በረራ አራዛሚው አዲስ ርምጃ

0
50

ተመራማሪዎች በድሮን ላይ ጨረር ተቀባይ ክፍል በመግጠም በዓየር ላይ ባትሪውን ኤሌክትሪክ ኃይል በመሙላት የበረራ ጊዜውን ማራዘም እንደሚቻል  መገንዘባቸውን ዘናሽናል ኒውስ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

እስከ አሁን በገመድ አልባ ስልክ፣ ሰዓት… ኃይል  መሙላት ቢቻልም ድሮንን ለመሙላት መሬት ማረፍ ግድ ሆኖ ቆይቷል፡፡

 

አሁን ግን በቻይና የሲቪል አቪዬሽን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪው ጂያን ሁዋ ሀን ረዘም ላለ ጊዜ ለደን ቁጥጥር፣ ለአደጋ ክትትል እና ቁሳቁስ አቅርቦት… ለሚሰሩ ድሮኖች ችግር ለነበረው የኃይል አቅርቦት መፍትሄ ማግኘታቸውን ነው ያበሰሩት፡፡

በአዲሱ ግኝታቸው “ፔሮብስኪት” ንብብር፣ የካልሺየም ማእድንን በመገልገል የጨረር ኃይሉን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል መቀየር ይቻላል ነው ያሉት – ተመራማሪው፡፡ ኃይል መሙያው የሚገኝበት የድሮኑ ክፍል በጨረሩ ሙቀት እንዳይጐዳም ማቀዝቀዣ ንብብር መግጠም እንደሚቻል ነው ያሰመሩበት፡፡ በጨረር ከተቋተው የብርሃን ኃይል 38 ነጥብ 49 በመቶውን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል መቀየር መቻሉንም አረጋግጠዋል፤ የተቀየረው ኃይልም ድሮኑን የማንቀሳቀስ አቅም መፍጠሩን ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

 

ኃይል በመሙላቱ የሙከራ ሂደት በጨረር ኃይል መቀበያው በኩል ያለው የድሮኑ ክፍል ከ80 እስከ 90 ዲግሪ ሴልሺየስ መሞቁን ነው የተገነዘቡት፡፡ ይህንን ለመቆጣጠርም የሙቀት መከላከያ ጥቃቅን “ክሪስታሎች” አስገብተው በማቀዝቀዝ አፈፃፀሙን ማስተካከል ችለዋል− ተመራማሪው ጂያን ሁዋ ሀን እንዳብራሩት፡፡

በመጨረሻም ከቤተ ሙከራ ወጥቶ በአስተማማኝ መልኩ መስራት እንደሚችል ለማረጋገጥ ኃይል የመሙላቱ ተግባር ቀለል ባሉ ድሮኖች እንደሚሞከር ነው ያደማደሙት -ተመራማሪው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ  4  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here