የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሠረት

0
289

የኢትዮጵያ የመጀመሪያው  የተጻፈ ሕገ መንግሥት ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት በይፋ ታወጀ። ይህ ሰነድ በኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ ውስጥ ፍጹም አዲስ ምዕራፍ ከፈተ፤  ኢትዮጵያንም ከነበረችበት ጥንታዊ አደረጃጀት ወደ ዘመናዊ የመንግሥት መዋቅር አሸጋገረ። ይህም የመጀመሪያው ሕጋዊ ሙከራ እንደነበር ተክለጻድቅ መኩሪያ “ዐፄ ኃይለ ሥላሴና የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረዋል። ከዚህ ታሪካዊ አዋጅ በፊት ኢትዮጵያ በጽሑፍ የሰፈረ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት አልነበራትም። የኢትዮጵያ የበላይ ሕግ የሃይማኖት፣ የማኅበራዊ እና የፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎችን አጣምሮ የያዘው እና ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲሠራበት የነበረው ፍትሐ ነገሥት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ያልተጻፉ ዘመናት ያስቆጠሩ የአካባቢ ባሕላዊ ሥርዓቶች እና ልማዶች ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ያገለግሉ ነበር። በወቅቱ የነበረው የሥልጣን መዋቅር ዘውዳዊ እና ፍጹም ማዕከላዊ ባልሆነ መልኩ የአካባቢው መሳፍንት እና መኳንንት የየራሳቸውን ግዛት በራስ ገዝነት የሚያስተዳድሩበት የፊውዳል ሥርዓት እንደነበር ደግሞ አበራ ጀምበሬ (ዶክተር) “የኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ መግቢያ” በሚለው ጥናታቸው አብራርተዋል።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሕገ መንግሥት የማውጣትን አስፈላጊነት ያመኑባቸው በርካታ ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩ። የአካባቢውን መሳፍንት እና  ገዢዎችን ሥልጣን በመገደብ ሥልጣን ሁሉ በአንድ ማዕከላዊ የንጉሥ እጅ እንዲገባ ማድረግ ዋነኛው ፍላጎት ነበር። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያን ከነበረችበት የባላባት ሥርዓት አውጥቶ ወደ ዘመናዊ መንግሥታዊ አደረጃጀት ማሸጋገር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በወቅቱ የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል ስለነበረች ራሷን እንደ ዘመናዊ እና ስልጡን ሀገር ለዓለም ማሳየት ትፈልግ ነበር። በተለይም የአውሮፓ ሀገራት ኢትዮጵያን ኋላ ቀር አድርገው የሚመለከቱበትን ምክንያት ለማስቀረት ታስቦ የተደረገ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ነበር።

የሕገ መንግሥቱ ረቂቅ የተዘጋጀው በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የንጉሡ የቅርብ አማካሪ በነበሩት በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ መሪነት ነው። ሰነዱ ሲረቀቅ የጃፓንን የሜይጂ ሕገ መንግሥት እንደ ዋና ሞዴል ተጠቅሟል። ጃፓን የራሷን ባሕል እና ዘውዳዊ ሥርዓት ጠብቃ እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደዘመነች ማየታቸው ለዚህ ምርጫ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው። ረቂቁ ከተዘጋጀ በኋላ በታላቅ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ በሚገኘው ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ በንጉሠ ነገሥቱ፣ በታላላቅ መሳፍንት፣ መኳንንት እና የሃይማኖት መሪዎች ፊት ተፈርሞ ጸደቀ።

ሕገ መንግሥቱ ሰባት ምዕራፎች እና 55 አንቀጾች የነበሩት ሲሆን የንጉሠ ነገሥቱን ፍጹም ሥልጣን በሕግ ያረጋገጠ ነበር። ንጉሡ የጦር ኃይሎች የበላይ አዛዥ፣ ሕግ አውጪ፣ ፈራጅ እና አስፈጻሚ ሆነው ተደነገጉ። የንግሥና ሥልጣኑም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የዘር ሐረግ እንዳይወጣ ተደረገ። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ ሁለት ምክር ቤት ፓርላማ ተቋቋመ። የመጀመሪያው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሲሆን አባላቱ በቀጥታ በንጉሡ የሚሾሙ መኳንንት እና መሳፍንት ነበሩ። ሁለተኛው የሕግ መምሪያ ምክር ቤት ሲሆን አባላቱ በመሳፍንቱ እና በአካባቢው መሪዎች የሚመረጡ የተማሩ ወጣቶች እና ባላባቶች ነበሩ። በዚህ መዋቅር ውስጥ የሕዝብ ቀጥተኛ ምርጫ አልነበረም። ከዚህም ሌላ ንጉሡን የሚያማክሩና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሚመሩ ሚኒስትሮች የተሾሙ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው፣ የመንቀሳቀስ መብት እንዳላቸው እና ያለ ሕግ ትዕዛዝ እንደማይታሰሩ ተደነገገ። ሆኖም እነዚህ መብቶች ከንጉሡ  ሥልጣን በታች የተገደቡ ነበሩ።

የአካባቢው መሳፍንት እና መኳንንት የሕገ መንግሥቱ መውጣት የራሳቸውን ታሪካዊ ሥልጣን እና ጥቅም የሚጋፋ አድርገው ተመልክተውት ነበር ሲሉ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1966” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል። ሕገ መንግሥቱ መሳፍንቱ በየግዛታቸው የነበራቸውን የራስ ገዝነት ሥልጣን ቀስ በቀስ እየቀነሰ በአዲስ አበባ ለሚገኘው ማዕከላዊ መንግሥት አሳልፎ የሚሰጥ ሕጋዊ መሠረት የጣለ ሲሆን ይህም ለመሳፍንቱ ትልቅ ስጋት ፈጥሮ ነበር። በተለይም በመሳፍንቱ ወታደራዊ ኃይል ላይ ከባድ መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣ ሲሆን መሳፍንቱ እስከዚያ ዘመን ድረስ በየግዛታቸው ያደራጁትን የግል ጦር የመበተን እና የመከላከያ ኃይሉን በሙሉ ለንጉሠ ነገሥቱ የበላይ አዛዥነት የማስገዛት ግዴታ ጥሎባቸዋል። ይህ የጦር መዋቅር ለውጥ የመሳፍንቱን ወታደራዊ ጉልበት ሙሉ በሙሉ ያዳከመ ሲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ዘመናዊ መደበኛ ጦር በአዲስ አበባ እንዲገነቡ እና የአካባቢ ዓመጾችን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ወታደራዊ የበላይነት እንዲጨብጡ አድርጓቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የንጉሡን ፍጹም ሥልጣን ይበልጥ ለማጠናከር የተወሰዱ ሌሎች በርካታ እርምጃዎች የነበሩ ሲሆን ከሀገር ውስጥ ገቢ የሚሰበሰበውን ግብር በቀጥታ ወደ ማዕከላዊው ካዝና ገቢ የማድረግ አዲስ የፋይናንስ ሥርዓት ተዘርግቶባቸዋል። ይህ የገንዘብ ቁጥጥር መሳፍንቱ የነበራቸውን የኢኮኖሚ አቅም ያሳጣቸው ሲሆን ንጉሠ ነገሥቱ አዳዲስ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት እና ለውጭ ሀገር ትምህርት ወጣቶችን በመላክ ለመንግሥት ታማኝ የሆነ አዲስ የተማረ የቢሮክራሲ ክፍል በመፍጠር የመሳፍንቱን ባሕላዊ የአማካሪነት ሚና ሙሉ በሙሉ የተኩበትን ስልት ያሳያል። መሳፍንቱ ሕገ መንግሥቱ በይፋ በሚታወጅበት ሥነ ሥርዓት ላይ በግንባር ተገኝተው የፈረሙት በፈቃደኝነት ሳይሆን የንጉሡን እያደገ የመጣ ኃይል በመፍራት እና የፖለቲካ መገለል እንዳይደርስባቸው በማሰብ ነበር።

የ1923 ዓ.ም ሕገ መንግሥት መታወጅ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መዋቅር ላይ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ማኅበራዊ ሕይወት፣ በባሕላዊ እሴቶች እና በዜጎች ንቃተ ሕሊና ላይ ከፍተኛ የለውጥ ማዕበል አስከትሏል። ይህ ሰነድ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ አዳዲስ ማኅበራዊ ክስተቶች እንዲፈጠሩ በር የከፈተ ሲሆን በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል የነበረውን ግንኙነትም በአዲስ መልክ ቀርጾታል። ሕገ መንግሥቱ በሀገሪቱ ላይ ያመጣቸው ዋና ዋና የማኅበራዊ ለውጦች የሚከተሉትን ያካትታሉ፤  የዜግነት ጽንሰ ሐሳብ መፈጠር እና የሕግ የበላይነት ባሕል መጀመር ትልቅ ማኅበራዊ ለውጥ ነበር። ከዚያ በፊት የነበረው ማኅበረሰብ ራሱን የሚመለከተው የአካባቢው መሳፍንት ወይም የባላባቱ “ጭሰኛ” ወይም “ተገዢ” አድርጎ ነበር። ሕገ መንግሥቱ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ “የኢትዮጵያ ዜጋ” የሚል ወጥ መዋቅር በመፍጠር ሁሉም ሰው በአንድ የጋራ ሀገራዊ ሕግ ሥር እንዲተዳደር አደረገ። ያለ ሕግ ትዕዛዝ ማንኛውንም ሰው ማሰር መከልከሉ እና የሰዎች የመንቀሳቀስ መብት መከበሩ በማኅበረሰቡ ውስጥ የግል ነፃነት እና የደኅንነት ስሜት እንዲያድግ ረድቷል። የባርነት ሥርዓት እንዲዳከም እና ማኅበራዊ እኩልነት እንዲሰፍን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ተጥሏል። በወቅቱ በኢትዮጵያ በባሕል ደረጃ ሥር ሰዶ የነበረውን የባሪያ ንግድ እና የባርነት ሥርዓት ለማስቀረት ንጉሠ ነገሥቱ የዓለም መንግሥታት ማኅበር የሰጣቸውን ግዴታ ለመወጣት ይህንን ሕገ መንግሥት እንደ መሣሪያ ተጠቅመውበታል። ሁሉም ዜጋ በሕግ ፊት እኩል መሆኑ መታወጁ የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር ከፍ ያደረገ ሲሆን ዝቅተኛ ማኅበራዊ ደረጃ ይሰጣቸው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀስ በቀስ ሰብዓዊ መብቶቻቸውን እንዲያውቁ እና እንዲጠይቁ በር ከፍቷል።

አዲስ የተማረ ማኅበረሰብ መፈጠር እና የባሕላዊው ባላባት ተሰሚነት መቀነስ ሌላው ማኅበራዊ ለውጥ ነበር። ንጉሡ ሕገ መንግሥቱን ተፈጻሚ ለማድረግ ታማኝ የቢሮክራሲ ኃይል ስለሚያስፈልጋቸው ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በስፋት ማስፋፋት ጀመሩ። ይህም በትምህርታቸው እና በእውቀታቸው ብቻ ወደ ሥልጣን እና ማኅበራዊ ክብር የሚወጡ ወጣቶች እንዲፈጠሩ አደረገ። ይህ ክስተት ዘር እና የቤተሰብ ሐረግን ብቻ አይቶ ክብር እና ሥልጣን ይሰጥ የነበረውን የፊውዳል ማኅበራዊ የደረጃ ሥርዓት በእጅጉ የተናቀጠና የተዳከመ እንዲሆን አድርጎታል። የከተሞች መስፋፋት እና ማኅበራዊ መስተጋብር ማደግም የዚህ ሂደት ውጤት ነው። ማዕከላዊ መንግሥቱ ሲጠናከር እና የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ፍርድ ቤቶች በአዲስ አበባ እና በትላልቅ የክልል ከተሞች ሲቋቋሙ በርካታ ሕዝብ ከገጠር ወደ ከተማ መፍለስ ጀመረ። ይህ ፍልሰት ከተለያዩ አካባቢዎችና ብሔረሰቦች የመጡ ሰዎች በአንድ ላይ እንዲኖሩ፣ እንዲነግዱ እና አዳዲስ ዘመናዊ ባሕሎችን እንዲላመዱ በማድረግ ጠባብ የአካባቢተኝነት ስሜት እንዲቀንስ እና ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር አድርጓል። የፍርድ ሥርዓቱ ዘመናዊ መሆን በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረውን የደም መመለስ እና የበቀል ባሕል አስቀርቷል። ቀደም ሲል በአካባቢ መሳፍንት እና በባሕላዊ ዳኞች ይሰጥ የነበረው ፍርድ ወጥ ባለመሆኑ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ እና የእርስ በርስ ግጭት ይፈጥር ነበር። ሕገ መንግሥቱ ግን የተደራጀ የፍርድ ቤት መዋቅር እንዲዘረጋ መንገድ በመክፈቱ ሕዝቡ በቀልን ትቶ ጉዳዩን በሕግ አግባብ የመፍታት እና የመንግሥትን የዳኝነት ሥርዓት የማመን ማኅበራዊ ልምድ እንዲያዳብር አድርጎታል።

የ1923 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ፍጹም ዲሞክራሲያዊ ባይሆንም ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር ለማምጣት የተደረገ ትልቅ የታሪክ እርምጃ ነበር። ይህ ሕገ መንግሥት በ1928 ዓ.ም በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ ቢቆይም ከነፃነት በኋላ በ1948 ዓ.ም በተሻሻለው ሕገ መንግሥት እስከተተካበት ጊዜ ድረስ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ሆኖ አገልግሏል።

ሳምንቱ በታሪክ

የልጅ ሚካኤል እምሩ ሹመት

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ከአብዮቱ ማዕበል በኋላ በለቀቁት ቦታ ሐምሌ 15 ቀን 1966 ዓ.ም ልጅ ሚካኤል ዕምሩ ተሾሙ። የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ቢሆኑም ተራማጅ እና “መሬት ላራሹን” የሚደግፉ በመሆናቸው በተማሪዎች እና በወታደሮች ዘንድ ተቀባይነት ነበራቸው። እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ ሕገ መንግሥታዊ ንጉሥ ሥርዓት የሚቀይር ረቂቅ አቅርበው ነበር።

የልጅ ሚካኤል ካቢኔ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ቢሞክርም እውነተኛው ሥልጣን ወደ ደርግ ኮሚቴ እጅ እየገባ በመምጣቱ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው የደርግን ትዕዛዝ በማስፈጸም የተገደበ ነበር። መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ሲወርዱ የሁለት ወሩ የልጅ ሚካኤል የሥልጣን ዘመን አብቅቶ ነበር፤ በኋላም ከእስር እና ግድያ በመዳን  ሀገራቸውን አገልግለዋል።

ምንጭ፦ የኢትዬጵያ አቢዬት – በአንዳርጋቸው ጥሩነህ (ዶ/ር)

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 13  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here