ከሀገር ተሞክሮ ምን እንማራለን?

0
193

ሀገራት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ዩኔስኮ ከ2022 እስከ 2026 ባሉ ዓመታት ያወጣቸውን ሪፖርቶችና የጥናት ውጤቶች ስንመለከት የተለያዩ ሃገራት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና ለማስከበር ለዘርፉ የሰጡት  ትኩረት ከፍተኛ ስለመሆኑ  ያመላክታል፡፡ የትምህርትን ጥራት አስጠብቆ ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና ለዘርፉ የሚበጀተው የገንዘብ መጠንም ድርሻቸው የጎላ እንደሆነ ይታመናል ፡፡

የፈተና ቁጥጥርን በጥብቅ ስርአት ተግብረው የትምህርት ጥራትን ያስጠበቁ በርካታ ሀገራት መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከእነዚህ ሃገራት መካከል ቻይና፣ደቡብ ኮርያ እና ሲሸልስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ቻይና

የሩቅ ምሥራቋ ቻይና ለፈተና የምትሰጠው ትኩረት እጅግ ጠንከር ያለ ነው፡፡  በዚህም በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።  ፈተናን በቻይና መምህር ብቻ አይፈትንም፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎትም ሌላኛው ፈታኝ ነው፡፡  በፈተና ጊዜ በአካባቢው ምንም አይነት  ረብሻ እንዲኖር አይፈለግም፤ አምቡላንስና ሌሎችም መኪኖች ለተማሪዎች አገልግሎት ለመስጠት በተጠንቀቅ ይቆማሉ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ማዕከል አንዱ አካል የሆነው የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የትምህርት እቅድ ኢንስቲትዩት (IIEP-UNESCO) እና ተያያዥ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጥብቅ የፈተና ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት በትምህርት ጥራት፣ በአካዳሚክ ታማኝነት እና በሃገር አቀፍ የሰው ኃይል ብቃት ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ጥቅም አለው። የፈተና ማጭበርበርን (Exam Malpractice) መከላከል የትምህርት ስርዓቱን ተዓማኒነት ለመጠበቅም ወሳኝ መሆኑን ጥናቶቹ ያሰምሩበታል።

ቻይና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና(ጋኦካኦ) ላይ እጅግ ጥብቅ ቁጥጥር የምታደርገው  የዜጎችን ማህበራዊ እኩልነትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ፣ ፈተናው የአንድን ተማሪ የወደፊት ህይወት ሙሉ በሙሉ የሚወስን በመሆኑ እና የትምህርት ስርዓቱን ታማኝነት በመጠበቅ ማህበራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ነው፡፡ የጋኦካኦ ፈተና በቻይና የብሄራዊ ደህንነትን ያህል ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል።

በቻይና በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ለጋኦካኦ ፈተና ይቀመጣሉ፡፡ ለአብነት የቅርብ አመታትን ተፈታኞች ብንመለከት በ2024 ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እንዲሁም በ2025 ደግሞ ከ13 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል፡፡ ቻይና ይህንን የጋኦካኦ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናን ፍፁም እምነት የሚጣልበት፣ ፍትሃዊ እና ከስርቆት የጸዳ ለማድረግ እጅግ በጣም ጥብቅ የሆኑ የቴክኖሎጂ፣ የህግ እና የሎጂስቲክስ ስልቶችን ትከተላለች።

ወታደርን ጨምሮ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያዎች የፈተናውን ሚስጥራዊነት ለመጠበቅ አገልግሎት ላይ የሚውሉበት ነው፡፡ የፈተና ሚስጥራዊነቱም ከፈተና ዝግጅትና ከህትመት ይጀምራል፡፡

የጋኦካኦ የፈተና ወረቀቶች የሚታተሙት ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ነው።

በህትመት የሚሳተፉ የህትመት ባለሙያዎችም ከፍተኛ የኋላ ታሪክ ፍተሻ እና ሚስጥር የመጠበቅ ስልጠና የማለፍ ግዴታ አለባቸው፡፡ እነዚህ የህትመት ሰራተኞች ህትመቱ በሚከናወንበት ቦታ ውስጥ ለሳምንታት ከማንም ጋር እንዳይገናኙ ስልኮች እና ማንኛቸውም የኢንተርኔት ግንኙነት ካላቸው መሣሪያዎች በሙሉ ርቀወ  እንዲቆዩ ይደረጋል። ከህትመት መጠናቀቅ በኋላም ቢሆን የህትመት ሰራተኞቹ ፈተናው በመላው ሀገሪቱ ተጠናቆ እስኪያልቅ ድረስ ከተፈቀደላቸው ቦታ መውጣት ፈጽሞ አይፈቀድላቸውም።

ከግቢው የሚወጣ ማንኛውም ዓይነት ቆሻሻ እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ ፍተሻ ይደረግበታል። የህትመት ክፍሎችም 24 ሰዓት በደህንነት ካሜራ የሚጠበቁ ሲሆን፣ ካሜራዎችም እንቅስቃሴን የሚመዘግቡ ሴንሰሮች የተገጠሙባቸው ናቸው።

በጥብቅ ቁጥጥር ተዘጋጅቶ የታተመው የጋኦካኦ ፈተና ወደ ፈተና ጣቢያ ሲጓጓዝም ከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ የፈተና ወረቀቶች በታጠቁ የፖሊስ እና የልዩ ሃይል አባላት ታጅበው፣ የጂፒኤስ መከታተያ በተገጠመላቸው የጦር መኪኖች ወደ ፈተና ጣቢያዎች ይጓጓዛሉ። ከወታደሮች ባሻገር የፈተና ወረቀቶች ታትመው ካለቁ በኋላ፣ በልዩ ሁኔታ በታሸጉ  የፖስት የጭነት መኪናዎች ይጫናሉ።

መኪኖቹም በልዩ ፖሊስ እና ኮማንዶዎች ታጅበው ወደ ፈተና ጣቢያዎች ይጓዛሉ። በጉዞ ላይም  እያንዳንዱ የፈተና ሳጥን እና መኪና በሳተላይት የጂፒኤስ ክትትል ይደረግበታል፡፡ ፈተና የጫነ መኪና ከመንገዱ ጥቂት ሜትሮችን ወጣ ካለ መኪናው ላይ የተገጠመው ጅፒኤስ በቀጥታ ለቤጂንግ ማዕከላዊ ቁጥጥር ክፍል ማስጠንቀቂያ ይላካል።

ተማሪዎች ወደ ፈተና ጣቢያ ከመግባታቸው በፊት እነሱን ተክቶ የሚፈተንላቸው ሰው እንዳያመጡ ለመከላከል የፊት ገጽታ፣ የዐይን ብሌን እና የጣት አሻራ ፍተሻ ይደረጋል። ይህንንም ፍተሻ አልፈው ሌላ ፍተሻ ይጠብቃቸዋል፡፡ ወደ መፈተኛ ክፍሉ ከመግባታቸው በፊት ሰዓት፣ ስልክ፣ ጌጣጌጥ እና ማንኛውም የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ አለመያዛቸው በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ የታገዘ ፍተሻ ይደረጋል፡፡

ቻይና ለጋኦካኦ ፈተና በእያንዳንዱ የፈተና ጣቢያ ዙሪያ የሞባይል ኔትወርክ ዋይፋይ እና የብሉቱዝ ሞገዶች እንዳይሰሩ የሚከላክሉ ኃይለኛ የሲግናል ማፈኛዎች ትጠቀማለች፡፡ ቁጥጥሩ በዚህም አይቆምም፡፡ ከመፈተኛ ጣቢያዎች ውጭ ልዩ የሬዲዮ ሞገድ መቆጣጠሪያ መኪኖችን ታቆማለች። እነዚህ መኪኖች ወደ ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ የሚላኩ ያልተለመዱ የሬዲዮ ሞገዶችን ወይም በሚስጥር ማዳመጫዎች የሚተላለፉ ድምፆችን ይከታተላሉ።

እያንዳንዱ የፈተና ክፍል በከፍተኛ ጥራት በሚቀርጹ ካሜራዎች የተደራጀ ነው። እነዚህ ካሜራዎች በቀጥታ ከክልላዊ እና ከሀገራዊ የፈተና መቆጣጠሪያ ማዕከላት ጋር የተገናኙ ናቸው። እነዚህ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ ካሜራዎች ተማሪዎች በፈተና ሰዓት ያልተለመደ የሰውነት እንቅስቃሴ ካሳዩ በክፍል ውስጥ ላሉ ፈታኞች ፈጣን ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ። በዚህ ሁሉ ፍተሻ አልፎም ፈተናን ሲያጭበረብር የተገኘ ተማሪ እስከ 7 አመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድበት ይችላል፡፡ በዚህ ብቻም አያበቃም ሲኮርጅ የተገኘ ተማሪ የወደፊት የትምህርት እና የሥራ ዕድል ሙሉ በሙሉ እንዲበላሽ ያደርጋል።

አስቀድመን ባነሳናቸው የፍተሻ መንገዶች ያለፉት ተፈታኝ ተማሪዎች ትኩረታቸው እንዳይከፋፈል በፈተና ጣቢያዎች ዙሪያ ያሉ መንገዶች በሙሉ ይዘጋሉ። መኪናዎች የጥሩምባ ድምፅ እንዳያሰሙ ይከለከላሉ፣ የኮንስትራክሽን ስራዎች ይቆማሉ፣ አልፎ ተርፎም በአቅራቢያ ያሉ የንግድ ቦታዎች ድምፅ እንዳያሰሙ ይታገዳሉ። የፖሊስ መኪናዎች እና አምቡላንሶች ለማንኛውም ድንገተኛ አደጋ በተጠንቀቅ ይቆማሉ።

የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በ2025 የፈረንጆች የዘመን አቆጣጠር ባጠናው “How the Gaokao Shapes Chaina” በተሰኜ ጥናት ላለፉት አስርት አመታት ለተመዘገበው የቻይና አስደናቂ የኢኮኖሚ እድገት አንድ ሶስተኛ ያህሉን አስተዋፅኦ ያበረከተው በዚህ የፈተና ስርዓት የበለፀገው የሀገሪቱ ትምህርት እንደሆነ ያሳያል፡፡

ቻይና የፈተና ስርዓቷን እንዲህ ጥብቅ ማድረጓ በሀገሪቱ ፍትሃዊ ውድድር እንዲሰፍን አስችሏል፡፡ ምንም እንኳን ፈተናው ከባድና አስጨናቂ ቢሆንም በቻይና ማኅበረሰብ ዘንድ እጅግ ፍትሃዊ እና ግልጽ የውድድር መድረክ ተደርጎ ይወሰዳል።

አንድ ከዝቅተኛ ቤተሰብ የተገኘ ተማሪ በችሎታው ብቻ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ የሚችልበት ኢኮኖሚያዊ መሰላል በመሆን ያገለግላል። ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችም የተሻለ ክፍያና የሥራ ዕድል ያገኛሉ። የመንግስት ባለስልጣናትም በዝምድናና በሌሎች ጥቅሞች የሚያስቀጥሩት ሰው እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ይህም ጠንካራ የስራ ባህልና የስራ ስነምግባር እንዲኖር አግዟል፡፡ ለዚህ ፈተና ለዓመታት ሌት ተቀን መዘጋጀት በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ዲሲፕሊን፣  የጊዜ አጠቃቀም ክህሎት እና በከባድ ጫና ውስጥ የመሥራት ብቃትን ስለሚያሳድግ በዚህ ስርዓት የሚወጡ ምሩቃን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጠንካራ የሥራ ባህላቸው፣ በታማኝነታቸው እና በቴክኒክ ብቃታቸው እጅግ ተፈላጊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የቻይና ጥብቅ የፈተና ቁጥጥር ስርዓት የሀገሪቱን ፖለቲካዊና የመንግስት አስተዳደር የተረጋጋ እንዲሆን ማስቻሉን የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ውጤት ያሳያል፡፡

የመንግሥትና የግል ኩባንያዎች ብቁ መሪዎችንና ባለሙያዎችን የሚመርጡት በዚህ ስርዓት በወጣ ውጤት ላይ ተመመስርተው በመሆኑ የሙስና እና የዘመድ አምላኪነት ስጋትን ቀንሷል፡፡ ይህም ዜጎች ስኬትም ሆነ ውድቀት በራሳቸው ጥረት ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንዲቀበሉና፣ በስርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ እንዲሆን በማድረግ ሀገራዊ መረጋጋትን በማጠናከር አግዟል።

ደቡብ ኮሪያ

ሌላኛዋ ጥብቅ የፈተና ቁጥጥር ስርዓት ያላት ሀገር ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ናት፡፡ ደቡብ ኮሪያ ሱነንግ ለተሰኜው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ልዩ ትኩረት ትሰጣለች፡፡ በዚህ ፈተና ተማሪዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት የትኛውም ዩኒቨርሲቲ መግባት እንደሚችሉና ለወደፊት የስራ ዕድል  ወሳኝ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የፈተና ደህንነትን ለመቆጣጠርም ፈተናውን የሚያወጡ መምህራን ፈተናው እስከሚጠናቀቅበት ቀን ድረስ ስልክ፣ ላፕቶፕና ሌሎችም የግንኙነት መሳሪያዎችን እንዳይዙ ተደርገው  ምስጢራዊ በሆነ ቦታ ከግንኙነት ርቀው እንዲቆዩ ታደርጋለች፡፡

ቁጥጥሩም በዚህ ብቻ አያበቃም ፈታኝ መምህራን የሚጥሉት ቆሻሻ ሳይቀር ፍተሻ ይደረግበታል፡፡ የሚጥሉት  የወረቀት ቁርጥራጭ ምንም አይነት ኮድ ወይም መረጃ እንዳይወጣበት በጥብቅ ይፈተሻል። ፈተናው የተማሪዎችን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስን ስለሆነ ምንም አይነት ስህተት እንዳይፈጠርና ያለአግባብ የሚጎዳም ሆነ የሚጠቀም ተማሪ እንዳይኖር እንጅ፡፡

ሲሸልስ

ለፈተና ጥራት ጥብቅ ቁጥጥር ከሚያረድጉት ሃገራት መካከልም  ሲሸልስም ትጠቀሳለች። ሲሸልስም እንደ ቻይና እና ደቡብ ኮርያ ሁሉ  የፈተና ፍትሃዊነትን ለማስጠበቅ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ጥብቅ የሆኑ የፈተና ክትትልና አሰጣጥ ደንቦችን ተግባራዊ ታደርጋለች፡፡

ሲሸልስ ቁጥጥር ማድረጓ ብቻ አይደለም፡፡ የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናዎች በእንግሊዙ ካምብሪጅ ዩኒቨረሲቲ እንዲዘጋጁ ማድረጉ ነው፡፡ የሲሸልስ ተማሪዎች በፈተና ወቅት ለፈተና ከተፈቀዱ ቁሳቁሶች ውጭ ማንኛውንም መጻሕፍት፣ ወረቀቶች ወይም ከፈተና ጋር ያልተያያዙ ቁሳቁሶችን ይዘው መግባት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

ከእነዚህ ሀገራት የትምህርትና የፈተና ስርዓት በርካታ ቁምነገሮችን መውሰድ ይቻላል፡፡ የትምህርት ስርዓቱን በማሻሻል የፈተና ቁጥጥር ስርዓቱንም ከመጀመሪያው የክፍል ደረጃ ጀምሮ ጥብቅ ቁጥጥር ቢደረግበት  የኢትዮጵያ የትምህርት ስርኣት በሂደት መሻሻሎችን ለማሳየት ያስችለዋል፡፡

አማርኛ በአማርኛ

ጠንካራ –  የማይሸነፍ – ብርቱ

ታማኝ – ሀቀኛ- ተስማሚ

በሸታ – ደዌ – ጤና ማጣት

መረዳዳት – መተባበር – መተጋገዝ

 

( አስፋው ሙቀት)

በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here