“ሰኔን ያላረሰ ሐምሌን ዘር ያልዘራ፣
አብቅሎም አያጭድ አይሞላም ጎተራ!” የሚለው ስንኝ የክረምት መግባትን ተከትሎ ተደጋግመው ይስተጋባሉ፤ ምክንያቱም ደግሞ የክረምቱን መግባት ተከትሎ አርሶ አደሮች ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ማሳቸው የሚያደርጉበት ወሳኝ ወቅት በመሆኑ ነውና፡፡
ክረምት ለኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች የነገው የጥጋብ ዘመን መሠረት የሚጣልበት፣ ማረሻ እና በሬው የሚዋሀዱበት የተስፋ ጊዜ ነው። የዘንድሮው የክረምት እርሻ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? አርሶ አደሩስ ለዚህ ወሳኝ ወቅት ምን ያህል ተዘጋጅቷል?” የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት በኩር ጋዜጣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን ሐሳብ የስልክ ቅኝት አድርጋለች።
ከእነዚህ አርሶ አደር መካከል በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር አስራት አሸናፊ አንዱ ናቸው። አርሶ አደሩ በስልክ እንዳብራሩት በአሁኑ ወቅት የክረምቱ ዝናብ ስርጭት እጅግ ተስማሚ እና የተስተካከለ መሆኑን ተከትሎ የሰብል እንክብካቤ ሥራዎችን በስፋት እያከናወኑ ይገኛሉ።
አርሶ አደር አስራት በዘንድሮው የምርት ዘመን በአምስት ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን እያለሙ ይገኛሉ። እያለሙት ከሚገኙ ሰብሎች መካከል ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ድንች፣ ዳጉሳ እና በርበሬ በዋናነት ይጠቀሳሉ። እስካሁንም አንድ ሄክታር በቆሎ፣ አንድ ሄክታር ስንዴ እና ሁለት ቃዳ (ግማሽ ሄክታር) ድንች የዘሩ ሲሆን የበርበሬ ተከላንም አጠናቀው ወደ እንክብካቤ ተሸጋግረዋል።
በቀጣይም የጤፍ እና የዳጉሳ ማሳቸውን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዳላጋጠማቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ እስካሁንም አምስት ኩንታል ዳፕ እና ሦስት ኩንታል ዩሪያ ገዝተው በማሳቸው ላይ ተጠቅመዋል። ለጤፍ እና ለስንዴ ሰብል የሚሆን ተጨማሪ ማዳበሪያ በቀጣይ እንደሚገዙም ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ ጊዜን እና ጉልበትን ለመቆጠብ ዘመናዊ የእርሻ ትራክተርን እየተጠቀሙ ይገኛሉ። “የበቆሎውን እና የበርበሬውን ማሳ ጨምሮ ወደ ሁለት ሄክታር የሚጠጋውን መሬት ያረስኩት በትራክተር ነው” ያሉት አርሶ አደር አስራት ቀሪውን በበሬ በማረስ ባሕላዊ እና ዘመናዊ አሠራርን አጣምረው እየሠሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላው ሐሳባቸው ያካፈሉን በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ደለሎ በተሰኘው አካባቢ የእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት አርሶ አደር ሀብቱ ፀዱ ናቸው፤ የዘንድሮው የክረምት እርሻ ሥራቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አቶ ሀብቱ እስከ 700 ሄክታር የሚደርስ ማሳ እያለሙ ይገኛሉ። በምርት ዘመኑ ጥጥ፣ አኩሪ አተር እና ሰሊጥ በስፋት የዘሩ ሲሆን የእርሻ ሥራቸውንም በራሳቸው ትራክተር ነው ያረሱት።
እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ የዘንድሮው ክረምት ዝናብ መግባት ከነበረበት ጊዜ ጥቂት ዘግየት ብሎ የጀመረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ግን የተስተካከለ እና ለእርሻ ሥራው ምቹ የዝናብ ስርጭት አለ።
ሆኖም ዝናቡ በመዘግየቱ ምክንያት ቀደም ብሎ ተዘርቶ የነበረው ዘር በመበላሸቱ ድጋሚ ለመዝራት መገደዳቸውን አስታውቀዋል። አርሶ አደሩ ለዘንድሮው እርሻቸው ከ350 እስከ 400 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ (ዳፕ እና ዩሪያ) እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል።
አቶ ሀብቱ በመጨረሻም አካባቢው እጅግ ለም እና ሀገርን ሊመግብ የሚችል አቅም ያለው ቢሆንም፤ የመንገድ እና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ሥራቸውን ፈታኝ እንዳደረገው ጠቁመዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ እንዳስታወቀው በዘንድሮው የመኸር እርሻ በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰፊ የእርሻ መሬት በዘመናዊ መንገድ ታርሶ በዘር ተሸፍኗል። በአንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተው የዝናብ መቆራረጥ አርሶ አደሩን ለስጋት ቢያጋልጠውም ዞኑ 12 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ በማቀድ እየሠራ ይገኛል።
በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ከበኩር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንዳብራሩት በዘንድሮው የመኸር እርሻ 542 ሺህ 364 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል። በዚህም ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ እና ጥጥ ከፍተኛ ሽፋን ይዘዋል።
አቶ ሞገስ እንደገለጹት በዞኑ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ታቅዶ የነበረ ሲሆን 774 ትራክተሮችን በማሰማራት 403 ሺህ 307 ሄክታር ማረስ ተችሏል። በተጨማሪም ምርታማነትን ለማሳደግ የክላስተር (የኩታ ገጠም) እርሻ በስፋት እየተተገበረ ይገኛል። ከ314 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ለምቷል፡፡
የግብዓት አቅርቦትን በተመለከተም ከ39 ሺህ 273 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ታቅዶ 33 ሺህ 311 ኩንታል ለዞኑ ቀርቧል፡፡ ከ13 ሺህ 355 ኩንታል በላይ ዳፕ እና ዩሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ ውሏል።
እንደ አቶ ሞገስ ማብራሪያ ከሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የዝናብ ስርጭቱ እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ነው። በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው ሰብል የተሻለ የዕድገት ደረጃ ላይ ይገኛል። በቀጣይም የተዘራውን ሰብል በአግባቡ ለመንከባከብ የአረም ሥራ እና የተባይ ቁጥጥር በከፍተኛ ትኩረት ይከናወናል።
አቶ ሞገስ እንዳስገነዘቡት እስከ ቀበሌ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር በመቀናጀት የክትትል ሥራ እየሠሩ ነው። “በክልል ደረጃ የምትፈልጉት ድጋፍ አለ ወይ?” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ “በአሁኑ ሰዓት መደበኛ የእርሻ ሥራ በራሳችን ባለሙያዎች እና አቅም እየተፈታ ያለ ነው። ሆኖም ወደፊት እንደ አንበጣ ወይም መጤ ትል የመሳሰሉ ድንገተኛ የተባይ ወረርሽኞች ከተከሰቱ የኬሚካል ድጋፍ ሊያስፈልገን ይችላል” በማለት መልሰዋል።
በተመሳሳይ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ በተያዘው መኸር እርሻ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። የመምሪያው ኃላፊ ቤዛዊት ጌታሁን እንደገለጹት፤ በተያዘው የመኸር ወቅት ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሠራ ነው።
በመኸር እርሻው እስካሁን 266 ሺህ 453 ሄክታር መሬት በበቆሎ፣ ስንዴ፣ ሰሊጥ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር እና በሌሎች ሰብሎች ዘር ተሸፍነዋል። ሰብልን በኩታ ገጠም አሠራር በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው። ከ170 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የተሸፈነ መሆኑንም አብነት አንስተዋል። 60 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ ትራክተር በመጠቀም የእርሻ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
በተመሳሳይ 517 ሺህ 864 ኩንታል ማዳበሪያ እና 26 ሺህ 234 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት ተችሏል።
በተያዘው የምርት ዘመን 422 ሺህ 480 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 17 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ኃላፊዋ አስታውቀዋል። ምርታማነትን ለማሳደግ የዘር ጥራትን መጠበቅ ፣ ዘርን በወቅቱ መዝራት ከአርሶ አደሩ እና ከባለሙያዎች እንደሚጠበቅ ወ/ሮ ቤዛዊት አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2018/19 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ ከ205 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርና ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ በከፍተኛ ንቅናቄ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። የእርሻ ሥራን በማዘመን እና የክላስተር አሠራርን ለማስፋፋት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጿል።
የቢሮዉ የሰብል ልማት ባለሙያ ወ/ሮ እንዬ አሰፋ ለበኩር እንደገለጹት፣ በክልሉ በዘንድሮው መኸር እርሻ አምስት ሚሊዮን 589 ሺህ 28 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ፤ አፈፃፀሙ ከዕቅድ በላይ አምስት ሚሊዮን 618 ሺህ 874 ሄክታር መሬት ለእርሻ ዝግጁ ማድረግ ተችሏል።
እስካሁንም አራት ሚሊዮን 78 ሺህ 230 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ባለሙያዋ አስታውቀዋል። በዋናነትም በቆሎ፣ የምግብ ገብስ፣ ዳጉሳ፣ ማሽላ እና ቦሎቄ የተዘሩ ሲሆን ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሩዝ የመሳሰሉ ሰብሎችም በስፋት እየተዘሩ ይገኛሉ።
ክልሉ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የትራክተር እርሻን በስፋት እየተገበረ ይገኛል። ባለሙያዋ እንዳብራሩት አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ ታቅዶ እስካሁን አንድ ነጥብ ሦሥት ሚሊዮን ሄክታር ማረስ ተችሏል። በተለይም እንደ ወልቃይት እና ምዕራብ ጎንደር ባሉ ሰፊ የእርሻ አቅም ባላቸው አካባቢዎች ሁለት ሺህ 839 ትራክተሮች በሥራ ላይ ውለዋል።
በክልሉ ያለው የዝናብ ስርጭት ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ መልክ ያለው መሆኑን ያነሱት ባለሙያዋ በአንዳንድ አካባቢዎች በቂ፣ በሌሎች መካከለኛ፣ በአንዳንዶቹ ደግሞ እጥረት የሚታይበት ስለመሆኑ ጠቁመዋል። በተለይም ከሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የዝናብ ስርጭቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ባለሙያዋ ጠቁመዋል።
የዝናቡን ፀባይ እና ያለውን የቀሪ የዘር ጊዜ ግምት ውስጥ በማስገባት አርሶ አደሩ ጥንቃቄ የተሞላበት አሠራር እንዲከተል ባለሙያዋ መክረዋል። በተለይም በቀሪ ጊዜያት ቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎችን እንዲዘሩ ጥሪ አቅርበዋል።።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


