጩ መቀነስ፣ መልሶ መጠቀም፣ ዳግም ማዘዋወር (ሪሳይክል) እና በአግባቡ ማስወገድ ነው። ሁለተኛው የሕብረተሰብ ተሳትፎን ያማከለ ሲሆን፣ ሦስተኛው “የበከለ ይከፍላል” የሚለው ነው።
አዋጁ በአንቀጽ 10 እንደሚደነግገው ማንኛውም ሰው ለደረቅ ቆሻሻ መጣያ ተብሎ ከተዘጋጀ ቦታ ውጭ በየመንገዱ መጣል አይችልም። በሕዝብም ሆነ በግል ይዞታ ላይ ቆሻሻን በማቃጠል ማስወገድ ደግሞ የተከለከለ ነው።
አዋጁ የዜጎችን ኃላፊነትም በግልጽ አስቀምጧል፤ ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤቱ ድንበር ጀምሮ እስከ 20 ሜትር ያለውን አካባቢ ንጹህ የማድረግ ግዴታ አለበት። የንግድ ተቋማት ደግሞ ከይዞታቸው 50 ሜትር ድረስ ያለውን አካባቢ የማጽዳት ኃላፊነት አለባቸው። ቆሻሻ በተዘጋጁ ገንዳዎች ተለይቶ መጣልና ለአገልግሎቱ የተወሰነውን ክፍያ መፈጸምም የሕግ ግዴታ ነው።
በአዋጁ መሠረት ቆሻሻን የሚያመነጩ ተቋማት የቆሻሻ መጠንን ለመቀነስ፣ መልሶ ለመጠቀም( ወደ ሪሳይክል ለመላክ) ተገቢ ሥርዓት መዘርጋት አለባቸው። ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ቦታዎችን የሚያስተዳድሩ አካላትም በቂ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችና መጸዳጃ ቤቶችን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።
አዋጁን ለሚተላለፉ ሰዎችም ጠንካራ የአስተዳደርና የወንጀል ቅጣቶች ተደንግገዋል። የተከለከለ ፕላስቲክ ይዞ የተገኘ ሰው ከሁለት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር ይቀጣል። እነዚህን ፕላስቲኮች ያመረተ፣ ያስገባ፣ ለገበያ ያቀረበ ወይም የሸጠ ሰው ደግሞ ከ50 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር መቀጮ እንዲሁም እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ይደነግጋል። ሌሎች የአዋጁ ጥሰቶችም ከአምስት ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር መቀጮ ወይም እስከ አንድ ዓመት እስራት ያስከትላሉ።
“ቆሻሻ ችግር ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ዕድልም ነው” ያሉት አቶ አወቀ በተለይ ፕላስቲክ፣ ወረቀት፣ ብረትና መስታወት / ጠርሙስ/ ተለይተው ቢሰበሰቡ እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል (ሪሳይክል)ገቢ ሊያስገኙ ይችላሉ። በርካታ ያደጉ ሀገራትም ቆሻሻን ወደ ኤሌክትሪክ ኀይል፣ ማዳበሪያና ሌሎች አዳዲስ ምርቶች በመቀየር ለኢኮኖሚያቸው እሴት እየፈጠሩ ይገኛሉ። ስለዚህ የከተማ ጽዳት የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉም ዜጋ የጋራ ግዴታ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
ቆሻሻን ከምንጩ መቀነስ፣ በአግባቡ መለየት፣ መልሶ መጠቀምና አዋጁን በታማኝነት መተግበር ከተሞችን ንጹህ፣ ጤናማና ውብ ለማድረግ ወሳኝ መንገድ ነው። ንጹህ አካባቢ የጤናማ ሕይወት መሠረት እንደሆነ በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ኃላፊነት ሲወጣ የአዋጁ ዓላማ ከወረቀት ወደ ተግባር እንደሚሸጋገርም ጠቁመዋል፡፡
አዋጁ የከተማ ንፅህና የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነዋሪዎች፣ የንግድ እና የሌሎች የተቋማት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ያጎላል። ቆሻሻን በመንገድ፣ በወንዝ፣ በፍሳሽ መስመር ወይም ባልተፈቀደ ቦታ መጣል የተከለከለ ሲሆን፣ በተፈቀደ የቆሻሻ ስብስብና ማስወገጃ ስርዓት ብቻ እንዲጠቀሙ ይጠይቃል። ይህ አቅጣጫ በተግባር ሲተገበር የከተሞችን ውበት ከመጠበቅ ባለፈ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል፣ የፍሳሽ መስመሮችን ከመዘጋት ለመጠበቅና የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ እንደ ሚረዳም አቶ አወቀ አስገንዝበዋል፡፡
በመንገድ አጠቃቀም ላይም አዋጁ ያለው ትኩረት መንገድ ለታሰበበት ዓላማ ብቻ እንዲውል የሚያስገድድ ነው፡፡ የእግረኞችን መንገድ ለንግድ ማዋል፣ በግንባታ እቃ መዝጋት፣ ያለፈቃድ ማስታወቂያ ማቆም ወይም የመንገድ መብትን በሚጎዳ መልኩ መጠቀም እንዳይፈጸምም ይደነግጋል። የዚህ ዓላማ የትኛውም መንገድ ለትራፊክ ፍሰት፣ ለእግረኞች ደህንነትና ለከተማው ሥርዓት ላለው እንቅስቃሴ እንዲያገለግል ማድረግ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
አዋጁ መሠረተ ልማቶችን የመጠበቅ ግዴታ ላይም የደነገጋቸው ሕጎች አሉ፡፡ በዚህም የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የፍሳሽ፣ የአረንጓዴ ቦታዎችና ሌሎች የሕዝብ መሠረተ ልማቶች የጋራ ሀብት መሆናቸውን ያስገነዝባል። እነዚህን መሠረተ ልማቶች ማበላሸት፣ መስበር፣ ያለፈቃድ መቀየር ወይም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረግ በሕግ ተጠያቂነት ያስከትላል። ይህ አቅጣጫ መሠረተ ልማቶች በሕዝብ ገንዘብ የሚገነቡ በመሆናቸው ከብልሽት እና ከድጋሚ ወጪ ለመጠበቅ የሚያገለግል ነው።
የከተማ አስተዳደሮች የቆሻሻ ስብስብ አገልግሎትን ማሻሻል፣ የመንገድ ቁጥጥርን ማጠናከርና ለህብረተሰቡ ተከታታይ ግንዛቤ መፍጠር ይኖርባቸዋል። በሌላ በኩል ነዋሪዎችም የከተማው ንፅህናና መሠረተ ልማት የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብ ሕጉን ማክበር ይጠበቅባቸዋል።
የከተማ ልማት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ዋና ዓላማ ቅጣት መጣል ብቻ ሳይሆን ንጹህ ፣ደህንነቱ የተጠበቀ እና ለነዋሪዎቹ ምቹ የሆነ ከተማን መፍጠር ነው፡፡ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ፣ መንገዶችን በስርአት መጠቀም እና መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ የሕግ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ የከተማ ልማት መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውንም አዋጁ በግልጽ እንደሚያሳይ ነው አቶ አወቀ ያስገነዘቡት፡፡
መረጃ
የመንገድ አጠቃቀም መመሪያዎች
መንገዶች ለተሽከርካሪዎች እና ለእግረኞች ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚከተሉትን ህጎች መተግበር ያስፈልጋል፦
- የእግረኛ መንገድ አጠቃቀም፡ እግረኞች ሁልጊዜ የእግረኛ መንገድን (Sidewalk) መጠቀም አለባቸው። የእግረኛ መንገድ በማይኖርበት ጊዜ ከመንገዱ በስተግራ በኩል (ተቃራኒ ትራፊክን እያዩ) መጓዝ ይመረጣል።
- መንገድን ስለማቋረጥ፡ መንገድ ሲያቋርጡ የእግረኛ መብራት (Pedestrian light) ወይም የሰዎች መተላለፊያ (Zebra crossing) መጠቀም ግዴታ ነው።
- የተሽከርካሪ ፍጥነት ገደብ፡ አሽከርካሪዎች በተለይም በመኖሪያ አካባቢዎች፣ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ እና በሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው መንገዶች የተወሰነውን የፍጥነት ገደብ ማክበር አለባቸው።
- የመንገድ ዳር ንግድ እና ግንባታ፡ ያለ ህጋዊ ፈቃድ የመንገድ ዳርቻዎችን ለንግድ ስራ ማዋል ወይም የግንባታ እቃዎችን በመንገድ ላይ መደርደር ለትራፊክ አደጋ እና ለትራፊክ መጨናነቅ ትልቅ ምክንያት ነው።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


