“ግራህን ሲመታህ ቀኝህን ስጠው” የሚባለውን ሀሳብ የሚቀበሉት አሉ። እኔ ግን አልቀበለውም።
ይህንን ሀሳብ ለመቀበል ቀላል ሊመስል ይችላል። በተግባር መከወን ግን ሌላው ፈተና ነው። ዓለም ትሕትናን ሳይሆን ኀይልን ነው የምትሸልመው።
ይህን ሀሳብ ለመቀበል ጠንካራ አማኝ መሆን ያስፈልጋል። ሁኔታ፣ጊዜ እና ቦታም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት። ይህ ራስን ዝቅ ማድረግ ለሞራል እና ግብረገብነት የሚሰበክ ቢሆንም በቀጥታ ተቀብሎ ማስተናገድ በዓለም ሽቅድምድም ያስቀድማል።
ሁሉ ራሱን ለማውጣት በሚሮጥበት፣ ፉክክር፣ ሽኩቻ፣ ቅናት፣ ሴራ፣ እና መጠላለፍ በበዛበት ዓለም ውስጥ እንዴት ነው ግራ ፊታችንን ሲመቱን ቀኛችንንም ድገሙት ማለት የምንችለው?
ዛሬ ስለ ይቅርታ ነው መጻፍ የፈለግሁት። በብዙ አኗኗራችን ውስጥ ያለ ሀሳብ ነው። ብዙ የተወራለት ነገር ግን የሕይወትን ኮምፓስ በብዙ መልኩ የለወጠ ቃል ነው።
የማህበረሰባችንን እሴትና እውነት ከምናገኝባቸው የጥበብ ውክልናዎች መካከል ሙዚቃ ይቅርታን ደጋግማ አዚማለች።
ጥበብ ለማህበራዊ ለውጥ መዋል አለባት በሚባልበት ቀደም ባለው ዘመን ብዙ መካሪ፣ ነቃፊ፣ ተቺ፣ ቀስቃሽ ሙዚቃዎችን ያዜመው ጥላሁን ገሠሠ “ይቅርታ ምንድን ነው” ብሎ አዚሟል።
ጥላሁን የይቅርታ ባህላችንን ስሑትነት በማንሳት እንደገና እንድናስብ በማዜም ነው ዘፈኑን የሚጀምረው።
“ይቅርታ ምንድን ነው ካልተስተካከለ
እሾህ አሜኬላ ሆድ እያበቀለ”
የይቅርታ ወጉ ልብን ንጹህ አድርጎ፣ ጥፋትን አምኖ፣ ለካሳ ተዘጋጅቶ መቅረብ ነው። ከትናንት ስሕተት መማር እና ለወደፊት ላለመድገም ቃል መግቢያ ነው። ጥላሁን በዚህ አልተደሰተም። ትርጉሙ ላይ እንስማማ ነው የሚለው። ሰው በውስጡ ለሌላ ጸብ እየተዘጋጀ እና ቂም ይዞ ይቅርታ ማድረግ የተዛባ ትርጉም ነው በጥላሁን ዘፈን ግጥም ውስጥ፦
“ሰው ይቅርታ ቢለኝ ምንም የለው ዋጋ
በልቡ ጎዝጉዞ አጋም እና ቀጋ”
አጋም እና ቀጋ ጠንካራ እሾሆች ናቸው። የሰው ልጅ ውስጡ ያልሻረን ቂም ለማዳፈን ይቅርታን ሲጠይቅ ውሎ አድሮ ለበቀል መነሳቱ አይቀርም። ያ ዳግም የመነሳት እና ቂም እርሾ በእሾህ ተመስሏል። በዚህ መልኩ የሚደረግ ይቅርታ ፍሬ ቢስ ነው።
“የልብን ሰርቶ ይቅር በሉኝ
ምንስ አጠፋሁ ምን በደልኩኝ
በማለት አለ ሰው የሚያሞኝ
ቂምን በሆድ ይዞ መታረቅ
ይቅርታ አድርጉ እያሉ መራቀቅ
አጉል ነው ከንቱ መበሻሸቅ”
ይቅርታ ምንጩ ስሕተትን ማመን፣ መጸጸት እና የልብ ስብራት ነው። በጥላሁን ትዝብት ግን አውቀው የሚሳሳቱ፣ ጥፋትን የሚደጋግሙ ሰዎች አሉ። “ጥፋት የለብኝም፤ ግን ይቅርታ” የሚሉ ሰዎች አሉ። በቆሻሻ ልብ ውስጥ የሚቀመጥ ይቅርታ መቆሸሹ አልቀረም። ይቅርታው ለይስሙላ ነበርና መብሸቅ ብቻ ውጤቱ ይሆናል።
“ከልብ ውስጥ አይወጣም ተንኮል ለዘወትር
ቂም ሀያል ዱላ ነው ድምፅ የሌለው በትር”
ሰዎች በስሕተትም ይሁን ሆን ብለው ይበድሉናል። በደሉ ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ በእነሱ ላይ የምንይዘው ቂም የከፋ ነው። ላደረሱብን ጥፋት የምንሰጠው ትርጉም እና ግንዛቤ ቀጣይ ሕይወታችንን ይወስነዋል። ቂም ውስጣችንን የሚበላ ካንሰር ሆኖ ከጉዳቱ በላይ ይበድለናል። ድምጽ አልባ በትር ሆኖ ይቀጠቅጠናል። በሕይወታችን ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ተግባራትን ጊዜ፣ አቅም፣ እና ትኩረት የቂም አረም ይበላብናል።
“ንጹህ ሰው በመምሰል ውስጡ ሳይታወቅ
ላይ ላዩን በመሳቅ ይላል እንታረቅ”
የኀይል ፈላስፋው ኒኮሎ ማኪያቬሊ “ስለሰላም አብዝቶ የሚያወራ መሪ ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው” እንደሚለው በጥላሁን ዘፈን ውስጥ ቂም እና በደልን ደብቀው ይቅርታ የሚሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በውስጣቸው እሳት ያዳፈኑ፣ የውሸት ፈገግ የሚሉ እና በደላቸውን የረሱ የሚመስሉ ናቸው። ጊዜ፣ ቦታ እና ሁኔታ ጠብቀው የሚበቀሉ ናቸው።
ጽሐዬ ዮሐንስ የይቅርታን ትርጉም እና አስፈላጊነት፣ ማን፣ መቼ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት የት ነበርሽ በሚል ዘፍኗል።
“ተበድዬስ ማሪኝ አልልም የቀረው ይቅር እንጂ
እንኳን ልልክ አማላጅ እግሬ አይረግጥም ያንቺን ደጅ”
በዚህ ዘፈን ውስጥ የሚያዜመው ገጸ ባህርይ የተበደለ፣ ፍርድ የተጓደለበት ነው። ነገር ግን እሱ ነው የበደለኝ የምትል ሴት አለች። ከዚህም አልፋ ይቅርታ ይጠይቀኝ እያለች ሰው የላከችበት ትመስላለች።
“አፍቅሬ እኖራለሁ ስትይኝ ከርመሻል
ታምኜ እዘልቃለሁ ስትይኝ ከርመሻል
ያኔ በአንደበትሽ ጥሩ ሰው መስለሻል
ቃልሽ የታጠፈው ዛሬ ምን ነክቶሻል?”
ይህች ሴት ፍቅረኛዋን ጥላው ሄዳለች። ጥንት ፍቅር ሲጀምሩ ሀቀኛ ነበረች። በአንደበቷ አረጋግጣለታለች። ካንተ አይነጥለኝ ብላው ነበር። ዛሬ ግን ያ ተረት ሆነ። በመጨረሻም ወሰነች። ጥላው ሄደች። ከእቅፉ ሸሽታ ሄደች። እሱ ጥላኝ ሄደች ይላል። እሷም የሄደችበት ምክንያት ይኖራታል፤
መክሯታል፤ ታግሷታል፤ ለፍቅር ብሎ መከፋትን ችሏል። በዚህ ጊዜ ሁሉ ተበዳዩ እሱ ነው። ለዚህ ነው ይቅርታ መጠየቅ ያንቺ እንጂ የኔ ተግባር አይደለም የሚላት።
በእድሜ ሳይገደብ ከልጅ እስከ አዋቂ
የበደለ ሰው ነው ይቅርታ ጠያቂ
መቻሌ ሳይንሰኝ የጥፋትን ህመም
እንደምን አድርጌ ይቅር በይኝ ልበል?
ፍትሕ ፈላጊ ነው፤ ፍቅርም ፈላጊ ነው፤ ድንገት አንቺ እኔን ይቅርታ ለመጠየቅ ከመጣሽ አልጨክንብሽም ይላል። በድላው የውሸት ተበደልሁ ማለቷ ግሩም ነው። እሱ ግን አይቆርጥም። ምነው ከረፈደ፣ እስከዛሬ የት ከርመሽ ነው ከሚል በቀር ሊቀበላት ያስባል።
“የውሸት መንገዱ ጎዳናው ከታየሽ
ምህረት ባልነፍግሽም አንቺ ግን ዘገየሽ”
የኤፍሬም ታምሩ ቂም አልይዝም ባንቺ ዘፈን ለየት ያለ የይቅርታን ሀሳብ ይዟል።
አንቺ አጥፊ ነሽ፤ ነገር ግን ለፍቅሬ ስል አልቀየምሽም የሚል የተበዳይ ፍቅር ልመና ነው የምንሰማው። የበደለችው ሴት የጥፋተኝነት ስሜት ረብሿት ጥላው ሄዳለች። እሱ ግን ግዴለም ተመለሽ አልቀየምም፤ ሁሉን እረሳልሻለሁ ብሎ ሲማጸን እንሰማዋለን።
አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ሰዎችን መበደል በበደል ፈጻሚው ህሊና በኩል የቦምብ ፍንዳታ ያህል የሚያሳድድ እሳት ይለቃል። የተበደለው ሰው በዳዩን ዝም ማለቱ፤ የበዳይን ነፍስ ይቀጣታል። ኤፍሬም ቂም አልይዝብሽም የሚላት ሴት ኀዘንተኛ ናት። ራሷ በበዳሏ ተጸጽታ ጥላ ሄዳለች። “ተይልኝ” እያለ የሚለምናት እንድትመለስ ነው። እሱ ፍጹም ሰው ይመስላል። ብታጠፋም ፍቅራቸው ከጥፋቷ በላይ ነውና የወደፊቱን አብሮነት አብዝቶ ይፈልገዋል። የበደለችውን ረስቷል። ግን እሷን ላለማጣት ሲል ነው።
ከፍተሽ ግቢ በሬን ከፍተሽ እንደወጣሽ
ጥፋትሽን ልሸከም ጨርሼ ከማጣሽ
ናፈቀኝ ፈገግታሽ የጨዋታሽ ለዛ
መጣ በዙሪያዬ የፍቅርሽ መዓዛ
ዛሬም እንደፊቱ እንኑር በጋራ
እጠብቅሻለሁ ከይቅርታ ጋራ
ሕብስት ጥሩነህ ይቅርታ የምትለው ለፈጣሪ ነው። የሰው ልጆች በምድር የሚገጥሟቸው ችግሮች ሁሉ የአምላክ ቁጣዎች ናቸው ትላለች። የፈጣሪን ሕግ እና ትዕዛዛት መሻር እና መተላለፍ ነው የዚህ ሁሉ ያበቃን ትላለች ኅብስት። ምሕረቱም ከራሱ ነው።
“እባክህ አምላክ ሆይ ላደረግነው ኃጢአት
በቃችሁ በልና ስጠን ምህረትን”
ከበደልኩሽ ማሪኝ የሚለው የአያሌው መስፍን ሙዚቃ ጥፋቱን ያምናል። ካንቺ ከተለየሁ ኮሳሳ ሆንሁ፣ ከርታታ ሆንሁ፣ ሰው የሌለው ሆንሁ ይላል። ለዚህም ነው ማሪኝ የሚለው። “የአንድ ቀን ጥፋት ነው፤ ሰው ይሳሳታል” የሚሉ የሚያራሯትን ልመናዎች ይተርካል። ሽማግሌ በእኔ እና አንቺ መሐል አያስፈልግም የሚል ጽኑ እምነት አለው። በፈጣሪ ስም የሚለምናት ይቅር እንድትለው በማዘን ነው።
በይቅርታ ላይ የተዜሙ ሙዚቃዎቻችን ብዙ ናቸው። በነዋይ ደበበ “እኛው እንታረቅ” ይህንን ጽሑፍ ልቋጨው። በፍቅረኛሞች፣ በወዳጆች፣ በቤተሰቦች፣ በቡድኖች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ሦስተኛ ወገን ሳይሰማ ቢደረጉ እንዴት መልካም ነበር። ባል እና ሚስት ጉዳያቸውን በራሳቸው ቢፈቱ እንዴት ውብ ነበር። ሽማግሌ የታራቂዎችን ሕመም አይረዳም። ግንኙነቱን ስለማስቀጠል ነው የሚመክረው። የተጣሉት ሰዎች ግን ሰከን ብለው ቢነጋገሩ ችግራቸውን ራሳቸው ይፈቱት ነበር። ለባል ከሚስት በላይ ለሚስትም ከባል በላይ የሚቀርባቸው የለም። አመል ከማስቆጠር በቀር። ይህን ማድረግ በስሜት መብሰልን ይጠይቃል። ነዋይ ደበበ እሱን ነው የሚለን።
ሰላም ሁኑልኝ።
መረፊያ
የይቅርታ መሐልይ
ማነዉ የፈለገኝ?
በማይነጋ ሌሊት
በማይመሽ ቀን መሀል
ተዘርሬ ስገኝ፡፡
ከተዉሽኝ በኋላ ‘ርቃን ቀርታ ነፍሴ
እንኳንስ ከሰው ዐዉድ ተነጠልኩ ከራሴ፡፡
ተመልሼ ልምጣ ተመልሰሽ ነዪ
ልጣል ምሰሶዬን ማገርሽን ጣዪ
አዲስ ቤት መገንባት ዛሬ መች ይደላል
ለምደዉ ወደተዉት መመለስ ይቀላል፡፡
ካሳ ባልክልሽ ቁና ጤፍ ሰፍሬ
ባዶ እጄን አልቆምም ከደጅሽ ደፍሬ
ጽንፍ የለሽ ይቅርታን ውሰጅ ከከንፈሬ፡፡
በዕውቀቱ ስዩም፡፡
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


