ሀገራት ያጡትን ሰላም እንዴት መለሱት?

0
210

በዓለም ታሪክ በከባድ ግጭት እና በጦርነት ተፈትነው ከመፈራረስ የተረፉ ሀገራት በርካታ ናቸው፡፡ ሀገራቱም ወደ ጦርነት የሚገቡት በአንድ ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ እንጅ፡፡

በፖለቲካ አለመግባባት፣ በሥልጣን ሽኩቻ፣ የምርጫ ውጤትን አለመቀበል፣ በአስተዳደር ችግሮች፣ በሕግ የበላይነት መዳከም፣ በዘር፣ በብሔር ወይም በሃይማኖት ልዩነቶች አማካኝነት  ግጭቶች ይከሰታሉ። ከነዚህ በተጨማሪም  በታሪክ ቂምና ቅሬታ፣ በተፈጥሮ ሀብት ይገባኛል ፉክክር፣  በእርሻና በግጦሽ መሬት ባለቤትነት፣ በድንበር አለመግባባት፣ በግዛት ይገባኛል ጥያቄዎች፣ በሥራ አጥነት፣  በኑሮ ውድነት፣ በሀብት በእኩል አለመከፋፈል፣ በውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በፍትሕ እጦት፣ በሙስና እና በመንግሥት አቅም ማነስ አማካኝነት ሃገራት ወደ ግጭት እና ጦርነት ይገባሉ፡፡

ይሁንና ሀገራቱ ጦርነቱ ያስከተለባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግር በመረዳትና ጦርነትን  በመጸየፍ ወደ ሰለማዊ ኑራቸዉ ለመመለስና ሰላምን ለማምጣት ብዙ ተግባራትን ያከናዉናሉ፡፡

ሰላምን ለማስፈንም  ውይይትን፣ ስምምነትን እና የተቋማትግንባታን በዋነኛነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡

የተለያዩ ሀገራት ሀገራዊ ምክክርን ያካሄዱት እንደየታሪካቸው፣ የግጭት ሁኔታቸው እና የፖለቲካ አውዳቸው ነው፡፡ ዋናው ዓላማ ግን ተቃራኒ የሆኑ ወገኖችን በአንድ ጠረጴዛ ላይ ማሰባሰብ፣ ቅሬታዎችን መስማት፣ በጋራ መፍትሔ መፈለግ እና ዘላቂ ሰላም መገንባት ነው፡፡ የሰላምን መንገድ ከተከተሉ ሀገራት መካከልም ሴራሊዮን አንዷ ናት፡፡ ሴራሊዮን እ.አ.አ ከ1991 እስከ 2002 ድረስ ለ11 ዓመታት የቆየ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት አሳልፋለች፡፡

ይህ ጦርነት ሀገሪቱን ከፍተኛ የሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ አስገብቷታል፡፡

ሀገሪቱ እ.አ.አ በ1961 ከቅኝ አገዛዝ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ   በሙስና፣ በዘመድ አዝማድ፣ ጥቅማጥቅም እና በደካማ መንግሥታዊ ተቋማት ስትታመስ ቆይታለች፡፡ በወቅቱ ብዙ ዜጎች መንግሥት ጥቂቶችን ብቻ እንደሚጠቅም ያምኑ ነበር፡፡

ሴራሊዮን በአልማዝ ማዕድን በጣም የበለጸገች ሀገር ብትሆንም ይህ ሀብት ግን ለሕዝብ እድገት ሳይውል ለሙስና እና ለታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ምንጭ ሆኗል፡፡ በኋላም “የደም አልማዝ” (Blood Diamonds) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ እነዚህ አልማዞች እ.አ.አ ከ1991 እስከ 2002 ድረስ አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት አስከትለዋል፡፡ ጦርነቱም ወደ 75ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል፤  ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጭካኔም አስከትሏል፡፡

ዋናው ግጭት አብዮታዊ የተባበሩት ግንባር (RUF) በመባል የሚታወቀው የአማፂ ቡድን በምሥራቅ ሴራሊዮን በተለይም በኮኖ አውራጃ ዙሪያ ዋና ዋና የአልማዝ ማዕድን ማውጫ ክልሎችን እንዲቆጣጠር አድርጓል፡፡

አብዮታዊ የተባበሩት ግንባር እነዚህን አልማዞች እንደ ላይቤሪያ ባሉ ጎረቤት ሀገራት ውስጥ በድብቅ አስገብቷቸዋል፡፡ ሕገ-ወጥ በሆነው ገንዘብም ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶችን ገዝቶበታል፡፡ በሀገሪቱ በርካታ ወጣቶች ሥራ አልነበራቸውም፤ የትምህርት እድልም ውስን ነበር፤ ይህ ሁኔታም ወጣቶችን በታጣቂ ቡድኖች በቀላሉ እንዲመለመሉ አድርጓቸዋል፡፡

እ.አ.አ በ1991 በፎዴ ሳንኮህ የሚመራው አብዮታዊ የተባበሩት ግንባር በጎረቤት ላይቤሪያ ድጋፍ ወደ ሴራሊዮን ገብቶ በመንግሥት ላይ በትጥቅ የታገዘ አመፅ ጀመረ፡፡

በወቅቱ የሀገሪቱ የጦር ኀይል ደካማ ስለነበር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩ በርካታ አካባቢዎች ከእጁ ወጡ፡፡ ይህም ጦርነቱ እንዲስፋፋ አደርጓል፡፡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በርካታ ሕፃናት በግዳጅ ወደ ጦርነት ገብተዋል፡፡ ትምህርት፣ ጤና እና ኢኮኖሚው በእጅጉ ተጎድተዋል፡፡ ከዚህ  በኋላ የመንግሥት እና አብዮታዊ የተባበሩት ግንባር መሪዎች የሎሜ የሰላም ስምምነትን እ.አ.አ በ1999  ፈርመዋል፡፡

ስምምነቱ ምንም እንኳን ወዲያውኑ ሙሉ ሰላም ባያመጣም ለመጨረሻው መፍትሔ መንገድ ከፍቷል፡፡ በዚህ ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት በርካታ የሰላም አስከባሪ ኀይል አሰማርቷል፡፡ የትጥቅ ማስፈታትና የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማሕበረሰብ የመመለስ መርሀ ግብሮችን(ፕሮግራሞችን) ደግፏል፡፡

በሴራሊዮን የእውነትና እርቅ ኮሚሽን (Truth and Reconciliation Commission – TRC) የተቋቋመው ለ11 ዓመታት (ከ1991 እስከ 2002) ከዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ እ.አ.አ በ1999 በተፈረመው የሎሜ (Lomé) የሰላም ስምምነት አማካኝነት ነው፡፡ ዓላማውም በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ ግፎችን በግልጽ ማሳየት፣ ተጎጂዎችን መስማት፣ ተጠያቂነትን ማጠናከር እና ዘላቂ እርቅ ማምጣት ነበር፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ እ.አ.አ በ2002 ሥራውን የጀመረ ሲሆን ጦርነቱም በዚያው ዓመት በይፋ ተጠናቋል፡፡

የእውነት  እና  የእርቅ  ኮሚሽኑ   በጦርነቱ ወቅት  የተፈጸሙ  የሰብዓዊ  መብት        ጥሰቶችን በመመዝገብ ተጎጂዎች የደረሰባቸውን ጉዳት  በይፋ እንዲናገሩ ዕድል ሰጥቷል፡፡

ግፍ  ፈጻሚዎች  ድርጊታቸውን እንዲገልጹ አበረታቷል፤ የጦርነቱን መንስኤዎች ለይቷል፤ ግጭት ዳግም እንዳይከሰት ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል፤ የሕዝብ ችሎቶች ተካሂደው ተጎጂዎች በይፋ ምስክርነት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡  የቀድሞ ተዋጊዎች፣ የመንግሥት ወታደሮች፣  የአማጺ ቡድኑ አባላት እና ሌሎች ተሳታፊዎችም ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ለሕፃናትና ለፆታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ልዩ ጥበቃ ያለው የችሎት ሂደት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህም ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽኑ እ.አ.አ በ2004 ባቀረበው የመጨረሻ ሪፖርቱም ጦርነቱ በዋነኝነት የተከሰተው በሙስና፣ በድህነት፣ በወጣቶች መገለል እና በደካማ  አስተዳደር ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡ ለተጎጂዎች የካሳ እና የማገገሚያ ድጋፍ እንዲደረግ መክሯል፡፡

የፍትሕ ሥርዓት፣ የፀጥታ ተቋማት እና የመንግሥት አስተዳደር እንዲሻሻሉ ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል፡፡

በሴራሊዮን    የእውነትና እርቅ ኮሚሽን እና ልዩ  ፍርድ ቤት (Special Court for Sierra Leone)  በአንድ  ጊዜ  ነበር        የተቋቋሙት፡፡

ነገር ግን ዓላማቸው የተለያየ ነበር፡፡

የእውነትና እርቅ ኮሚሽን  ዋና ትኩረቱ እውነትን ማውጣት፣ ሕዝቡን ማስታረቅ እና ምክረ ሐሳብ መስጠት ነበር፡፡ ልዩ ፍርድ ቤቱ ደግሞ ከባድ የጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን የፈጸሙ ዋና ኃላፊዎችን ለፍርድ አቅርቧል፡፡ ሴራሊዮን ያሳየችው ትምህርት ዘላቂ ሰላም የሚገነባው በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት በመደበቅ ሳይሆን እውነቱን በግልጽ በማውጣት፣ ተጎጂዎችን በማዳመጥ፣ ኃላፊዎችን(ወንጀል ፈጻሚዎችን) ተጠያቂ በማድረግ እና የግጭቱን መሠረታዊ መንስኤዎች በመፍታት  ነው፡፡

እ.አ.አ ከ1989 እስከ 2003 የተከሰተው የላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ በአንድ ምክንያት የተከሰተ አልነበረም፡፡ ለብዙ ዓመታት የተከማቹ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማሕበራዊ  እና የብሔር ችግሮች ተደራርበው ወደ ጦርነት በማምራታቸው ነው፡፡

አ.አ.አ ከ1822 ጀምሮ የአሜሪካው የቅኝ ግዛት ማሕበረሰብ (American Colonization Society)በላይቤሪያ የቅኝ ግዛት ሰፈራ አቋቁሞ ነበር፡፡ በዚህም ነጻ የወጡ ጥቁር አሜሪካዊያንም (Americo-Liberians) የሀገሪቱን ስልጣን ለብዙ ዓመታት ተቆጣጥረው ቆይተዋል፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ ተወላጅ ሕዝብ ግን ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ተገልሎ ነበር፡፡ ይህም ጥልቅ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ እ.አ.አ በ1980 ማስተር ሰርጀንት ሳሙኤል ዶ (Samuel Doe) ፕሬዚዳንት ዊልያም ቶልበርትን በመግደል በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ያዘ፡፡

አዲሱ መንግሥት ስልጣን ቢይዝም ዴሞክራሲን ግን አላጠናከረም ነበር፡፡ በተለይም የብሔር ክፍፍል አገዛዙን ፈትኖት ነበር፡፡ ሳሙኤል ዶ የራሱን የክራን ብሔር በተለየ ሁኔታ ይደግፋል ተብሎ ተደጋጋሚ ወቀሳ እና ቅሬታ ይቀርብበት ነበር፡፡ ሌሎች ብሔሮች በተለይም ጂዮ እና ማኖ ላይ ጭቆና እና ግድያ ተፈጸመ የሚል ከፍተኛ ቅሬታ ነበረበት፡፡

ሌላው ሀገሪቱን ግጭት  ውስጥ ያስገባት የኢኮኖሚ ቀውስና ሙስና ነው፡፡ ሀገሪቱ በተፈጥሮ ሀብት (በአልማዝ፣ ወርቅ፣ እንጨት፣ ጎማ) ብትበለጽግም ሀብቱ ፍትሐዊ ክፍፍል አልነበረም፡፡ በዚህም ሙስና፣ ድኅነት እና ሥራ አጥነት ተባብሷል፡፡

እ.አ.አ በ1989 ቻርልስ ቴይለር የሚመራው የናሽናል ፓትሪዮቲክ ፍሮንት ኦፍ ላይቤሪያ(National Patriotic Front of Liberia (NPFL) ከኮትዲቯር በኩል ወደ ላይቤሪያ ገብቶ በመንግሥት ላይ የትጥቅ ትግል ጀመረ፡፡

ይህም የመጀመሪያውን የእርስ በርስ ጦርነት አስከትሏል፡፡  በጦርነቱም የመንግሥት ተቋማት ተዳክመዋል፣ ሕግና ሥርዓት ፈርሷል፣ በርካታ የታጠቁ ቡድኖችም ተፈጥረዋል፡፡

ይህ ችግር ያመጣው ጦስ ከ250ሺህ በላይ ሰዎች እንዲሞቱ አድርጓል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚና መሠረተ ልማትም በእጅጉ ወድመዋል፡፡ በርካታ ሕፃናትም የመቦረቂያ ጊዜያቸውን ትተው  በጦርነቱ ውስጥ እንዲሳተፉ ተገደዋል፡፡

ከዚህ ሁሉ ችግር በኋላም እ.አ.አ በ2003 በጋና አክራ የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ፤ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት (ECOWAS) እና የተባበሩት መንግሥታትም በሰላም ማስከበር ዘመቻ ተሳትፈዋል፡፡ ተዋጊዎች መሣሪያቸውን እንዲያስረክቡ ፕሮግራሞች ተካሂደዋል፡፡ እ.አ.አ በ2005 ኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ የአፍሪካ የመጀመሪያዋ ምርጫ ተወዳድራ ያሸነፈች ሴት ፕሬዚዳንት ሆነች፡፡ ይህም ለሀገሪቱ መረጋጋት አስፈላጊ ርምጃ ነበር፡፡

የላይቤሪያ ተሞክሮ የሚያስተምረው የፖለቲካ መገለል፣ የብሔር መከፋፈል፣ ሙስና እና ደካማ ተቋማት አንድ ላይ ሲገጣጠሙ ሀገርን ወደ ጦርነት ሊገፉ እንደሚችሉ ነገር ግን በድርድር፣ በሰላም ስምምነት፣ በፍትሕ እና በተቋማት ግንባታ ከዚህ ቀውስ መውጣት እንደሚቻል ነው፡፡

መረጃዎቹ ከሴራሊዮን እና ከላይቤሪያ ትሩዝ እና ኮንሳሌሽን ሪፖርቶች የተገኙ ናቸው፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 20   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here