አራት ዐሥርት ዓመታትን የተሻገረው ጠላትነት

0
156

በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው የአሜሪካና የኢራን ጦርነት በቅርብ ዓመታት ከታዩት እጅግ አደገኛ ወታደራዊ ግጭቶች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ግጭቱ በሁለቱ ሀገራት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በቀጣናው የሚገኙ በርካታ ሀገራትን፣ የዓለም የነዳጅ ገበያን፣ የባሕር ንግድ መስመሮችንና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በቀጥታ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡የጦርነቱ መነሻ አንድ ክስተት ብቻ አልነበረም፡፡ለበርካታ ዓመታት የተከማቸ የፖለቲካ፣ የደኅንነት እና የወታደራዊ ውጥረት  ተደምሮ ወደ ጦርነት ሊቀየር ችሏል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው እ.አ.አ ከ1979 ከኢራን እስላማዊ አብዮት ጀምሮ የአሜሪካና የኢራን ግንኙነት በእምነት፣ በፖለቲካ፣ በደኅንነት እና በክልላዊ ተፅዕኖ ላይ የተመሠረተ ከባድ የፉክክር ማዕከል ሆኖ ቆይቷል፡፡ይህ ፉክክር ታዲያ በቀጥታ በወታደራዊ ዘመቻ፣ በኢኮኖሚ ማዕቀብ፣ በሳይበር ጥቃትና በውክልና ጦርነቶች በኩል ወደ ተወሳሰበ የኃይል ፉክክር ተቀይሯል፡፡

የግጭቱ መነሻ

እ.አ.አ በ1979 የኢራን አብዮት በአሜሪካ የሚደገፈውን የሺሃ መሐመድ ሪዛ ፓህላቪ መንግሥትን አስወግዶ በአያቶላህ ሩሆላህ ኻሜኒ የሚመራውን እስላማዊ ሪፐብሊክ መሥርቷል፡፡ በዚያው ዓመት የአሜሪካ ኤምባሲ በቴህራን በአጋቾች ተወርሮ 52 አሜሪካዊያን ለ444 ቀናት ታግተው እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ይህ ክስተትም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አሻክሯል፡፡

እ.አ.አ ከ2000ዎቹ ጀምሮ ተደጋጋሚ የሁለቱ ሀገራት የውጥረት ምንጭ የሆነው ደግሞ የኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም ነው፡፡

በተጠቀሱት ዓመታት ኢራን የዩራኒየም ማበልፀጊያ ፕሮግራሟን አጠናክራ ቀጥላ ነበር፡፡አሜሪካና አውሮፓዊያን ደግሞ ኢራን ኒውክሌሩን የምታበለጽገው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመሥራት ነው በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡

ኢራን ግን ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለሕክምና እና  ለምርምር  ብቻ መሆኑን ስትናገር ቆይታለች፡፡ እ.አ.አ በ2015 በተፈረመው የኒውክሌር ስምምነት ውጥረቱን ለመቀነስ ቢሞክርም አሜሪካ እ.አ.አ በ2018 ከስምምነቱ ከወጣች በኋላ ውጥረቱ እንደገና ተባብሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤልም በግጭቱ አንዷ ተሰላፊ ሆናች፤ እስራኤል ኢራንን በክልሉ ላይ ትልቁ የደኅንነቴ ስጋት ናት የሚለው ደግሞ በእስራኤል በኩል የሚነሳው ምክንያት ነው፡፡

ኢራን ከእስራኤል ጋር የሚዋጉትን የሂዝቦላህን፣ የሃውቲዎችን እና ሌሎች የታጠቁ ቡድኖችን ትደግፋለች የሚል ክስ በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ይህን መነሻ በማድረግ ደግሞ አሜሪካ ለእስራኤል  ጠንካራ  የደኅንነት ድጋፍ ትሰጣለች፡፡ ይህም የአሜሪካ – ኢራን ግንኙነትን የበለጠ ያወሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ኃያላኑ ሩሲያና ቻይና ከኢራን ጋር  የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት አላቸው፡፡ ሁለቱ ኃያላን ሀገራትም በተደጋጋሚ ግጭቱ በውይይት እንዲፈታ ይጠይቃሉ፤ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ከኢራን ጋር የንግድና የስትራቴጂ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ነው፡፡

የአረብ ሀገራት አቋምን በምናይበት ጊዜም  የባሕረ ሰላጤ ሀገራት የሆኑት ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በአንድ በኩል ከአሜሪካ ጋር የደኅንነት ግንኙነት ያላቸው ሲሆን በሌላ በኩል ግጭቱ እንዳይሰፋ ያለሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ጦርነቱ ያስከተለው ጉዳት

ጦርነቱ በሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድምትን አስከትሏል፡፡የኢራን መንግሥት እንዳስታወቀው በአሜሪካና በእስራኤል ጥቃቶች ከሦስት ሺህ 400 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ26 ሺህ በላይ ቆስለዋል፡፡

በእስራኤል በኩል በኢራን የሚሳይል ጥቃቶች 26 ያህል ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡በአሜሪካ ወታደሮች እና ተቋሞች ላይም በቀጥታ የደረሱ ጥቃቶች ቢኖሩም በዚህ ግጭት የሞቱ የአሜሪካ ወታደሮች ትክክለኛ ቁጥር ከመላምት ውጪ በይፋ  በአሜሪካ መንግሥት በኩል አልተገለጸም፡፡

ጦርነቱ በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን

በኢራን የኒውክሌር ተቋማት፣ የወታደራዊ ማዕከላት፣ የነዳጅ ማከማቻዎችና የመጓጓዣ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡በአሜሪካ በኩል በቀጣናው ያሉ የጦር ሰፈሮቿን ለማጠናከር፣ የአየር ጥቃቶችን ለማካሄድና ተጨማሪ ኃይል ለማሰማራት በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች አውጥታለች፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው ኢራን የደረሰባትን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ለጥቃት የተጠቀመችባቸው በበርካታ ሀገራት በሚገኙ የጦር ሰፈሮች ላይ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት ፈጽማለች፡፡በኳታር፣ ባሕሬን፣ ኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኦማን፣ በሶሪያ እና በቆጵሮስ የሚገኙ የምዕራባዊያን ወታደራዊ ተቋማት የጥቃት ዒላማ እንደነበሩ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

በአጠቃላይ እ.አ.አ የ2026 የአሜሪካ – ኢራን ግጭት በሁለት ሀገራት መካከል የተካሄደ ብቻ ሳይሆን መላውን መካከለኛው ምሥራቅ ያካለለ የደኅንነት ቀውስ ሆኖ ታይቷል፡፡

ጦርነቱ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ

መካከለኛው ምሥራቅ የዓለም የነዳጅ ምርት ዋና ማዕከል ነው፤ ግጭቱ ታዲያ በዓለም ገበያ ላይ ፈጣን ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡የዓለምን ነዳጅ 20 በመቶ ያህሉ የሚተላፍበት የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ መስመር ደኅንነት አደጋ ውስጥ በመግባቱ የነዳጅ ዋጋ ከፍ ብሏል፡፡ሰርጡ በተደጋጋሚ በመዘጋቱ የመርከብ መድን ወጪ ጨምሯል፤ የንግድ መርከቦች ጉዞም ተስተጓጉሏል፡፡

ይህ ለነዳጅ አስመጪ ሀገራት የነዳጅ ወጪ እንዲጨምር፣ የዋጋ ንረት እንዲባባስና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲዘገይ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ ሀገራትም አብዛኛውን የነዳጅ ፍላጎታቸውን ከውጭ ስለሚያሟሉ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨመር በቀጥታ ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል፡፡ይህም የነዳጅ ወጪን፣ የትራንስፖርት፣ የምግብ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪ ጫና ያለባቸው ሀገራት ከፍተኛ የማስመጫ ወጪን ለመሸከም ተገድደዋል፡፡

ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች

አሜሪካና ኢራን እ.አ.አ ከ1979 የኢራን እስላማዊ አብዮት በኋላ በጠላትነት የተሞላ ግንኙነት ቢኖራቸውም በተለያዩ ወቅቶች ውጥረቱን ለማርገብና ወደ ድርድር ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶች አልተቋረጡም፡፡በእነዚህ ጥረቶች ውስጥ ኦማን፣ ስዊዘርላንድ፣ ኳታር፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለያየ ደረጃ የሽምግልና ሚና ተጫውተዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ኦማን ከሁሉም በላይ የሁለቱ ሀገራት እምነትን ያተረፈች አደራዳሪ ሀገር በመሆን ትጠቀሳለች፡፡የሁለቱ ሀገራት የመጀመሪያው ይፋዊ የመቀራረብ ጥረት እ.አ.አ በ2001 በጀርመን ቦን በተካሄደው የአፍጋኒስታን የወደፊት ሥርዓት ውይይት ላይ ታይቷል፡፡በዚያ ሂደት አሜሪካና ኢራን በቀጥታ ባይደራደሩም የታሊባን አገዛዝ ከተወገደ በኋላ የአፍጋኒስታን አዲስ መንግሥት እንዲቋቋም በተዘዋዋሪ ትብብር አድርገዋል፡፡ይህም እ.አ.አ ከ1979 በኋላ የተመዘገበ አስፈላጊ የዲፕሎማሲ መነሻ እንደነበር ይነገራል፡፡

ከዚያም እ.አ.አ በ2007 እና 2008 በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቀጥታ ተገናኝተው በኢራቅ የደኅንነት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡በውይይቱ የተወሰነ መግባባት ቢታይም ቋሚ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡

የዲፕሎማሲ ድርድሩ የታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተው ግን እ.አ.አ ከ2012 ጀምሮ በኦማን ዋና ከተማ ሙስካት በተካሄዱ ምስጢራዊ ውይይቶች ነው፡፡በኦማን ሱልጣን ቃቡስ አማካይነት የተጀመሩት እነዚህ ውይይቶች በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም እና አሜሪካ በኢራን ላይ በተጣሉ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ይህ ሂደት እ.አ.አ በ2013 ወደ ይፋዊ ድርድር ተሸጋግሮ በጄኔቫ፣ በሎዛንና በቪየና በአውሮፓ ሕብረት አስተባባሪነት ተካሂዷል፡፡

አሶሼትድ ፕረስ እንደዘገበው የእነዚህ ውይይቶች ትልቁ ውጤት እ.አ.አ በ2015 የተፈረመው የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ኢራን የዩራኒየም ማበልፀጊያ ሥራዋን ገደበች፤ የዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ተቆጣጣሪዎች ተቋሞቿን እንዲመረምሩም ፈቀደች፡፡በምላሹ አሜሪካና ሌሎች ሀገራት የተወሰኑ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ለማንሳት ተስማምተዋል፡፡ይህ እስካሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ትልቁና ታሪካዊው ስምምነት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ2018 አሜሪካ ከስምምነቱ መውጣቷና ከባድ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ኢራን ላይ እንደገና መጣሏ ውጥረቱን አባብሶታል፡፡

እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ በቪየና ስምምነቱን ለማደስ በአውሮፓ ሕብረት አስተባባሪነት ተከታታይ ውይይቶች ቢደረጉም የመጨረሻ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡በቅርብ ዓመታትም ኦማን እና ኳታር በተለይ በእስረኞች ልውውጥ፣ የታገደ የኢራን ገንዘብ እንዲለቀቅ እና በኒውክሌር ጉዳይ ዙሪያ የተዘዋዋሪ ድርድሮችን በማስተናገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ስዊዘርላንድም በሁለቱ ሀገራት መካከል የዲፕሎማሲ መልዕክቶች እንዲተላለፉ ስትሠራ የቆየች ገለልተኛ ሀገር ናት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተደረጉ ውይይቶች ተስፋ የሰጡ ቢመስሉም የተፈለገውን ውጤት ግን አላስገኙም፤ የኢራን የሚሳኤል ፕሮግራም፣ ኢራን ለታጣቂ ቡድኖች የምትሰጠው ድጋፍ፣ የአሜሪካ ማዕቀቦችና የቀጣናው የደኅንነት አወቃቀር ሁለቱን ሀገራት የሚያለያዩ ዋና ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል፡፡ይህም አሜሪካና ኢራን አሁንም ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ ለማግኘት ሩቅ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ከጥይት ድምጽ ርቆ በነበረው መካከለኛው ምሥራቅ ግጭቱ አገርሽቷል፤ ለግጭቱ እንደገና መቀስቀስ ደግሞ አንዱ ሌላኛውን ነው ተጠያቂ የሚያደርጉት፡፡

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 27-11-2018  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here