የወሎው ንጉሥ ሚካኤል (በፈረስ ስማቸው አባ ሻንቆ) በኢትዮጵያ የታሪክ ማኅደር ውስጥ በሃይማኖታዊ ማንነታቸው፣ በታዋቂው የዘር ሐረጋቸው እና በታላቅ የጦር መሪነታቸው ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ታላቅ መሪ ናቸው። የሕይወት ታሪካቸው እና የታሪክ አሻራቸው ከእስልምናው ዓለም መነሻ እስከ ሰሎሞናዊው ሥርወ-መንግሥት መገናኛ ድረስ ሰፊ ታሪካዊ ይዘት አለው።
ንጉሥ ሚካኤል ጥር 27 ቀን 1842 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም በወሎ ባላባቶች ባህላዊ የታሪክ አተራረክ ውስጥ ንጉሥ ሚካኤል የነብዩ መሐመድ 38ኛ የዘር ሐረግ እንደሆኑ በስፋት ይነገራል። በወሎ እስላማዊ ሥርወ-መንግሥት ማለትም በመሐመዶ ሥርወ-መንግሥት ማኅደር መሠረት የንጉሡ የትውልድ ሐረግ በቀጥታ ከነብዩ መሐመድ ልጅ ከፋጢማ እና ከባለቤቷ ከዐሊ ኢብን አቢ ጧሊብ ይነሳል። ይህ የዘር መስመር በባህል ደረጃ ትልቅ ክብር እና ቅቡልነትን ያሰጣቸው ነበር። ዘመናዊ የታሪክ ምሁራን በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በኖሩት በነብዩ መሐመድ እና በ19ኛውክፍለ ዘመን በኖሩት በንጉሥ ሚካኤል መካከል ያለውን የአንድ ሺህ ሶስት መቶ ዓመታት ልዩነት በማስላት 38ኛ ትውልድ የሚለው ቁጥር ጥቂት የትውልድ ክፍተቶች ሊኖሩት እንደሚችል ቢናገሩም ይህ ትረካ በወቅቱ የወሎን መሪዎች ታላቅነት እና ክብር ለማሳየት ትልቅ የታሪክ ሰነድ ሆኖ ያገለግላል። እዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባው በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹን ሙስሊም ስደተኞች በመቀበል ከነብዩ መሐመድ ጋር በቀጥታ የተገናኙት የአክሱሙ ንጉሥ ነጃሺ ሲሆኑ ንጉሥ ሚካኤል ግን በዘር ሐረግ የሚገናኙት የወሎው መሪ መሆናቸውን ነው።
“አባ ሻንቆ የአድዋው እንቆቆ፣
ጠላትን የሚጥል ሰይፍ ጋሻ አጥልቆ፤
የተንታው ግስላ የአባላጌው ነብር፣
ከጠላት መሀል ዘሎ የሚከመር፣
ንጉስ ሚካኤል ባለ ሶስት ግንባር፣
የወንዶች ቁና የማይደፈር”
ተብሎ የተገጠመላቸው ደፋር እና የጦር አዝማች መሆናቸውን ራሳቸው ዐፄ ምኒልክ መስክረውላቸዋል፡፡
ንጉሥ ሚካኤል በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ በርካታ የማይጠፉ አሻራዎችን ጥለዋል። በ1888ቱ ታሪካዊው የአድዋ ጦርነት ላይ ንጉሥ ሚካኤል 8000 እስከ 10000 የሚደርሱ ዝነኛ የወሎ እና የዓባይ ቦረና ፈረሰኞችን (የዓባይ ቦረና የሚባለው ሥፍራው ከዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ በመሆኑ ነው) እየመሩ ዘምተዋል። የወሎዉ ንጉሥ ራስ ሚካኤል በሶስቱም አዉደ ዉጊያዎች በመሳተፍ ታሪክ ሊዘነጋዉ የማይገባ ድል አድርገዋል፡፡ ራስ ሚካኤል አሊ ጠንካራ እና በቁጥር ብዙውን የጦር ሰራዊት በመገንባታቸው ይታወቃሉ፡፡
በጦርነቱ ወቅት የፈረሰኞቻቸው ማዕበል የጣልያንን ምሽግ በመስበር እና የጠላት ጦር እንዳይገናኝ በመበተን ረገድ ለድሉ መገኘት ፍጹም ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
የደሴ ከተማ የተመሰረተችው በ1874 ዓ.ም በንጉሥ ሚካኤል አማካኝነት ነው። ራስ መሐመድ ዓሊ ለአስተዳደራቸው የሚሆን ምቹ ማዕከል በመፈለግ ላይ ሳሉ በምሽት ሰማይ ላይ ታላቅ ተወርዋሪ ኮከብ ወደ መሬት ሲወርድ ተመለከቱ። ይህንን ክስተት እንደ መልካም የእግዚአብሔር ምልክት በመቁጠር ይህ ቦታ የኔ ደሴ ማለትም ደስታዬ ናት በማለት ቦታውን ደሴ ብለው ሰየሙት። ከተማዋ ከመመሥረቷ በፊት መቀመጫቸውን በመቅደላ አምባ ላይ አድርገው የነበረ ቢሆንም ወሎን በአንድ ማዕከል ለመግዛት እና የንግድ መስመሮችን ለመቆጣጠር ደሴ ይበልጥ ስትራቴጂካዊ ቦታ በመሆኗ የሥልጣን ማዕከላቸውን ወደዚህ አዛወሩ። ንጉሥ ሚካኤል በደሴ ከተማ ውስጥ ባለ ሁለት ፎቅ ዘመናዊ ቤተ መንግሥት ያስገነቡ ሲሆን ይህ ግቢ የወሎ፣ የትግራይ እና የአፋር አካባቢዎችን የሚያስተዳድርበት የታላቁ የሰሜን ኢትዮጵያ መንግሥት ዋነኛ የፖለቲካ ማዕከል ሆነ። ደሴ ከተመሠረተች በኋላ ከቀይ ባሕር ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ የሚሄዱ የንግድ መስመሮች መሸጋገሪያ በመሆን በፍጥነት አድጋለች፡፡ ንጉሡ የተለያዩ እደ-ጥበብ ባለሙያዎችን፣ ነጋዴዎችን እና የሃይማኖት መሪዎችን በከተማዋ እንዲሰፍሩ በማድረጋቸው ከተማዋ የባህልና የኢኮኖሚ ማዕከል ለመሆን በቃች።
ንጉሥ ሚካኤል በ1906 ዓ.ም በልጃቸው በልጅ ኢያሱ አማካኝነት የወሎ እና የትግራይ ንጉሥ ወይም ንጉሠ ጽዮን ተብለው በይፋ ተሹመዋል።
በፖለቲካ ብልሃታቸውም የዐፄ ምኒልክን ልጅ ወይዘሮ ሸዋረገድን በማግባት ወደ ዐፄው ቤተመንግሥት የተዘረጋ ሲሆን ከዚህ ጋብቻ የተወለዱት ልጃቸው ልጅ ኢያሱ በዐፄ ምኒልክ ፈቃድ የኢትዮጵያ አልጋ ወራሽ እና መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ይህም የእስልምናውን የመሐመዶ ሥርወ-መንግሥት ከክርስቲያኑ ሰሎሞናዊ ሥርወ-መንግሥት ጋር በቀጥታ አስተሳስሮታል። በ1870 ታዋቂው የቦሩ ሜዳ ጉባኤ ላይ ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላም በወሎ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል። ይህ እርምጃቸው በእስልምና እና በክርስትና ባህል መካከል የነበረውን ማኅበራዊ ትስስር በማጠናከር ለዛሬው የወሎ ልዩ የባህል መቻቻል እና አብሮ መኖር ትልቅ መሠረት ጥሏል።
ልጅ ኢያሱ የዳግማዊ ምኒልክን አልጋ ወራሽ ሆነው ስልጣን በያዙበት ወቅት የሸዋ መኳንንት እና ቤተ ክርስቲያኑ “እስልምናን ሊያስፋፋ ነው” በሚል ሥጋት መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ከሥልጣን አወረዷቸው። በምትካቸውም የዐፄ ምኒልክን ልጅ ዘውዲቱን ንግሥት፣ ራስ ተፈሪ መኮንንን (በኋላ ዐፄ ኃይለ ሥላሴን) ደግሞ አልጋ ወራሽ አድርገው ሾሙ። ይህንን የልጃቸውን ከሥልጣን መውረድ ያልተቀበሉት የወሎው ንጉሥ ሚካኤል የልጃቸውን አልጋ ለማስመለስና የሸዋን መኳንንት ለመቅጣት ወደ አዲስ አበባ ዘመቱ። ንጉሥ ሚካኤል ከሰሜን ኢትዮጵያ ያስከተሉት ጦር እጅግ ግዙፍ፣ የሰለጠነ እና የታወቁትን የወሎ ፈረሰኞች ያካተተ ነበር። የሸዋ መኳንንት በበኩላቸው በጦር ሚኒስትሩ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲናግዴ (አባ መላ) መሪነት ሰፊ ጦር አደራጁ።
ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት የንጉሥ ሚካኤል ጦር እጅግ በጀግንነት የሸዋን መከላከያ ሰብሮ በመግባት ወደ አዲስ አበባ ለመቃረብ ችሎ ነበር። ሆኖም ግን የሸዋ ጦር የተሻለ ዘመናዊ መሣሪያ (አውቶማቲክ ጠመንጃ እና መድፍ) የታጠቀ በመሆኑ እና የንጉሥ ሚካኤልን ጦር በስትራቴጂ ከበው ማጥቃት በመቻላቸው የጦርነቱ የበላይነት ወደ ሸዋ ጦር አዘነበለ። በዚህ እጅግ አውዳሚ ጦርነት ላይ በሁለቱም ወገን በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አልቀዋል። ንጉሥ ሚካኤል እስከመጨረሻው ሰዓት በጽናት ቢዋጉም የጦር ሰራዊታቸው ተሸንፎ እሳቸውም ተማረኩ። ልጅ ኢያሱም የአባታቸውን መማረክ በሰሙ ጊዜ ወደ አፋር በረሃ ለመሸሽ ተገደዱ።
ምንጭ፡- «የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ኃይለ ሥላሴ» ፡- ከተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ «ዳግማዊ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት»፡- ከአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ የዒትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
ሳምንቱ በታሪክ
ዐፄ ይኩኑ አምላክ ነገሡ
ዐፄ ይኩኑ አምላክ ነሐሴ 5 ቀን 1262 ዓ.ም ነገሱ፡፡ የዐፄ ይኩኖ አምላክ ንግሥና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ “የሰሎሞናዊ ሥርወ-መንግሥት መታደስ” በመባል የሚታወቅ ታላቅ የሥልጣን ሽግግር ነው። ንጉሡ የመጨረሻውን የዛጉዌ መስመር መሪ በጦርነት በማሸነፍ ማዕከላዊውን ሥልጣን ወደ ቀደመው የአክሱም ነገሥታት ወገን መመለስ ችለዋል። ለዚህ የሥልጣን ስኬታቸው በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም አበምኔት በአባ ኢየሱስ ሞዓ እና በአቡነ ተክለሃይማኖት የሚመራው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አካል ከፍተኛ የፖለቲካ እና የሕዝብ ቅቡልነት ድጋፍ አድርጎላቸዋል።
ይህ ንግሥና የሥልጣን ማዕከሉን ከላስታ ተራሮች ወደ መካከለኛው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች (ወሎ እና ሰሜን ሸዋ) ያዛወረ ሲሆን የአማርኛ ቋንቋ የቤተ መንግሥት ይፋዊ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል መሠረት ጥሏል። ዐፄ ይኩኖ አምላክ ለ15 ዓመታት በነገሡበት ዘመን የገነተ ማርያምን ውቅር ቤተ ክርስቲያን አሳንጸዋል፤ በእሳቸው የተጀመረው ሥርወ-መንግሥትም እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ለ744 ዓመታት ሀገሪቱን መርቷል።
ምንጭ፡- «የኢትዮጵያ ታሪክ፦ ከአክሱም መነሳት እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ» — ከተክለ ጻድቅ መኩሪያ
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


