በሁለት ሰዎች መካከል የተቀጣጠለ ውብ የፍቅር ነበልባል የሚጠፋው በታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም አስደንጋጭ ክህደት ብቻ ይመስልሃል?
አይደለም! አብዛኞቹ ግንኙነቶች የሚሰነጠቁት በጥንቃቄ ባልተያዙ ጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ነው። አእምሯችን በቁጣ፣ በጉዳት ወይም በንዴት አውሎ ንፋስ በተዋጠበት እና የምክንያታዊነት ደጃፍ በተዘጋበት በዚያች አጭር ቅጽበት፡፡
የሳይካትሪስቱ እና የኦሽዊትዝ አሰቃቂ ካምፕ ተራፊው ቪክቶር ፍራንክል በታዋቂው “ማንስ ሰርች ፎር ሚኒንግ” በተሰኘው መጽሐፉ አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ የሚነገር ድንቅ እውነት አለ።
በማነቃቂያው እና በምላሻችን መካከል ክፍተት አለ። በዚያች ክፍተት ውስጥ ምላሻችንን የመምረጥ ነፃነታችን ይገኛል። በምላሻችን ውስጥ ደግሞ እድገታችን እና ነፃነታችን ያርፋሉ። ይህን ሀሳብ በምሳሌ እንየው።
በፍቅር ግንኙነት ውስጥ “የስሜት ብልህነት” ማለት ይህቺን አጭር ክፍተት የማስተዋል እና የመግዛት ጥበብ ነው። የትዳር አጋርህ/ሽ ያቀረበልህ/ሽ ወቀሳ ማነቃቂያ ነው። የአንተ/ አንቺ የቁጣ ጩኸት ወይም ዝምታ ደግሞ ምላሽ ነው። የስሜት ብልህነት የጎደለው ሰው በዚህ ክፍተት ውስጥ ሳይቆም በቀጥታ ወደ ስሜታዊ ፍንዳታ ይገባል፤ የስሜት ብልህነት ያለው ሰው ግን በዚያች ክፍተት ውስጥ ቆሞ አስተዋይ ምላሽን ይመርጣል።
ዳንኤል ጎልማን “ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ” በተሰኘው መጽሐፉ እንደሚያስረዳው ከፍተኛ የአእምሮ ብቃት (IQ) ያለው ሰው በሙያው ስኬታማ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በግንኙነቶቹ ውስጥ ስሜቱን የመቆጣጠር ብቃት (EQ) ከሌለው ህይወቱ በውድቀት የተሞላ ይሆናል።
ጎልማን አእምሯችን በሁለት ክፍሎች እንደሚሰራ ያብራራል፡ ስሜታዊው አእምሮ (አሜግዳላ) እና አስተዋዩ አእምሮ (ፕሪፍሮንታል ኮርቴክስ) በሚባሉ።
በግንኙነት ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠር አሚግዳላ አደጋ እንደተደቀነበት በማሰብ አእምሮአችንን ይቆጣጠረዋል። ይህ “የአሚግዳላ ጠለፋ” ይባላል። በዚህ ጊዜ በደማችን ውስጥ አድሬናሊን እና ኮርቲሶል የተባሉ የጭንቀት ሆርሞኖች ይለቀቃሉ፤ ምክንያታዊው አእምሯችን ይዘጋል፤ ከዚያም እንጮሃለን፣ እንሳደባለን፣ ወይም ግንኙነቱን ጥለን እንሸሻለን።
የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጆን ጎትማን በጥንዶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለ40 ዓመታት ያህል አጥንተዋል። የፍቅር ላቦራቶሪ በተሰኘው የምርምር ማዕከላቸው ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥንዶችን እንቅስቃሴ፣ የልብ ምት፣ የሆርሞን መጠን እና የፊት ገጽታ በመመልከት ጥናት አድርገዋል።
“ጥንዶች ከተነጋገሩበት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ደቂቃዎች በመነሳት ብቻ 93 በመቶ ያህሉ ጥንዶች አብረው ይዘልቃሉ ወይስ ይፋታሉ የሚለውን አስቀድመው መተንበይ ይችላሉ” ብለዋል።
ጎትማን ግንኙነትን የሚገድሉ አራቱን የጥፋት ፈረሰኞች በጥናታቸው ለይተዋል፡
- ወቀሳ/ትችት፦ የሰውን ሰብዕና ማጥቃት (ለምሳሌ፡ “አንተ ሁልጊዜ ግዴለሽ ነህ!” ማለት)
- ንቀት፦ አካላዊ እና ቃላዊ ዝቅ ማድረግ፣ መሳለቅ፣ በዓይን ማንጓጠጥ። (ይህ ለፍቺ ዋናው ምክንያት ነው)
- ተከላካይነት፦ ጥፋትን አለመቀበል እና ወዲያውኑ ተከላክሎ መመለስ።
- ድንጋይ መሆን/ዝምታ፦ ራስን ሙሉ በሙሉ መዝጋት፣ አለመስማት እና ወደኋላ ማፈግፈግ።
እነዚህ አራቱም ባህሪያት የስሜት ብልህነት ማነስ ውጤቶች ናቸው። በጥናቱ መሠረት፦ በስሜት የበሰሉ ጥንዶችም ይጣላሉ፤ ነገር ግን ልዩነታቸው የግንኙነት ጥሪ ሲቀርብላቸው ፈጣንና በጎ ምላሽ መስጠታቸው እና የተበላሸውን ግንኙነት ወዲያውኑ ለመጠገን ጥረት ማድረጋቸው ነው።
ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታደለ ቢሆንም በስሜት ብልህነት በኩል ግን ትልቅ ፈተና ተደቅኖበታል። የዚህ ትውልድ ዋነኛ የስሜት ስብራት ምንጮች የሚከተሉት ናቸው።
- ፈጣን እርካታ፦ የኢንተርኔት ፍጥነት፣ የምግብ ማዘዣ መተግበሪያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ “ላይክ” ትውልዱን ትእግስቱ እንዲጠፋ አድርገውታል። በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ግን ትእግስት እና ጊዜ ያስፈልጋል።
- መሰወር (Ghosting) እና በቀላሉ መተው፦ አለመግባባት ሲፈጠር ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ ሌላውን ሰው በሶሻል ሚዲያ “Block” ማድረግ ወይም “Ghost” ማድረግ የተለመደ ሆኗል። ይህ የስሜት ማሸሽ መገለጫ ነው።
- ዲጂታል ረብሻ እና ትኩረት ማጣት፦ ባልና ሚስት ወይም ፍቅረኛሞች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ስልካቸውን ሲጎረጉሩ ይታያሉ። ይህ ለሌላው ሰው “አንተ ለእኔ ዋጋ የለህም” የሚል የስሜት መልእክት ያስተላልፋል።
የስሜት ብልህነት በተፈጥሮ የሚሰጥ ስጦታ ሳይሆን በጥረትና በልምምድ የሚያድግ ክህሎት ነው። የአሁኑ ትውልድ በግንኙነቶቹ ውስጥ ስሜቱን የሚገዛበት እና EQ ውን የሚያሳድግበት አምስት ወርቃማ ደረጃዎች እኚህ ናቸው፡
ሀ. የ90 ሰከንድ ሕግን መተግበር፦
በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ሳይንቲስት የሆኑት ዶ/ር ጂል ቦልቴ ቴይለር “ማይ ስትሮክ ኦፍ ኢንሳይት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት አእምሯችን ለቁጣ ወይም ለፍርሃት ምላሽ ሲሰጥ የሚለቀቀው ኬሚካል በደማችን ውስጥ የሚቆየው ለ 90 ሰከንድ ብቻ ነው።
ከ 90 ሰከንድ በኋላ ቁጣው ቀጣይነት የሚኖረው እኛ በአእምሯችን በምናስበው አሉታዊ ሀሳብ ኬሚካሉን እንደገና እየመገብነው ስለሆነ ብቻ ነው።
ንዴት ሲመጣ ወዲያውኑ መልስ አትስጥ። ጥልቅ ትንፋሽ እየወሰድክ እስከ 90 ሰከንድ ቁጠር። ያን ጊዜ የአሚግዳላ ጠለፋው ስለሚቆም አእምሮህ በሎጂክ ማሰብ ይጀምራል ይላሉ ሳይንቲስቱ።
ለ. ስሜትን ስም መስጠት፦
የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና ፕሮፌሰር ዶ/ር ዳን ሲገል “ኔም ኢት ቱ ቴም ኢት” የሚል ፅንሰ-ሐሳብ አላቸው። ስሜታችንን በቃላት ስንገልጸው የአእምሯችን አስተዋይ ክፍል ይነቃቃና ስሜታዊው ክፍል ይረጋጋል።
“አንተ/አንቺ አስደንግጠኸኛል/ሽኛል” ብለህ/ሽ ከመጮህ ይልቅ፣ በእርጋታ ራስህን ሕሊናህ ውስጥ ጠይቅ። “አሁን ምን ይሰማኛል? ፍርሃት? የዋጋ ቢስነት ስሜት? ወይስ ንዴት?” ስሜቱን ለራስህ ስም ስትሰጠው ኃይሉ ይቀንሳል ይላሉ የስነልቦና ይሮፌሰሩ።
ሐ. ከ”አንተ/አንቺ” ውንጀላ ወደ “እኔ” አገላለፅ መቀየር፦
ጆን ጎትማን እንደሚያስረዱት አለመግባባትን በለሰለሰ መንገድ መጀመር የግንኙነትን እድሜ ያራዝማል።
“አንተ ሁልጊዜ አትደውልልኝም! ግዴለሽ ነህ!” የሚለው የተሳሳተ እና የወቀሳ ንግግር ነው። ከዚያ ይልቅ “እኔ ቀኑን ሙሉ ስላልተነጋገርን ብቸኝነት ተሰምቶኛል፤ ብትደውልልኝ ደስ ይለኛል” የሚለው ይስሜት ብልህነት የተሞላበት ንግግር ነው።
የመጀመሪያው መንገድ የሌላኛውን ሰው ተከላካይነት የሚቀሰቅስ ሲሆን ሁለተኛው ግን የራስን ስሜት በቅንነት መግለጽ ነው።
መ. ንቁ አዳማጭ መሆን፦
አብዛኛው ሰው የሚያዳምጠው መልስ ለመስጠት እንጂ ለመረዳት አይደለም። ባልደረባህ/ሽ ሀሳቧን/ቡን ሲገልጽ/ስትገልጽ፤ አእምሮህ ቀጣዩን መከላከያ መልስ ሲያዘጋጅ ከቆየ አዳማጭ አይደለህም።
ስልክህን አስቀምጥ። ዓይን ለዓይን ተናበብ። ንግግሩን ሲጨርሱ እንዲህ በል/በይ፦ “እሺ፣ እንደተረዳሁት ከሆነ አርፍጄ በመምጣቴ ምክንያት አልተከበረሁም ብለሽ ስላሰብሽ አዝነሻል፤ ትክክል ነኝ?” ይህ ሌላው ሰው “ተሰምቼአለሁ” የሚል ታላቅ የስሜት እርካታ እንዲሰማው ያደርጋል።
ሠ. ዲጂታል ጾም እና ማይንድፉልነስ፦
በቀን ውስጥ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ስልክን አጥፍቶ ከአጋር ጋር ጥራት ያለው ጊዜ ማሳለፍ። ማህበራዊ ሚዲያ የሚያመርተውን የንፅፅር እና የትዕግስት ማነስ በሽታ ለመፈወስ ከዲጂታል ዓለም እረፍት መውሰድ እና በአሁኑ ቅጽበት (Present Moment) መኖርን መልመድ ይገባል።
የስሜት ብልህነት ትዕግስትን እና ብናገር ወይም ባደርግ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ለሰከንድ ቆም ብሎ የማሰብ ችሎታ ነው። ችሎታው በልምምድ የሚዳብር ነው።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


