ጋዜጠኛው እና ቋንቋው

0
43

ከየትኛውም የብዙኃን መገናኛ ዓይነት በአመዛኙ የምከታተለው ሬዲዮ ነው። በዚህ ከ20 ዓመት የማያንስ ልምድ አለኝ።  በዚህ ልምዴም ጋዜጠኛው ዘገባ የሚሠራበት ቋንቋ ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱን ተገንዝቤአለሁ፡፡ ይህ ለምን ኾነ?

በግሌ መልስ መስሎ የታየኝ መሰናዶዎችን ጊዜ ወስዶ አጥርቶ መሥራቱ ጊዜ ስለሚወስድ በስልክ የተገኘውን ለሥርጭት ማብቃትና ተጠያቂውን በአካል አቅርቦ ያለውን ይበል በሚል በቀላሉ መገላገል መለመዱ ይመስለኛል። ይህ ልማድ ደግሞ ቋንቋውን እየጎዳው ይገኛል። የቀጥታ ሥርጭት ረቂቅ ጽሑፍ ጥያቄዎች ይዘጋጁለት እንደሁ እንጂ ሙሉ ዝግጅቱ ረቂቅ ተጽፎለት ስለማይታረም እንዲሁም መረጃው በድምጽ ብቻ ያለ ስለሆነ ደጋግሞ ለማንበብ ስለማይመች በወሳኝ የቃለ መጠይቅ ክፍሉ ላይ የቋንቋ አጠቃቀም ችግር ቢኖር ተቆርጦ አይጣልም። ይህ ደግሞ ለአድማጩ ጆሮ ይጎረብጣል። በተደጋጋሚ ከሚሰሙ የጋዜጠኞች የቃላት አጠቃቀም ችግሮች መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው አንቱ እና አንተ የሚሉትን ቃላት መቀላቀል ነው።  ለምሳሌ፣ “ሥራችንን በአግባቡ እየፈጸምን ነው ሲሉ አቶ እንትና ሀሳቡን ገልጿል” የሚለው አዘጋገብ ያወዛግባል።

ሌላኛው የአገላለጽ ግድፈት ደግሞ የቃል ድግግሞሽ ነው። “እንትና ከእንትና ጋር ከባድ ፉክክር ይጠብቀዋል ተብሎ ይጠበ ቃል”በማለት የቃል ድሪቶ መጠቀም ተለምዷል። ይሄ መስተካከል አለበት፡፡

“የሚቀጥለውን መሰናዶ ሻሺቱ ነው የምታቀርበው”  የሚለው አገላለጽ ከጠራ ጾታዊ አገላለጽ የራቀ ነው። “ሴቷ ነው የምታቀርበው” ማለት ከተቻለ አበበ እና ከበደ ነው የሚያቀርቡት ማለት ሊቻል ነው ማለት ነው። ስህተቱ ታርሞ  አበበ እና ከበደ ናቸው የሚያቀርቡት መባል ነው ያለበት በሚለው ከተስማማን ሻሺቱ ናት የምታቀርበው ነው መባል ያለበት።

አንድን ቋንቋ የሚጠቀም ሰው ከስም በፊት ምን እንደሚቀድም፣ ከስም በኋላ ምን እንደሚከተል ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል። ትክክለኛው አሰያየም ኤፍ ኤም   ጣና   ወይስ  ጣና  ኤፍ ኤም ? ኤፍ ኤም የሚለው የጣቢያው ስም ሲሆን የቦታው ስም ኤፍ ኤም  የሚለውን መጠሪያ ቃል ገላጭ ነው። ለምሳሌ፣ ኤፍ ኤም   ጣና  109.9 በሚለው አገላለጽ ውስጥ ቁጥሩ የሚያመለክተው ጣቢያውን ነው ካልን ታዲያ ለምንድን ነው ኤፍ ኤም  በሚለው እና በሜጋሄርዙ መካከል የቦታ ስም የምናስገባው? ከዚህ ይልቅ  ጣና  ኤፍ ኤም 109.9 ብንለው አይሻልም ትላላችሁ?  ኤፍ ኤም   ጣና  ማለት ከተቻለ ትምህርት ቤት ጣና ሐይቅ ማለት ይቻላል ማለት ነው። አይ እንደዚህ አይባልም ጣና ሐይቅ ት/ቤት ነው የሚባለው ካላችሁኝ ደግሞ እንግዳውስ እናንተም  ጣና  ኤፍ ኤም  በሉ የሚለው ምላሼ ይሆናል።

የጋዜጠኝነት ሙያ ራሱ የሚቀዳው ከጥበብ ነው ብየ አምናለሁ። ጋዜጠኝነት እና ኪነ ጥበብ መዋያቸውም ማደሪያቸውም አንድ ነው ብየ አስባለሁ። አንዱ ባለበት ሌላው የሚጠፋ አይመስለኝም። ለዚህ ነው ጋዜጠኛ ሲያረጅ ደራሲ እንዲሆን የሚጠበቀው።

ጋዜጠኛው ቃለ መጠይቅ ያደረገለትን ሰው አላስፈላጊ ንግግር በቀጥታ መውሰድ የለበትም። በጽሑፍ የሚዘጋጀውን መሰናዶ ያህል ፍጹም ጥራት ያለው ንግግር እንዲያደርግ ባይጠበቅም ሙያው ጋዜጠኝነት እንደመሆኑ መጠን የጋዜጠኛው ቋንቋ እንግዶች ከሚናገሩት በእጅጉ የተሻለ አገላለጽ ሊኖረው ይገባል።

ከዚህ በፊት ክፍት የጋዜጠኝነት ሥራ ማስታወቂያ ሲወጣ “ከአካባቢ ዘየ አነጋገር የጸዳ የቋንቋ ክህሎት ያለው” የሚለው እንደ አንድ መስፈርት ሲጠቀስ ሰምተን እናውቃለን። አሁን አሁን ግን ይህ መስፈርት የቀረ ይመስላል። የአንድን አካባቢ ዘየ ብዙኃን መገናኛዎች ላይ በገፍ እየሰማን ነው። ባነነ የሚለውን የአራዳ ቃል ብዙኃን መገናኛዎች ላይ መስማት በቋንቋ እንደመራቀቅ ተቆጥሮ እንደልብ ሲነገር እየሰማን ነው። “ትንሽ ይከብዳል” አለ የዘመኑ ጋዜጠኛ። ትንሽ ብሎ ከባድ አያስቅም? “ትንሽ ያሳዝናል” ማለትስ ትንሽ አያሳዝንም? ሊቆቹ እነደበበ ሰይፉ፤ ለአማርኛ ቋንቋ ተጨማሪ ቃላትን እንዳላበረከቱበት የብዙኃን መገናኛው በዘየ እንዴት ይወረሳል? ለምሳሌ ወንድሜ መጥቶ ለማለት መጦ፣ እህቴ መጥታ ለማለት መጣ፣ ይሄኛውማ የቃላት ብቻ ሳይሆን የጾታ አገላለጽ ችግርም ያስከትላል። ከቤት ወጥቶ ለማለት ወጦ እየተባለ በሕዝብ ብዙኃን መገናኛዎች በኩራት ሲነገር መስማት እየተዘወተረ ነው።

ከእኔ ችሎት አማርኛ እና እንግሊዝኛ ተከሠው ቢቀርቡልኝ በነባራዊ እውነታ (ፋክት) እንግሊዘኛን ዋሾ ብየ እቀጣዋለሁ። ምክንያቱም እንግሊዘኛ የሚናገረው እና የሚጽፈው ይለያያልና። አማርኛ ሦስት ፊደል ከጻፈ ሦስቱንም በድምጽ ያስደምጣል። እንግሊዘኛ አምስት ፊደል ጽፎ የሚናገረው ሁለት ፊደላትን ብቻ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ book ተብሎ ሲጻፍ አራት የእንግሊዘኛ ፊደላት ሲኖሩት በድምጽ ሲነበብ ግን “ቡ” እና “ክ” የሚሉ ሁለት ፊደላት ብቻ ናቸው። ወደዚህ ጣጣ የወሰደኝ ዘመነኞቹ አማርኛን ሲጻፍ እና ሲነበብ የተለያየ ስለሚያስመስሉት ነው። ወጥቶ በሚል የሚጻፈውን ወጦ ብሎ ከተናገረው አማርኛ እንደ እንግሊዘኛ በድምጽ እና በጽሑፍ ሊለያይ ከጊዜያት በኋላም ይሄኛው ቃል ሲጻፍ ፊደሉ እንዴት ነበር? ብለን እንድንጠይቅ ሊያደርጉን ነው የሚል ስጋት ስላደረብኝ ነው። በዚህ ዘመን ብዙ የቋንቋ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ደራሲዎች አሉን፡፡ ነገር ግን ለአዳዲስ ነገሮች፣ እቃወች፣ ሁኔታዎች የአማርኛ ስያሜ ሲሰጡ አይስተዋልም። ሆነ ተብሎ ታስቦበት የአንድን አካባቢ ወግ፣ ባህል፣ አነጋገር እና አኗኗር ለመግለጽ ታስቦ የተዘጋጀ የሬዲዮ መሰናዶ ወይም መጽሐፍ ካልሆነ በቀር በብዙኃን መገናኛ  የሚነገር፣በመጽሐፍ የሚቀርብ ጉዳይ ሥነ-ጽሑፋዊ ውበቱን ጠብቆ መቅረብ እንዳለበት ነው የሚገባኝ። በጽሞና ለአንድ ሰዓት ሬዲዮ ብታዳምጡ ለ፣ በ፣ ከ፣ የ፣ ን፣ የሚሉትን ፊደላት ጨምሮ ቅድመ እና ድህረ-ቅጥያወች በትክክል በቦታቸው ተሰካክተው አትሰሟቸውም።

“ፕሮግራም” የሚለው የእንግሊዘኛ ቃልማ አስገዳጅ እስኪመስል ድረስ በሁሉም ብዙኃን መገናኛዎች በሚያስብል መጠን ነው ሲጠቀሙት የሚሰማው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተወልዶ ከፌስቡክ የተረፈ ሰዓት ኑሮት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን መከታተል የጀመረ ታዳሚ “ፕሮግራም” የሚለው ቃል አማርኛ ነው  ብሎ ሊከራከር ይችላል። በአማርኛ ሲናገር ያጋጠመውን ስህተት አለማረም ነውርነቱ  የመቅረቱን ያክል በየንግግሩ መካከል እንግሊዝኛ መቀላቀል የብቃት መለኪያ የተደረገ ይመስላል።

አንድ አዘውትሬ የምሰማው የሬዲዮ ጣቢያ አዳዲስ ጋዜጠኞችን ባንድ ጊዜ ቀጠረና ሦስት አዳዲስ ጋዜጠኞች ባንድ ነባር ጋዜጠኛ ሊጠየቁ መነጋገሪያ  ያዙ። ከሦስቱ አንዱን አውቀው ስለነበር ከመሰናዶው በኋላ ደውየ “እንኳን ደስ አለህ!” አልኩት። እሱም “እንዴት ነው የምለምደው ይመስልሀል?” አለኝ። እኔም “ጥሩ ጋዜጠኛ ይወጣሀል” ስለው “ኧረ ባክህ!” ብሎ ሊግደረደር ሞከረ። እኔም “እውነቴን ነው ብዙ ጋዜጠኞችን እኮ አሰልጥነናል፤ መገመት አይከብደንም” ስለው በጣም ሳቀ።

ቀጣዩ ትችቴ በሁለት ጋዜጠኞች ስለሚቀርቡ መሰናዶዎች ነው።  ሁለት  ጋዜጠኞች እጅግ በተናበበ መልኩ ዝግጅቶችን ሲመሩ አንድ ጋዜጠኛ ብቻውን ከሚያቀርበው የበለጠ መሳጭ ነው። ሆኖም በእኔ አስተውሎት ይህ አቀራረብ ሳቢነቱ እየቀነሰ መጥቶብኛል። አንዱ የተናገረውን ሌላኛው ከመድገም ባለፈ መጀመሪያ ለቀረበው ንግግር ማሳመሪያ ወይም ማሳረጊያ ሲሰጥ አይታይም። አንደኛው ጋዜጠኛ “አድማጮቻችን ቀጣዩን ሙዚቃ ሰምተን እንመለሳለን” ሲል ሌላኛው “አወ ልክ ብለሀል፤ አድማጮቻችን ቀጣዩን ሙዚቃ ሰምተን እንመለሳለን” ይላል። ይህ አልበቃ ብሎት ባልደረባው “ለዕለቱ የያዝናቸውን ፕሮግራሞች ቀጥሎ ይቀርባል” በማለት አንድ እና ብዙ አምታቶ ሲናገር ደግሞ በዝምታ ያልፈዋል።

“ለአለፉት አንድ ዓመታት” ሲል ከአጠገቡ ያሉት ሰዎች በዝምታ ማለፋቸው ይገርመኛል። “መስከረም 2 ለዕለተ ሮብ 2018 ዓ.ም የተዘጋጀውን ዜና ይዘን ቀርበናል” በማለት ዋዜማ እና ማግስት አዛብቶ ከዓርብ እስከ አልታወቀው ሮብ ድረስ ከዕድሜያችን ላይ ሲቆርጥ፣ ጥቅምት 8 ላይ ሁኖ ትናንትና ጥር 7 ቀን ብሎ ከዕድሜያችን ላይ 90 ቀናትን ሲዘግን ከአጠገቡ ሁኖ ዝም ያለ ባልደረባ ምናችን ሲወሰድ ሊነግረን ነው? አንዳንዴማ የቋንቋ መሳሳት አያስነውርም የሚል ያዘጋገብ መመሪያ አለ እንዴ እስክል ድረስ ያስገርመኛል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ጋዜጠኛው ተሳስቶ የአካባቢ ዘየ ሲናገር ወይም ቃላትን ሲያዛባ የሥርጭት ባለሙያዎች ጭምር ማስተካከያ ይሰጡ ነበር። ጋዜጠኞቹ ራሳቸውም ቢሆኑ ሲሳሳቱ አድማጮቻቸውን ይቅርታ ጠይቀው  ስህተቱን እንደገና ያስተካክሉ ነበር። የአሁኖቹ ጋዜጠኞች ስንቱን አስተካክለን እንዘልቀዋለን በሚል ይመስላል በስህተት የተናገሩትን እንደገና ለማረም ጥረት አያደርጉም። የበፊቶቹ ጋዜጠኞች እንደሳል፣ ንጥሻ የመሳሰሉ የተፈጥሮ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው  ይቅርታ ብለው ነበር ሥራቸውን የሚጀምሩት። አሁን ላይ ሁሉም በ”ኦንላይን” ሁኗል። እንግሊዝኛ ቀላቀልኩ እንዴ?

“አንድ ገበሬ ከሩቅ ክፍለ ሀገር ተነስቶ ጉዳይ ሊያስፈጽም ወደ አዲስ አበባ ይሄዳል። መመለሻ ገንዘብ ስላልነበረው የተሻለው አማራጭ ጃንሆይን መለመን እንደሆነ አመነ። ንጉሡ ከሚወጡበትና ከሚገቡበት መንገድ አጠገብ ካለ ከፍታ ቦታ ላይ ሁኖ “በወደቀችው ባንዲራ አቤቱታየን ስሙኝ!” ሲል ይጮሀል። ንጉሡም መኪናቸውን አስቁመው ሲሰሙት ገበሬው ያጋጠመውን ተናገረ። ንጉሡም “ታዲያ አሁንስ እየለመንክ የማትሄድ?” ሲሉት “ጃንሆይ አሁንስ ምን እያደረግኩ ነው?” አላቸው ይባላል።

የሥርጭት ብዙኃን መገናኛው በየሰዓቱ “ሀሳብ አስተያየት ስጡኝ!” እያለ ጥሪ እያደረገ አይደል? እኔስ አሁን ምን እያደረግኩ ነው?

(ዳኛ ኃይለማርያም ፍስሀ)

በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here