ልጆች እና ወላጆች እንዴት ሰነበታችሁ? የክረምት ወቅት ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ልጆች ከረጅም የትምህርት ገበታ በኋላ ሰፊ የእረፍት ጊዜ የሚያገኙበት ልዩ አጋጣሚ ነው። ብዙ ጊዜ ወላጆች ይህንን ሶስት ወር ገደማ የሚቆይ ረጅም ጊዜ ልጆቻቸው እንዴት ፍሬያማ በሆነ መንገድ ማሳለፍ እንዳለባቸው ማቀድ ይፈታተናቸዋል። ይሁን እንጂ የክረምቱን እረፍት በአግባቡ ከተጠቀምንበት ልጆች አዳዲስ የሕይወት ክህሎቶችን የሚቀስሙበት፣ የፈጠራ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት እና ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ራሳቸውን በንቁ አእምሮ የሚያዘጋጁበት ወርቃማ የዕድገት ምዕራፍ ሊሆን ይችላል።
ይህንን የእረፍት ጊዜ ፍሬያማ ለማድረግ መደበኛ ባልሆነው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የማይገኙ ነገር ግን ለሕፃናት የዕለት ተዕለት ሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ልጆች እንደ እድሜያቸው መጠን የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲለምዱ ማድረግ በራስ መተማመናቸውን በእጅጉ ይገነባል። የራሳቸውን አልጋ ማንጠፍ፣ ክፍላቸውን ማስተካከል እና ቀላል የቁርስ ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ ኃላፊነትን እንዲለማመዱ ያደርጋቸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን በቤት ውስጥ ሆነው በስዕል፣ በሸክላ ሥራ ወይም በተለያዩ የእጅ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ማበረታታት የፈጠራ አቅማቸውን ያሳድጋል፡፡ እንደ ቋንቋ እና መሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት (የሕፃናት ኮዲንግ) ባሉ አጫጭር ስልጠናዎች ላይ ማሳተፍ ደግሞ የወደፊት የዕውቀት አድማሳቸውን ያሰፋዋል።
ሌላኛው እና ዋነኛው የክረምት ተግባር የንባብ ባህልን ማዳበር ነው። በትምህርት ዘመን ልጆች የሚያነቡት ፈተናዎችን ለማለፍ ብቻ ሊሆን ስለሚችል ክረምት ለንባብ ፍቅር የሚያዳብሩበት ምርጥ ወቅት ነው። እንደ ታሪክ፣ ሳይንስ እና ልብ ወለድ ያሉ የልጆች መጽሐፍትን በመግዛት ወይም በአቅራቢያ ወደሚገኙ የሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት በመውሰድ የማንበብ ልምዳቸውን ማሳደግ ይቻላል። በተለይም ያነበቡትን መጽሐፍ ይዘት ተመልሰው ለወላጆቻቸው እንዲተርኩ ማድረግ የማስታወስ፣ የመተንተን እና የመናገር ብቃታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያጎለምሰዋል።
ምንም እንኳን የክረምቱ ዝናባማ የአየር ንብረት ልጆችን ቤት ውስጥ ሊያቆያቸው ቢችልም፣ ዝናብ በሌለባቸው ቀናት እና ክፍት በሆኑ የቤት ውስጥ ስፖርት ማዕከላት ውስጥ መንቀሳቀስ ለጤንነታቸው ወሳኝ ነው። ልጆችን እንደ ዋና፣ እግር ኳስ፣ ማርሻል አርት (ታይኮንዶ) ወይም ቅርጫት ኳስ ባሉ ስፖርቶች ውስጥ ማስመዝገብ በአካልም በሥነ-አእምሮም እንዲጠነክሩ ያደርጋቸዋል። ዝናብ በሚዘንብበት እና ከቤት መውጣት በማይቻልበት ሰዓት ደግሞ እንደ ቼዝ፣ ገበጣ፣ እና የተለያዩ የቦርድ ጨዋታዎች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የአእምሮ አስተሳሰባቸውን በጨዋታ መልክ ማሳለጥ ይቻላል።
ይህ ወቅት ልጆች ማኅበራዊ ግንኙነትን እና የሀገራቸውን ባህል የሚረዱበት መድረክ መሆን አለበት። የክረምት እረፍትን ፍሬያማ የማድረግ ምስጢሩ ጨዋታን፣ ዕውቀትን እና እረፍትን በአንድነት አቀላቅሎ በዕቅድ መምራት ላይ የሚመሰረት ሲሆን ነው፤ ይህም ልጆች ወደ ቀጣዩ ክፍል ሲዛወሩ በተሻለ ዝግጁነት እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል ይላል የዩኒሴፍ የልጆች ልማት መርሐ-ግብር።
ተረት
አህያው እና ሸክሙ
በድሮ ጊዜ ከባለቤቱ ጋር የሚኖር እጅግ በጣም ታካች አህያ ነበረ። ይህ አህያ በየቀኑ ከጌታው ጋር ወደ ጨው ማውጫ በመሄድ ጨው በጀርባው ተሸክሞ ወደ ገበያ ያመላልስ ነበር። አህያው ግን ሥራውን በጣም ይጠላው ነበር።
አንድ ቀን ወደ ገበያ እየሄዱ ሳለ ሳይታሰብ አንድ ወንዝ ለመሻገር ሲሞክር አህያው ተንሸራቶ ወንዙ ውስጥ ወደቀ። ወደ ላይ ለመነሳት ጥቂት ደቂቃዎችን ፈጀበት። በዚያ ጊዜ ውስጥ ግን በጀርባው ላይ የተጫነው ጨው በሙሉ በውኃው ስለሟሟ፣ ጀርባው በጣም ቀለለለት። አህያው በዚህ በጣም ተደሰተ። “የስራ ማቅለያ መንገድ አገኘሁ!” ብሎ አሰበ።
በማግስቱም ጌታው ጨው ጭኖበት ወደ ገበያ ሲሄዱ አህያው ሆን ብሎ ወንዙ ላይ ሲደርስ ራሱን ውኃው ውስጥ ጣለ። አሁንም ጨው ሟሙቶ ጀርባው ቀለለለት። ጌታው ግን የአህያውን ተንኮል ወዲያውኑ ተረዳ።
በሦስተኛው ቀን ጌታው በአህያው ጀርባ ላይ ጨው ሳይሆን ጥጥ ጫነበት። አህያው ምንም ሳያውቅ እንደለመደው ወንዙ ላይ ሲደርስ ሆን ብሎ ራሱን ውኃው ውስጥ ዘፈቀ። ነገር ግን ጥጡ ውኃውን በሙሉ ምጥጥ አድርጎ ስለያዘው ክብደቱ ከመቶ እጥፍ በላይ ጨመረ። አህያው ከባድ ሸክሙን ተሸክሞ መነሳት አቅቶት በጣም ተሰቃየ። ከዚያች ቀን ጀምሮ አህያው ተንኮል እና ስንፍና ሰውን እንደሚያስጠቁ ተረድቶ ስራውን በአግባቡ መሥራት ጀመረ።
ምንጭ፡- የኤሶፕ ተረቶች
ሞክሩ
- በአንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ አንድ ሻማ፣ አንድ የከሰል ምድጃ እና አንድ የጋዝ ፋኖስ አሉ። አንተ እጅ ላይ ያለው ግን አንድ የክብሪት እንጨት ብቻ ነው። መጀመሪያ የትኛውን ታበራለህ?
- ሁልጊዜ የሚጨምር እንጂ በህይወት ዘመንህ አንድም ቀን ቀንሶ የማያውቀው ነገር ምንድን ነው?
- ጥርስ አለው ግን አይነክስም። እሱ ማን ነው?
መልስ
- ክብሪቱን (ምክንያቱም ክብሪቱ ሳይበራ ሌሎቹን ማብራት አይቻልም!)
- እድሜህ
- ማበጠሪያ
ነገር በምሳሌ
-“ከምታውቀው በላይ እወቅ፣ ከምትሰራው በላይ ሥራ”፦ ሁልጊዜም እውቀትን ለማግኘት መጣር እና ሰነፍ አለመሆንን ያሳስባል።
-“ሳትመረምሩ አትናገሩ፣ ሳታኝኩ አትዋጡ”፦ አንድን ነገር ከመናገራችን ወይም ከመወሰናችን በፊት በደንብ ማሰብ እንዳለብን ይመክራል።
-“ካልዘሩት አይበቅልም”፦ ዛሬ መልካም ነገር ካላደረግን ነገ ጥሩ ፍሬ ማግኘት አንችልም።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


