ክረምት ለተማሪዎችና መምህራን ከመደበኛው የቀለም ትምህርት እረፍት የሚወሰድበት ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የተሻለ ዝግጅት የሚደረግበት፣ ያልተረዱትን የሚደገፉበት እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማሕበረሰባዊ ኃላፊነት የሚወጡበት ወርቃማ ጊዜ ነው።
የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት አሰራር እንደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ፊንላንድ ባሉ የተሸለ የትምህርት ሥርዓት ባላቸው ሀገራት በሰፊው የተለመደ ስትራቴጂ ነው። በእነዚህ ሀገራት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በክረምት ወራት ለረጅም ጊዜ ከትምህርት ገበታ የሚርቁ ተማሪዎች “የክረምት ዕውቀት መሸርሸር” ሊያጋጥማቸው ይችላል፤ ቀደም ሲል የተማሯቸውን ሀሳቦች የመርሳት ዕድላቸውም ከፍተኛ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ከሚማሩ ተማሪዎች ውስጥ ተማሪ አበባ ምህረትን አነጋግረናል፡፡
ተማሪ አበባ ምህረት የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቱ ለእኔ ትልቅ ስንቅ ሆኖኛል። ባለፈው ዓመት አስቸጋሪ የነበሩብኝን የትምህርት ዓይነቶች አሁን ላይ በደንብ ለመረዳት ችያለሁ፤ በቀጣይ ዓመት ክፍሌ ውስጥ ከበፊቱ የተሻለ ውጤት እንደማመጣ ሙሉ እምነት አለኝ።ከትምህርቱ ጎን ለጎን የሚሰጠን የስነ-ምግባር ትምህርት ለአስተሳሰባችን ትልቅ ጥንካሬ ሰጥቶናልም ብላናለች።
ዛሬ ዛሬ በብዙዎች ዘንድ “የአሁኑ ትውልድ ብልሽት ገጠመው፣ ሥነ ምግባር ራቀው” የሚሉ ምሬቶችን መስማት የተለመደ ሆኗል። ነገር ግን ችግሩን አጉልቶ ከመናገር ባለፈ፣ የመፍትሔው አካል ለመሆን በቁርጠኝነት የሚሠሩት ጥቂቶች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገራችንም በርካቶች የመፍትሔው አካል በመሆን የሚችሉትን አበርክቶ እየሰጡ ይገኛሉ፤ ይህ አበርክቶ ከሚገለጥባቸው ወቅቶች መካል ደግሞ የክረምት ወራት ተጠቃሽ ናቸው፤ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ መምህር ኃይለማርያም ዘውዱ አንዱ ናቸው። መምህር ኃይለማርያም ዘውዱ ተማሪዎችን በስነ ምግባር ለማነጽ ያነሳሳቸው የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ ምን ይሆን? ብለን ሀሳባቸውን እንዲያጋሩን በስልክ አነጋግረናቸዋል፡፡
መምህር ኃይለማርያም እንደነገሩን ይህንን በጎ ዓላማ ለመጀመር ያነሳሳቸው በግል ሕይወታቸው የታዘቡት እውነታ ነው። በተማሪነት ዘመናቸውም ሆነ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲ አስተማሪነታቸው፣ የተማሪዎችን ጠባይ እና የሥነ ምግባር በቅርበት እና በትኩረት ይከታተሉ ነበር።
“ካደጉ በኋላ ትውልዱ ሞተ፣ ተበላሸ ብሎ እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥና ከመውቀስ ይልቅ፣ እኔ ለትውልዱ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለምን አላበረክትም?’ የሚል ጥልቅ በውስጤ ያጭርብኛል” የሚሉት መምህሩ ይህ ቁርጠኝነትም ተመሳሳይ ዓላማ እና ሕልም ካላቸው ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በክረምት የበጎ አድራጎት ሥራ የስነ ምግባር ትምህርት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ማስተማር እንዲጀምሩ አስችሏቸዋል፡፡
በተናጠል ከማዘን ወደ ተግባር የተቀየረው ይህ ጥረት፣ ባለፈው ዓመት ፍሬ ማፈራት ጀመረ። መምህር ኀይለማርያምና ባልደረቦቻቸው ፍቃደኛ ከሆነ የግል ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር፣ በክረምት ወራት በዘጠኝ የመማሪያ ክፍሎች ከ700 መቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን በማሰባሰብ የሥነ ምግባር ማነጻጸሪያ ትምህርት መስጠት ጀምረዋል።
መምህር ኃይለማርያም እንደሚያስገነዝቡት፣ የትውልድ ግንባታ መነሻው ልጅነት ነው። ሕፃናት ገና በለጋ ዕድሜያቸው የጽኑ ሥነ ምግባር እና የስርዓት መሠረት ካልተጣለላቸው፣ ወደፊት አድገው ጥፋት ውስጥ ከገቡ በኋላ መስመር እንዲይዙ ማድረግ እጅግ አታጋይ፤ አንዳንዴም የማይቻል ይሆናል።
ስለዚህም፤ የአሁኑ ጊዜ ትውልድ… እያሉ ጣት ከመቀሰር፣ ትንሽ ደክሞና ለፍቶ ሕፃናትን ከስራቸው ማነፅ ይገባል ይላሉ።ከልጅነታቸው ጀምሮ የሥነ ምግባር ትምህርት ያገኙ ሕፃናት፣ ነገ ለአገርና ለወገናቸው የሚያስቡ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ይሆናሉ።በቀጣይም የስነ ምግባር ትምህርቱ ክረምትን ጠብቆ እና በውስን ቦታ ከሚሰጥ የጊዜ ሰሌዳ ተይዞለት ተከታታይ በሆነ መልኩ ቢሰጥ ብቁ ዜጋን ለማፍራት አስተዋጽኦው የላቀ ነው የሚል ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
በተመሳሳይ ያነጋገርናቸው በጣና ሀይቅ ትምህርት ቤት የቋንቋ መምህርት የሆኑት ወ/ሮ ሙሉመቤት መኮንን ናቸው፡፡መምህርቷ በተለያዩ ምክንያቶች የበጋ ትምህርታቸውን ሙሉ በሙሉ ያልተከታተሉ ተማሪዎችን ለመደገፍና በመስከረም ወር በተሻለ ተነሳሽነት ወደ ትምህርት እንዲመለሱ በማሰብ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በበጎ ፍላጎት እየሰጡ መሆኑን ነው የተናገሩ።ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ይህንን የበጎ ፈቃድ የማስተማር ሥራ ለሁለተኛ ጊዜ እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ተማሪዎች በሚሰጣቸው ትምህርት ተጠቃሚ በመሆናቸው እንዲሁም እሳቸውም በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ስለሚሰጥ መረጃው ትምህርት ቤቶች ከመዘጋታቸው በፊት ለመምህራንና ለተማሪዎች አስቀድሞ ቢደርስ፣ የተሻለ ዝግጅት በማድረግ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት በደሴ ከተማ፣ በይልማና ዴንሳ ወረዳ እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት
የደሴ ከተማ ስርዓተ ትምህርት የመማር ማስተማር ባለሙያ እና የክረምት ስራ በጎ ፈቃድ ፎካል ፐርሰን የሆኑት አቶ ዑስማን ጅብሪል እንዳሉት፤ በከተማው ባሉ የመንግስት እና የግል ትምህርት ቤቶች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጥ የአፈጻጸም ግምገማ በማድረግ፣ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እና አስፈላጊውን ኦሬንቴሽን በመስጠት ወደ ስራ ተገብቷል።
በዕቅዱ መሠረት በከተማዋ ከሚገኙ 54 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 42ቱ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጡ እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 13ቱ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጡ ተደርጓል። እስካሁን ባለው ሂደት 30 የሚሆኑት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 3 ሀይስኩሎች ብቻ ትምህርት መስጠት እንደጀመሩ ነው አቶ ሁሴን የተናገሩት።
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 2ሺህ 950 ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ 2ሺህ 630 የሚደርሱ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በኩል በሚፈለገው ልክ እስካሁን ወደ ትግበራ አለመገባቱን የጠቆሙት አቶ ዑስማን፣ ሂደቱ ተገምግሞ እንደ አዲስ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ መሰጠቱን አብራርተዋል።
በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ 32 ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የወላጆች በዓል በሚከበርበት ወቅት በገቡት ቃል መሰረት በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ የሚገኙ መምህራን ተማሪዎችን እያስተማሩ ይገኛሉ ነው ያሉት። ትምህርቱም በተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች ላይ በማተኮር ተማሪዎች ለቀጣይ ዓመት ስንቅ እንዲይዙ እና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያግዝ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል፣ የይልማና ዴንሳ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የሸዋስ አናጋው በዞን ደረጃ ወደ 1ሺህ200 አካባቢ ተማሪዎች ተመዝግበው የማጠናከሪያ ትምህርት ማግኘት አለባቸው የሚል እቅድ መሰጠቱን ገልጸው 1ሺህ 019 ተማሪዎች መመዝገብ መቻሉን ነው የተናገሩ።
በአሁኑ ወቅት በሁለተኛ ደረጃ ሁለት ትምህርት ቤቶች 1መቶ 89 ተማሪዎች፣ በአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከተመዘገቡት 8መቶ 30 ተማሪዎች ውስጥ 3መቶ የሚሆኑት ተማሪዎች በተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ ነው ያሉ። በዚህ በጎ ፈቃድ ስራ ላይ 20 የበጎ ፈቃደኛ ወጣት መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል ብለዋል።ከዚህ በተጨማሪም ነባር መምህራን በበጎ ማጠናከሪያ ትምህርት ማስተማር ስራው ላይ ተሳታፊ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትበይን ባንትይሁንም የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቱን ለማስጀመር ቀደም ባሉት ሳምንታት ሰፊ የንቅናቄ መድረክ መፈጠሩን እና በየትምህርት ቤቱ እና በየጎዳናው ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ ተማሪዎችና ወላጆች ስለ ፕሮግራሙ እንዲያውቁ መደረጉን ተናግረዋል፡፡በዚህም ቀላል የማይባል ቁጥር የተማሪዎች ምዝገባ ተካሂዷል። በተጨማሪም በበጎ ፈቃደኝነት ማስተማር የሚፈልጉ ወጣቶች በየክፍለ ከተማው እንዲውጣጡ የተደረገ ሲሆን፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ማስተማር የሚችሉ መምህራንም ውይይት ተደርጎላቸው ወደ ስራ ተገብቷል።
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አራት ሺህ 983 ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ተማሪዎችን መቀበል ተችሏል፤ በሁለተኛ ደረጃም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ተመዝግበዋል ነው ያሉት። እንደ ወ/ሮ ትበይን ገለጻ በአጠቃላይ በከተማዋ ስድስት ሺህ 183 ተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
በትምህርቱ ሂደት ከተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች በተጨማሪ፣ የስነ-ምግባር ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ይህ ትምህርት የተማሪዎችን ባህሪ እና የስነ-ልቦና ሁኔታ በመቀየር ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱ ወላጆችን በእጅጉ አስደስቷልም ብለዋል።
ግእዝ በአማርኛ
አስራት — ከአስር አንድ ግብር
ዕለት — ቀን
ገራህት — እርሻ፣ አዝመራ
ገነት — አታክልት፣ ገነት
ሆሣዕና — ድኅነት፣ መድኃኒት
ትውፊት — መውረስ፣ መቀበል
(ሰናይት በየነ)
በኲር የነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


