ወጣት የሱፍ እንድሪስ በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ ነዋሪ ነው። የሱፍ በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በማህበር ተደራጅቶ ወደ ግብርናው ዘርፍ ገባ፡፡ ከአባላቱ ጋር በአካባቢው ተፈላጊ የሆኑ ችግኞችን አፍልተው በመሸጥ ገቢ ማግኘት ጀመሩ፡፡
ከጓደኞቹ ጋር የተሰማራበት የግበርና ዘርፍ አዋጭ መሆኑን የተገነዘበው የሱፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የራሱን የግል የንግድ ፈቃድ በማውጣት በገበያ ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን የቆላማ ፍራፍሬ ችግኞችን በማፍላት የልማት ሥራውን ጀምሯል።
እንደ ወጣቱ ገለጻ አራት አይነት የተሻሻሉ የማንጎ (አፕል፣ ቶሚ፣ ኬንት እና ኪት የተባሉትን)፣ የብርቱካን፣ የሎሚ፣ የፓፓያ፣ የሙዝ እና የዘይቱኒ ችግኞችን እያለማ ለገበያ ያቀርባል።
“በዚህ ዓመት ብቻ (በ2018) ከ25 ሺህ እስከ 30 ሺህ የሚደርሱ የማንጎ ችግኞችን አፍልቼ ለገበያ አቅርቤያለሁ” የሚለው ወጣት የሱፍ ችግኞችን ከመሸጥ ባለፈ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ማንጎ በማልማት ፍሬውን እየሸጠ እንደሚገኝ ተናግሯል። የግብርና ሥራው የወጣት የሱፍን ሕይወት ከመሰረቱ ቀይሮታል። “ከዚህ በፊት ከነበረኝ የኑሮ ደረጃ አሁን ያለሁበት እጅግ የተሻለ ነው” የሚለው ወጣቱ ከሚያገኘው ገቢ የራሱን መኖሪያ ቤት መሥራት እና ቤተሰቡንም በጥሩ ሁኔታ እያስተዳደረ መሆኑን ተናግሯል።
የወጣቱ ሥራ የግል ሕይወቱን ከመቀየር ባለፈ ለአካባቢው የስነ-ምህዳር ለውጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተለይም ሀገራዊውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተከትሎ የአካባቢውን ለምነት ከመጠበቅ ባለፈ በሚበሉ የፍራፍሬ ዛፎች ጭምር አረንጓዴ እንዲለብስ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል። አሁን ላይ የሱፍ የሚያለማበት አካባቢ ማራኪ እና አረንጓዴ መሆኑን ወጣቱ በደስታ ይገልጻል። ወደፊት ሥራውን ይበልጥ ለማስፋፋት ትልቅ ራዕይ ሰንቋል። በቀጣይ ዓመትም እስከ 100 ሺህ ችግኞችን በማፍላት ለሽያጭ ለማቅረብ እቅድ አለው።
“ማንም ሰው ቢሠራ ሕይወቱን መቀየር ይችላል። ወጣቶች የመንግሥትን ሥራ ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ በግብርናው ዘርፍ ቢሰማሩ አዋጭ ነው። እኛም የሥራችንን ፍሬ እያየነው ስለሆነ ሌላውም ወጣት ጊዜውን ሳያጠፋ ወደ ሥራ ቢገባ የተሻለ ኑሮ መኖር ይችላል” በማለት የሱፍ ሥራ ለሌላቸው እና የመንግሥትን ሥራ ለሚጠብቁ ወጣቶች ምክር ሰጥቷል።
በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ (የሆልቲካልቸር) ቡድን መሪ አቶ አሳልፍ አሕመድ እንዳብራሩት በዞኑ ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ የለማ ሲሆን ከዚህም ከሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል።
ቡድን መሪው እንደሚሉት የዞኑ የአየር ንብረት ለተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬ ተስማሚ ነው። በደጋው አካባቢ ድንች፣ አፕል፣ ካሮት እና ነጭ ሽንኩርት በስፋት ይመረታሉ። በቆላማው እና ወይና ደጋው ክፍል ደግሞ ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና አቮካዶ በክላስተር ጭምር እየለሙ ይገኛሉ። ቀደም ሲል ለፍጆታ ብቻ ይመረት የነበረው ምርት አሁን ወደ ሰፊ የገበያ ትስስር አድጓል። አርሶ አደሩ ምርቱን በአካባቢው ገበያ ብቻ ሳይወሰን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ጭምር በማቅረብ ተጠቃሚነቱን አሳድጓል። በዚህም አርሶ አደሮች ቤት ከመገንባት፣ መኪና ከመግዛት እና ልጆቻቸውን ከማስተማር አልፈው ከፍተኛ የካፒታል አቅም እየፈጠሩ ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ከፍራፍሬ ልማት ጋር በማስተሳሰር ትልቅ ራዕይ ሰንቋል። “የምንተክለው ችግኝ ወደ ሚበላ መቀየር አለበት” በሚል መሪ ሀሳብ በዚህ ዓመት ብቻ ከሦስት ሺህ 745 ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬ ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን ከሁለት ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት ተሸፍኗል። ክልል አቀፉ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዚሁ ዞን ቃሉ ወረዳ የተካሄደ ሲሆን በአንድ ክላስተር ብቻ 213 ሄክታር መሬት ላይ 156 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የማንጎ ችግኝ ተተክሏል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ ለዜጎች የኢኮኖሚ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የማሕበረሰብ ጥምር ደን እርሻ ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ ፈጠነ መኮንን ተናግረዋል።
ባለሙያው ከበኵር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ዋና ዓላማ የአየር ንብረት ሚዛንን መጠበቅ ቢሆንም አሁን ላይ አርሶ አደሩን እና የከተማውን ነዋሪ ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። አርሶ አደሮች ባለፉት ሰባት ዓመታት ቡና እና አቮካዶን ጨምሮ ሌሎች የፍራፍሬ አይነቶች በማምረታቸው ከፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ መቻላቸዉን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩን በማደራጀት በኩታ ገጠም የፍራፍሬ ልማት እንዲሳተፍ እና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ማድረግ መቻሉንም አቶ ፈጠነ አስረድተዋል።
ከዚህም ባሻገር የዕጣን እና ሙጫ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ወደ ጎረቤት ሱዳን እና አውሮፓ ሀገራት ጭምር በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መሆን ችለዋል። የደን ልማት ማለት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ጭምር መሆኑን የገለፁት ባለሙያው እንደ አቮካዶ እና ፓፓያ ያሉ በአጭር ጊዜ ደርሰው ምርት የሚሰጡ የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት በማልማት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
“ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ ሊሆን አይችልም” የሚሉት ባለሙያው “ችግኝ መትከል የሁለት እና የሦስት ደቂቃ ሥራ ነው፤ እንክብካቤ ግን የዓመት ሙሉ ሥራ ነው” የሚሉት አቶ ፈጠነ ከተከላ በኋላ አረም ማረም፣ መኮትኮት፣ አስፈላጊ ግብዓት መጨመር፣ ዝናብ ሲጠፋ ውኃ ማጠጣት እና ከእንስሳት ንክኪ ለመጠበቅ አጥር ማጠር የግድ እንደሆነ ያሳስባሉ።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ እየጠፉ ያሉ ሀገር በቀል ዛፎችን እንደ ዝግባ፣ ጥድ፣ ኮሶ፣ ዋንዛ የመሳሰሉትን ለማጽደቅ አፅንኦት ሰጥተዋል። እነዚህ ዛፎች ቶሎ ላያድጉ እና ለውጣቸው እስከ ሦስት ዓመት ላይታይ ቢችልም ለዘላቂ ስነ-ምህዳር ያላቸው ጥቅም የጎላ በመሆኑ ህብረተሰቡ በትዕግስት ሊንከባከባቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በዘንድሮው ዓመት በአማራ ክልል አንድ ነጥብ 76 ቢሊዮን ችግኞችን በ261 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ባለው አፈፃፀም ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በ235 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መትከል ተችሏል። በተለይም ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከዘጠኝ ሺህ 392 በላይ የጥቃቅን እና አነስተኛ የደን ተቋማትን በማደራጀት ወደ ሥራ መግባታቸው የዘንድሮው ተስፋ ሰጪ ክንውን ነው።
በቀጣይ መርሐ-ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን ከዘመቻ ተከላ ይልቅ ባለቤትነትን ማዕከል ያደረገ አሠራር ላይ ትኩረት ይደረጋል። እያንዳንዱ ተቋም፣ ግለሰብ እና አርሶ አደር የተከለውን ችግኝ በአግባቡ የመንከባከብ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል። “እኛ የምንተነፍሰው ንፁህ አየር የሚመነጨው ከደን ነው፤ ስለዚህም ለተፈጥሮ የምንሰጠው እንክብካቤ ለራሳችን ሕልውና የምንሰጠው ዋስትና ነው” በማለት አቶ ፈጠነ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም የ800 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በጨለቃ ኩታገጠም በመገኘት አሻራቸውን አስቀምጠዋል። የችግኘ ተከላ መርሐ ግብሩን ሕብረተሰቡ በባለቤትነት እያከናወነው የሚገኝ መሆኑን የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በከፍተኛ ደረጃ የተራቆተውን መሬት እና ለድርቅ የተጋለጡ አካባቢዎች እንዲለመልሙ ሆነዋል ነው ያሉት። ሰብል ማብቀል ማይችል መሬት እንዲያበቅል ሆኗል። የደን ሽፋኑም ጨምሯል።
በየዓመቱ በሚከናወነዉ የችግኝ ተከላ ከተለመዱት የደን ዛፎች በተጨማሪ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ቡና፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ… ያሉ ለምግብነት እና ለገበያ የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት መተከላቸውን አስገንዝበዋል። እነዚህን ችግኞች መንከባከብ እና ለፍሬ ማብቃት ይገባል ብለዋል። የመርሐ ግብሩ ስኬታማነት የቤተሰብን፣ የክልሉን እና የሀገርን ገቢ በማሳደግ ጉልህ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር “ተስፋን እንትከል!” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ የሚገኘዉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከስምንት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ነው። ችግኞችን መትከል፣ ማጽደቅ እና ለኢኮኖሚ ጥቅም ማዋል የሀገራችን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትልቁ ግብ ነው።
መረጃ
የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ሲሆን ለምግብነት፣ ለጤና እና ለገቢ ምንጭነት የሚያገለግሉ እንደ ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ እና የመሳሰሉትን ተክሎች ማምረትን ያጠቃልላል።
ለልማቱ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች
ተስማሚ አየር ንብረት እና መሬት
የተለያዩ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች የተለያየ አየር ንብረት (ቆላ፣ ወይናደጋ፣ ደጋ) እና የአፈር አይነት ይፈልጋሉ።
በቂ የውኃ አቅርቦት፦ አብዛኛዎቹ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች ቶሎ ቶሎ ውኃ ስለሚፈልጉ የዝናብ ውኃን ብቻ ሳይሆን የመስኖ (በተለይ ዘመናዊ የጠብታ መስኖ) አቅርቦትን ይፈልጋሉ።
ምርጥ ዘር፦
በሽታን መቋቋም የሚችሉ እና የተሻለ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን መጠቀም ወሳኝ ነው።
እንክብካቤ፦ ማረም፣ መኮትኮት፣ ማዳበሪያ (በተለይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ/ኮምፖስት) መጨመር እና ፀረ-ተባይ መድሀኒቶችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


