ግብርና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት መሆኑ በተደጋጋሚ የሚነገር ሀቅ ቢሆንም የዚህ ዘርፍ ዋነኛ መሰረት የሆነው የአፈር ለምነት ጉዳይ ግን ፈታኝ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በተለይም በአማራ ክልል እየታየ ያለው የአሲዳማነት መስፋፋት የግብርናውን ዘርፍ ከሚፈትኑ ዓቢይ ችግሮች ቀዳሚው ሆኗል። አፈር ለኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ሀብትም በላይ ነው። የግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናችን መሰረት፣ የኢኮኖሚያችን ሞተር እንዲሁም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የኑሮ ሕልውና ነው። ሆኖም ይህ እጅግ ጠቃሚ ሀብት ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ በመራቆቱ እና በመሸርሸሩ ኢትዮጵያን ለከባድ ፈተና እያጋለጣት ይገኛል። ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ እና የአፈር ለምነትን ለመመለስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።
በቅርቡም በኢንተርናሽናል ፈርትላይዘር ዴቨሎፕመንት ሴንተር ትራንስፎርም መርሐግብር የአማራ ክልልን የአፈር ጤንነት እና ለምነት ለመጠበቅ ያለመ ውይይት ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከአማራ ክልል ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ ከግብርና ሚኒሥቴር እና በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የባለ ድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። ውይይቱ በቀጣይ የአፈርን ለምነት እና ጤንነት ለመጠበቅ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒሥቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒሥትር ዴኤታ አማካሪ ማሞ ደግሶ እንዳብራሩት በዓለም ላይ ከሚገኙ 28 የአፈር አይነቶች 23ቱ በኢትዮጵያ ይገኛሉ። ሆኖም በአፈር ሀብታችን አያያዝ እና አጠቃቀም ላይ ባሉ ክፍተቶች ምክንያት የግብርና ምርታማነት እጅግ እየቀነሰ መጥቷል።
እንደ ሀገር ከሚታረሰው መሬት ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በአሲዳማነት የተጠቃ ነው፤ ከዚህም 11 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በጨዋማነት የተጠቃ ነው። ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው ኮትቻ አፈር (ከፍተኛ የሆነ ውኃ የመያዝ እና የማቆየት አቅም ያለው የአፈር አይነት) ደግሞ ተገቢው የውኃ ማፋሰሻ ካልተሠራለት በስተቀር ለግብርና ሥራ አስቸጋሪ መሆኑን ጥናታዊ መረጃዎችን አጣቅሰው ተናግረዋል። ምንም እንኳን ችግሩ የገዘፈ ቢሆንም ሀገራዊ የአፈር ጤናን ለመመለስ ባለፉት አምስት ዓመታት ሰፊ ተግባራት መከናዎናቸውን አቶ ማሞ ጠቁመዋል።
የአፈር መሸርሸርን ለመግታት በተከናወኑ ሥራዎችም በአንድ ሄክታር 130 ቶን ይሸረሸር የነበረውን ወደ 54 ቶን ዝቅ ማድረግ ተችሏል። በተጨማሪም የተራቆተ መሬት መልሶ እንዲያገግም ተደርጓል። የአፈር ለምነትን በተፈጥሯዊ መንገድ ለመመለስም ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ከ83 ሺህ ሄክታር በላይ አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል። የተመዘገቡ ውጤቶች የሚበረታቱ ቢሆንም ዘላቂ የሆኑ የአፈር ልማት ጥበቃ ስልቶችን መተግበር እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና አሠራርን መከተል እንደሚገባም አብራርተዋል። በቀጣይ የተጀመሩ መልካም ተግባራት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ትራንስፎርም የአፈር ጤንነት እና ለምነት መርሐግብር የኢትዮጰያ ፕሮግራም ዳይሬክተር ካሳሁን አዴሎ (ዶ.ር) በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሊታረስ ከሚችለው መሬት ውስጥ ወደ 43 በመቶ የሚጠጋው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህንን ሀገራዊ አደጋ ለመቀልበስ እና የአፈር ለምነትን ለመመለስ ያለመ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ላለፉት 50 ዓመታት በማዳበሪያ ልማት ላይ ሲሠራ የቆየው አይ.ኤፍ.ዲ.ሲ (IFDC) ኢንተርናሽናል የተሰኘ ድርጅት በኢትዮጵያ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ቢሮ ከፍቶ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል። ድርጅቱ አሁን ደግሞ ትራንስፎርም ሶይል ሄልዝ ኤንድ ሶይል ፈርቲሊቲ (Transform Soil Health and Soil Fertility) የተሰኘ የአራት ዓመት ፕሮግራም በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በመተግበር ላይ ይገኛል።
ፕሮግራሙ በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ ወደ ትግበራ የገባ ሲሆን በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ በ12 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ የሚያተኩረው በእውቀት ሽግግር እና በአቅም ግንባታ ላይ ነው። አርሶ አደሮቹ የአፈር ለምነት ችግሮችን እንዲለዩም ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል። በአጠቃላይ ፕሮግራሙ በሦስቱም ክልሎች በአራት ዓመታት ውስጥ 65 ሺህ ሄክታር መሬት ከችግር ታድጎ ወደ ለምነት ለመመለስ እና 100 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትልቅ ግብ ሰንቆ እየሠራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች የአፈር ለምነትን በማሳጣት በስፋት የተከሰተውን እና በግብርና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀነውን የአፈር አሲዳማነት ችግር ለመፍታት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። ቢሮው ችግሩን ለመቀልበስ ከትራንስፎርም ኢትዮጵያ ፕሮግራም እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል።
በቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ምክትል ቢሮ ኃላፊ መሰሉ ብርሐኑ ለበኵር እንደገለጹት በክልሉ የአፈር ለምነት መቀነስ እና አሲዳማነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በክልሉ አምራች በሆኑ አካባቢዎች ከፍተኛ የአፈር አሲዳማነት ይስተዋላል። በተለይም በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ጎጃም፣ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ የሆነ የአፈር አሲዳማነት እንደሚታይ ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖችም ችግሩ በመካከለኛ እና በተለያየ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን በአጠቃላይ ክልሉ በአፈር አሲዳማነት ዋነኛ ተጠቂ መሆኑን አብራርተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች መሬትን በኖራ የማከም እና የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ነው ምክትል ኃላፊዋ የተናገሩት። ይህን ከፍተኛ ችግር ለመፍታት እና የአፈርን ለምነት ለመመለስ ቢሮው የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ወደ ተግባር መግባቱን ኃላፊዋ ገልጸዋል። ከእነዚህም መካከል አርሶ አደሩ ቨርሚ ኮምፖስት፣ መደበኛ ኮምፖስት እና ባዮ-ሳላሪን በስፋት እንዲያዘጋጅ እና እንዲጠቀም የማድረግ ሥራ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ተግባራት ናቸው።
በሌላ በኩል የአፈር ለምነትን በማሻሻል በኩል ትልቅ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው የትራንስፎርም ኢትዮጵያ ፕሮግራም በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ ዞኖች ተጨባጭ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። ፕሮግራሙ በተለይም የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግ፣ የኤክስቴንሽን ሥርዓቱን እስከ ታችኛው መዋቅር በማውረድ እንዲሁም ከተፈጥሮ ማዳበሪያ በተጨማሪ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያዎችን አጣምሮ የመጠቀም አቅምን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑ ገልጸዋል።
በክልሉ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የሚሠሩ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ፕሮጀክቶች ችግር እንዳይገጥማቸው፤ ቢሮው ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ወደ አንድ የጋራ መድረክ በማምጣት ሀብት እና ጉልበትን በማስተባበር የተሻለ ውጤት ለማምጣት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ለበኵር ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈር እና ውኃ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና ከፍተኛ ተመራማሪ ተስፋዬ ፈይሳ (ዶ/ር) በክልሉ ያለውን የአፈር ለምነት ችግር ስፋት እና እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ ርምጃዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደ ተመራማሪው ገለጻ በክልሉ በመታረስ ላይ ካለው መሬት ውስጥ 36 በመቶ የሚሆነው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ነው። ይህንን ለማከም አርሶ አደሮች የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።
ከዚህም ባሻገር በክልሉ የግብርና ሥራ ላይ በእጅጉ አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ የአፈር የተፈጥሮ ብስባሽ እጅግ አነስተኛ መሆን ነው። ለዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ አርሶ አደሩ ሰብል ካመረተ በኋላ በማሳው ላይ ምንም ዓይነት የሰብል ቅሪት (ገለባ) አለማስቀረቱ ነው። አፈሩም ከዓመት ዓመት የሚያርፍበት ጊዜ ባለመኖሩ የተፈጥሮ ማዕድኑን እያጣ እና እየተመናመነ መጥቷል። ስለሆነም አርሶ አደሩ የሰብል ቅሪትን ሙሉ ለሙሉ ከማሳው ማንሳት እንደሌለበት መክረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተቀናጀ የአፈር ለምነት አያያዝን መተግበር ግድ ብሏል። ይህ ማለት የፋብሪካ ማዳበሪያን ከተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ጋር አቀናጅቶ መጠቀም ነው።
ኢንተርናሽናል ፈርትላይዘር ዴቨሎፕመንት ሴንተር ትራንስፎርም (Transform) የተሰኘው ፕሮጀክት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በቀድሞው አሠራር መመሪያዎች ከላይ ወደ ታች የሚወርዱ ነበሩ፡፡ የትራንስፎርም ፕሮጀክት ግን ከታች ወደ ላይ የሚለውን አሠራር ተግባራዊ አድርጓል። “አሁን እያንዳንዱ አርሶ አደር ችግሩን ራሱ ይለያል፣ መፍትሔውም ላይ የራሱ የባለቤትነት ስሜት ይኖረዋል። አርሶ አደሩ በልቡ አምኖበት ‘እኔ መሥራት አለብኝ!’ ወደሚል አስተሳሰብ እንዲመጣ አድርጎታል” ሲሉ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በቃሉ ወረዳ የ019 ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ሰይድ የሱፍ አምስት ጥማድ መሬታቸው የአፈር ለምነቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል እየተንከባከቡት እንደሆነ ለበኵር በስልክ ነግረውናል። ከእንክብካቤ ተግባራት መካከልም በጎርፍ እንዳይሸረሸር ዙሪያውን አትክልት መትከል፣ እርከን መሥራት እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በስፋት መጠቀም ይገኙበታል። የሚያገኙት ምርትም ከዓመት ዓመት መሻሻሉን ነው የጠቀሱት። ለሌሎች አርሶ አደሮች ጭምር የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነዉ ተሞክሯቸዉን ያጋሩት።
መረጃ
የአፈርን ለምነት ለመጠበቅ
ሰብልን አፈራርቆ መዝራት።
የተፈጥሯዊ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) መጠቀም።
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ማጠናከር (እርከን መሥራት)።
ዛፎችን መትከል።
መሬትን ማሳረፍ።
የፀረ-አረም ኬሚካልን በአግባቡ መጠቀም እና ሌሎች ይገኙበታል፡፡
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


