የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በተቀመጡት ስምንት አጀንዳዎች ላይ በንዑስ ቡድኖች የሚደረገውን ውይይት በማጠናከር ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገሩን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ አስታውቀዋል፡፡
እንደሚታወቀው ሀገራዊ ምክክር አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበት የፖለቲካ እና የማሕበራዊ መደላደል የሚመቻችበት እንዲሁም ሕብረተሰቡን አላግባባ ያሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመምከር ሀገራዊ መግባባት ላይ እንደሚያደርስ ይታመናል፡፡የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ከተቋቋመ በኋላ ለአራት ዓመታት በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮችን በይፋ በማካሄድ ሕብረተሰቡ ለሀገራዊ ምክክሩ መነሻ ይሆናሉ ያላቸውን አንኳር ጉዳዮች በነፃነት እንዲያቀርብ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ዲያስፖራውንና የተለያዩ የሞያ ማሕበራትን ያሳተፉ የቪዲዮ ኮንፈረንስና የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮችንም አዘጋጅቶም ነበር፡፡እነዚህን ሥራዎችን ሲያከናውን ከቆየ በኋላም አሁን ላይ 4ሺህ ሰዎችን ስለኢትዮጵያ እንዲመክሩ አዲስ አበባ እንዲከትሙ ካደረገ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡
አሁን ላይ የኢትዮጵያ የሐገራዊ ምክከር ጉባኤ አዲስ ምዕራፍ ላይ የገባ ሲሆን ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በፀደቁት ስምንት አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ስምንቱ አጀንዳዎችም የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የውክልናና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች እና የተቋማት ግንባታ፣ በተጨማሪም በሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ በማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ዕጣ ፈንታ፣ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር እንዲሁም በሰላም ግንባታ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በድረ ገጹ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤታቸውን እና ማሕበራዊ ውላቸውን ሊያንጹ የሀሳብ የበላይነትን ማዕከል አድርገው እየተመካከሩ ናቸው፡፡ኮሚሽኑ እንደገለጸው በምክክር ጉባኤው በርካታ አመለካከቶች በምክንያት እየቀረቡ እና ተቃራኒ ሀሳቦች በአመክንዮ እየተስተናገዱ ነው፡፡አንዱ የሌላውን ብሶት እያዳመጠ ቀስ በቀስ የመግባባት ጎዳና እየተጠረገ ነው፡፡በዚህም ኢትዮጵያዊያን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰላማዊ መንገድ መነጋገር እንደሚችሉ በተግባር እየታየ ነው፡፡ኢትዮጵያ መሸከም የማትችለው ግጭትና አለመግባባትን እንጂ መመካከርን እንዳልሆነ ልጆቿ እያስመሰከሩ ይገኛሉ፡፡አላግባባ እና ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ በመለየት የመፍትሔ ሀሳቦች እየቀረቡ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊያን የመንግሥት አስተዳደርን፣ ማሕበራዊ ቁርኝትን፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን፣ ፍትሕ እና ርትዕን የተመለከቱ ቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮችን አንስተው መወያየታቸው በዘላቂነት የሀገር ባለቤትነት ስሜታቸውን እንደሚያጠናክር ኮሚሽኑ ያለውን እምነት አንጸባርቋል፡፡
ኮሚሽኑ እንደሚለው ተመካካሪዎች የሀሳብ ገደብ ሳይኖርባቸው የውስጣቸውን ስሜት አውጥተው እየተናገሩ ነው፡፡ የሚነሱ ሀሳቦች በርካታ ቢሆኑም ማዕከላቸውን ሀገር ላይ በማድረግ ተመካካሪዎች አካታችነትን፣ መደማመጥን እና አመክንዮን አንግበው እየተጓዙ መሆናቸውን ነው የጠቆመው፡፡
በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ዕይታዎችን በአንድ የጋራ አቋም ለማቀናጀት የሚደረገው ሂደት ለጉባኤው የመጨረሻ ግብ የሆነውን መግባባት ለማሳካት ወሳኝ እንደሆነም የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕ/ሮ) የገለጹ ሲሆን 10 አባላት ባሉት ጥቃቅን ቡድኖች ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ውይይት ተጠናክሮ በመቀጠል የተሰበሰቡት ሐሳቦች በሰብሳቢዎችና በጸሐፊዎች አማካኝነት 50 አባላት ላሉት ንዑስ ቡድኖች ቀርበው ተጨማሪ ውይይት ካደረጉባቸው በኋላ ሐሳቦቹ ተጨማሪ 250 አባላት ላሉት ስልታዊ ቡድኖች ቀርበዋል፡፡ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም በነበረው የምክክር ውሎም ከእያንዳንዱ ስልታዊ ቡድን በተመረጡ 25 የአጀንዳ ምክረ ሐሳብ አጠናቃሪዎች አማካኝነነት የተጠናቀሩ ምክረ ሐሳቦችን ያዳመጠው 16ቱ ባለ 250 አባላት ስልታዊ ቡድን በጥቃቅንና በንዑስ ቡድኖች ተነስተው በቀረበው ቃለ ጉባዔ ላይ ያልተካተቱ እና በአግባቡ ያልተብራሩ ያላቸውን ሐሳቦች አቅርቧል፡፡በስልታዊ ቡድኖቹ የተሰጡ አስተያየቶች ተካተውበት በድጋሚ የተደራጀውን ቃለ ጉባዔ የጋራ በማድረግ በቀጣይ ለሚደረገው እና 500 ተመካካሪዎችን ለያዙ ስምንት የምክክር ቡድኖች ለማቅረብ ዝግጅት አድርገዋል፡፡
እስካሁን ባለው የምክክር ሂደትም ተመካካሪዎቹ በመከባበር፣ በመደማመጥና በነፃነት ሐሳባቸውን እያቀረቡ መሆኑንም ነው ዋና ኮሚሽነሩ ያስታወቁት፡፡
የተሳታፊዎች አደረጃጀት ፍትሐዊነትን የተላበሰ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ በምክክር መድረኩም የተለያዩ አካላት ፍትሐዊ ውክልና አግኝተዋል፡፡ በቡድን ድልድሉ ወቅት የተፈጠሩ ክፍተቶችን በቴክኖሎጂ በማረም በእያንዳንዱ አጀንዳ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተመጣጠነ ውክልና እንዲኖራቸው መደረጉንም ነው የተናገሩት፡፡
እስካሁን ያለው የጉባኤው ሂደትም አበረታች መሆኑን የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነሩ ሀገራዊ ምክክሩ በውይይትና በመግባባት ለኢትዮጵያ ዘላቂና አዋጭ መፍትሔ ለማምጣት አስፈላጊ ሂደት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች መካከከል አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት ተመካካሪ ኮሎኔል ፈንታሁን ሙሀቤ የችግሮች መፍቻ መንገድ ምክክር መሆኑን እና አሁን ከኃይል አማራጭ በመውጣት ቅራኔዎችን በውይይት ለመፍታት ጥረት የማድረጊያው ግዜ እንደሆነ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡“በጦርነት እያጣን ያለዉ የሰዉ ሕይወት በመሆኑ ከጦርነት ወደ ምክክር መምጣታችን ለሀገር ሰላም የተወሰደ መፍትሄ ነው” ሲሉ የተደመጡት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ጄኔራል ዮሐንስ ገ/መስቀል ናቸው፡፡
ኃይለኪሮስ ረዳኢ የተባሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመካካሪም “ባለመመካከራችን በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ እልቂት አጋጥሞናል ይህንን ላለመድገምም በልዩነቶቻችን ላይ መምከር ይገባናል” ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን መሠረታዊና መዋቅራዊ ችግሮችን በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ መግባባት በመፍጠር መፍትሔ በመስጠት ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ለሕዝብ ጥያቄዎች ዘላቂ ምላሽ ለመስጠትና መግባባት ለመፍጠርም ወሳኝ ዕድል ነው፡፡
በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን በማጎልበት የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍም ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡የምክክር ጉባኤው ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችን ለቀጣዩ ትውልድ እንዳይተላለፉ ለማድረግ ያስችላል፡፡
በዚህ ሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ለሀገር የሚበጁ መፍት ሔዎችን በጋራ እየቀረጹ ይገኛሉ፡፡ ምክክሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ኢትዮጵያዊያንን በማቀራረብ የመተማመንና የአብሮነት መንፈስን እያጠናከረም ነው፡፡በሕዝቦች መካከል ፍቅርን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ይዞ እንደሚመጣ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ሰላምና የልማት ምዕራፍ ለማሸጋገር ታላቅ ተስፋም ተጥሎበታል፡፡ተሳታፊዎች እንዳሉት ደግሞ መድረኩ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል አስተማማኝ መሰረት ይጥላል፡፡
ምክክሩ ሁሉንም የማሕበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች የተካተቱበት በመሆኑ ተመካካሪዎቹ በነፃነትና በእኩልነት እንዲመክሩ አስችሏቸዋል፡፡ ሀገርን ሊገነቡ፣ ሊያጠናክሩና ሀገራዊ መግባባት ሊያመጡ የሚችሉ ሐሳቦችን ያለ ምንም ገደብ በነፃነት እየተስተናገደበት ይገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምክክር ሂደቱ በተመካካሪዎች አባላት አካራካሪ እና ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ከተከሰቱ መቋጫ እንዲያገኙ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ሚና የሚኖራቸውን 336 የጉባኤ አባላት በተመካካሪዎች ተመርጠዋል፡፡ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው በምክክር ሂደቱ ሁሉም ርዕሰ ጉዳዮች ወደ ጉባኤ ለውሳኔ አይቀርቡም፡፡ርዕሰ ጉዳዮቹ ለውሳኔ እንዲቀርቡ የሚደረገው በሥራ ቡድን ደረጃ የተወሰነ ውሳኔ ቢያንስ ሦስት ክልሎች ጉዳዩ በክልል ተወካዮች ጉባዔ እንዲታይና እንዲወስን ግልፅ የሆነ ጥያቄ ለኮሚሽኑ ሲያቀርቡ ከአስማሚ ግብረ-ኃይል ጥረት በኋላ በሥራ ቡድን ደረጃ የሚፈለገው ድምፅ ባለመገኘቱ ምክንያት ውድቅ የተደረገ ጉዳይ ሲኖር እና ጉዳዮች የሕዝቦችን እሴት፣ ማንነት እና ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ ሲታመንበት እንደሆነ ኮሚሽኑ ባስቀመጠው የውሳኔ አሰጣጥ መመሪያ ላይ ተመላክቷል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


