የሰብዓዊነት መገለጫ

0
186

የበጎ ፈቃድ ሥራ (Volunteering) ከጥንት ጀምሮ በሁሉም የሰው ልጆች ዘንድ እያደገ የመጣ ባሕል ነው፤ በዘመናዊ እና በተደራጀ መልኩ መጠናከር የጀመረው ደግሞ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ መሆኑን  ቮለንቲር አልቤርታ (www.volunteeralberta.ab.ca) የተሰኘው ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። መረጃው እንዳመላከተው በዚህ ዘመን ብዙ ሰብዓዊ ድርጅቶች ተቋቁመው ስለነበር በጎ ፈቃደኞችም በተደራጀ መንገድ ማገልገል ጀመሩ። ለአብነትም እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር በ1863 ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ሲመሠረት በጎ ፈቃደኞችን በሰፊው ያሳተፈ ከመጀመሪያዎቹ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አንዱ ነበር።

በኢትዮጵያም በጎ ፈቃደኝነት ከጥንት ጀምሮ በደቦ፣ ወንፈል፣ ዕቁብ፣ እድር እና በሌሎች ባሕላዊ የመረዳዳት ሥርዓቶች ይታወቃል። ዛሬም በመንግሥት፣ በሲቪክ ማሕበራት፣ በትምህርት  እና በሃይማኖታዊ ተቋማት አማካኝነት በተደራጀ መልኩ ይካሄዳል። ከጊዜ ወደ ጊዜም የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በየትኛውም ቦታ ገደብ ሳይደረግበት በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ትዕግስት ደርሶ ከበጎ ፈቃደኞች መካከል አንዷናት፤ ትዕግስት የበጎ አድራጎት  ተግባር የጀመረችው በበዓላት ጊዜ ለነዳያን የጾም መፍቻ የሚሆን ገንዘብ ከሕብረተሰቡ በማሰባሰብ ነበር። በጎ ሥራዋን በማጠናከርም ደም ትለግሳለች፤ ደም መለገስ የጀመረችው ደግሞ እህቷ  ስትወልድ ደም ፈሷት ስለነበር የፈሰሰውን ደም ለመተካት የሁለት በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ደም ተለግሷት ሕይወቷን መታደግ በመቻሉ ነው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም “የሌሎች ሰዎች ደም የእህቴን ሕይወት ከታደገልኝ እኔስ ለምን ሕይወት አላተርፍም!” የሚል የተነሳሽነት ስሜት በውስጧ ተፈጠረባት።በዚህ መነሻ በዓመት  ሦስት ጊዜም ደም ትለግሳለች።  በተጨማሪም እንደእሷ የበጎ አድራጎት ሥራ ከሚሠሩ  ጓደኞቿ ጋር በመሆን አልባሳትን በማሰባሰብ የታረዙትን ታለብሳለች። የበጎ አድራጎት ሥራን መሥራት  በገንዘብ የማይገኝ የአዕምሮ ርካታ እና የውስጥ ሰላምን ስለሚሰጥ መቼም ቢሆን እንደማታቋርጠው እና ሌሎችም ቢሳተፉ አትራፊ እንደሚሆኑ ገልጻልናለች።

መተዳደሪያዋ የሴቶች የውበት ሳሎን እንደሆነ የነገረችን አልማዝ ተረፈ ከምታገኘው ላይ በመቆጠብ ወላጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ያልቻሉ አምስት ሕጻናትን ዓመታዊ ወጪ መሸፈን ከጀመረች አራት ዓመታት ተቆጥረዋል። አልማዝ እንደነገረችን በዕድሜ የገፉ ሁለት ጎረቤቶቿን   ዘወትር እሁድ ገላቸውን ታጥባለች። ይህ ተግባሯ የመንፈስ ርካታ  አስገኝቶላታል። “የበጎ አድራጎት ሥራ ምንም የማይከፈልበት ቅንነት ብቻ የሚያሻው ተግባር ነው” የምትለው አልማዝ ባለ ቅን ልቦች ሁሉ እንዲፈጽሙት ጥሪዋን አስተላልፋለች።

በባሕር ዳር ከተማ “በጎነት ለእህትማማችነት፣ ለሴቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት!” በሚል መሪ መልዕክት ከሰሞኑ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄ  ተጀምሯል። በዚህ ሀገራዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ፕሬዝዳንት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ዘሃራ ሁመድ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 10 ሚሊዮን ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 15 የተመረጡ የንቅናቄ ተግባራት እንደሚከናወኑ ነው የጠቀሱት። ለአብነትም የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ደም መለገስ፣ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ይጠቀሳሉ፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከቁሳቁስ አቅርቦት ባሻገር ኅብረ ብሔራዊ እና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንዳለው የተናገሩት ደግሞ በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መስፍን አበጀ (ዶ/ር)  ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት በዚህ ዓመት ከ800 ሺህ በላይ የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ አባላት በበጎ ፈቃድ ሥራዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምትም በበጋም የሚቀጥል ሀገራዊ ባሕል እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፤ ከ234 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ተመዝግበው በተለያዩ ዘርፎች እየተሳተፉ ይገኛሉም ነው ያሉት።

በጎ ፈቃደኝነት ምን ማለት ነው?

በጎ ፈቃደኝነት አንድ ሰው ያለ ምንም ክፍያ በራሱ ፈቃድ ለሌሎች ሰዎች ወይም ለማሕበረሰብ ጥቅም የሚያከናውነው አገልግሎት ነው። ይህ የመረዳዳት፣ የመተባበር እና የማሕበራዊ ኃላፊነት መገለጫ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ለልማት፣ ለሰላም እና ለማሕበራዊ አንድነት ጠቃሚ መሣሪያ እንደሆነ ይታወቃል።

የበጎ አድራጎት ሥራ ቋሚ የዕድሜ ገደብ የሌለው ሲሆን ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አዋቂዎች እና አረጋዊያን እንደ እድሜያቸውና ችሎታቸው መሳተፍ ይችላሉ። ነገር ግን አንዳንድ ድርጅቶች ለተወሰኑ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ዝቅተኛ የዕድሜ መስፈርት ወይም የወላጅ ፈቃድ (ሕጻናት ከሆኑ በጎ አድራጎት ሥራውን የሚያከናውኑት) ሊጠይቁ ይችላሉ።

በበጎ አድራጎት ሥራ መሳተፍ የእያንዳንዱ ሰው መብት ሲሆን በጾታ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ ወይም በማሕበራዊ ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ ልዩነት ሊደረግ እንደማይገባ የተባበሩት መንግሥታት የበጎፈቃደኛ ድረ ገጽ ላይ ያለው መረጃ ያትታል።

ዓለም አቀፉ የበጎ ፈቃደኝነት መርህ እንደሚያሳየው ሴቶች፣ ወንዶችና ሕፃናት ያለ አድልዎ በበጎ ፈቃድ ሥራ የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል። ብዙ ጊዜ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ለመሳተፍ  የትምህርት ደረጃ አያስፈልግም። ይሁን እንጂ እንደ ሕክምና፣ የሕግ ምክር፣ ቴክኒክ ወይም ሌሎች ሙያዊ አገልግሎቶች ያሉ ሥራዎች ተገቢ የሙያ ብቃት፣ ስልጠና ወይም ፈቃድ ሊጠይቁ ይችላሉ።

በበጎ አድራጎት ሥራ ውስጥ  ለመሳተፍ  ከሁሉ በላይ የሚፈለገው ፈቃደኝነት፣ የማሕበረሰብ አገልግሎት ፍላጎት፣ ኃላፊነት፣ ትብብር እና ሌሎችን የመርዳት የራስ ተነሳሽነት ናቸው።

 

መረጃ

 

በዓለም  ላይ የበጎ ፈቃድ ሥራን ያበረታቱ ዋና ዋና ታሪካዊ ክንውኖች እነዚህ ናቸው፦

እ.አ.አ 1863 – International Committee of the Red Cross ተመሠረተ። ይህ በዓለም የተደራጀ የሰብዓዊ እርዳታና የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ እጅግ ወሳኝ መነሻ ሆኗል።

እ.አ.አ 1920 – ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወጣቶች በተደራጀ መልኩ ለመልሶ ግንባታ የሠሩበት ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ የሥራ ካምፕ ተጀመረ።

እ.አ.አ 1970 – የተባበሩት መንግሥታት በጎ ፈቃደኞች (UNV) ተቋቋመ። ይህም የበጎ ፈቃድ ሥራን በዓለም አቀፍ ደረጃ በልማት፣ በሰላም ግንባታ እና በሰብዓዊ እርዳታ ዘርፎች እንዲስፋፋ አድርጓል።

እ.አ.አ 1985 – የተባበሩት መንግሥታት ታኅሣሥ 5ን ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃደኞች ቀን (International Volunteer Day) ብሎ አወጀ።

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የነሐሴ  4  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here