ጦርነቱ እና የተባባሰው የረሃብ ስጋት

0
178

እ.አ.አ በየካቲት ወር 2022 የጀመረው የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ እጅግ ደም አፋሳሽ እልቂት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በይገባኛል ጥያቄዎቻቸው ላይ ያላቸው ፅኑ አቋም እና የጥቅም ግጭት ሰላማዊ መፍትሄን እጅግ አዳጋች በማድረጉ ጦርነቱ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ለዩክሬን ከፍተኛ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለጦርነቱ መባባስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ነው ሩሲያ በተደጋጋሚ የምታነሳው፡፡

በ8ኛው ዓለም አቀፍ በኢኮኖሚ አስተዳደር እና በአረንጓዴ ልማት ጉባዔ ላይ ስለጦርነቱ በቀረበው ጥናት እ.አ.አ በ2022 ሩሲያ ባደረገችው ወረራ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለዘመናት ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ ፈጥሯል፡፡

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና እንግሊዝን ጨምሮ በሩሲያ ላይ ከ40 በላይ ከባድ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ማዕቀቦችን ጥለዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ በውጭ ሀገር የተያዘውን ሀብት ማገድ፣ ሩሲያ የውጭ ሀገር የገንዘብ ክምችቶቿን የማግኘት አቅሟን መገደብ፣ ዋና ዋና የሩሲያ ባንኮችን ከስዊፍት ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ማስወገድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሥራት አቅማቸውን ማዳከም፣ እንደ ኮምፒውተሮች፣  እና ቴሌኮም ያሉ ቁልፍ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሩሲያ መላክን መከልከል፤ በነዳጅ ማጣሪያ መሣሪያዎች እና በሌሎች የኢነርጂ ዘርፎች ላይ የውጭ ግብይት (ኤክስፖርት) ቁጥጥር ማድረግ እንዲሁም የፖለቲካ መሪዎችን ጨምሮ ተጽዕኖ ፈጣሪ  ሰዎች  ላይ የጉዞ እገዳ መጣል ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለጦርነቱ ምላሽ ለመስጠት ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ኩባንያዎች በሩሲያ ውስጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በፈቃደኝነት አቁመዋል ወይም ገድበዋል፡፡ ይህ የኩባንያዎች መውጣት የሩሲያን ኢኮኖሚ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ገበያዎች እና ለአቅርቦት ሰንሰለቶች ያላትን ተደራሽነት በእጅጉ አዛብቶታል፡፡

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለው ግጭት ከጦርነቱ ተዋናይ ሃገራት ባሻገር በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይም ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል ባለው ግጭት እና በተጣሉት ማዕቀቦች ምክንያት ዓለም አቀፍ ንግድ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ የበርካታ ኩባንያዎች የአቅርቦት ሰንሰለት እንዲቋረጥ በመገደዱ፣ የምርት መጠን እንዲቀንስ እና ወጪዎች እንዲጨምሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

በተመሳሳይ በተለይም የምግብ እና የኃይል ወጪዎች (የዋጋ ግሽበት) ጫናን በማባባስ፣ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚታይ መቀዛቀዝን አስከትሏል፡፡

በሩሲያ የነዳጅ ኤክስፖርት ላይ የተጣለው ማዕቀብ በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ በዚህም ምክንያት በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ወዲያውኑ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ የኃይል አቅርቦት ላይ በከፍተኛ መጠን ጥገኛ  በመሆናቸው  የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡

ሀገራቱ ታዲያ ከሌሎች አማራጭ አቅራቢዎች ጋር የንግድ ግንኙነት በመፍጠር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የነዳጅ ምንጮቻቸውን እና የኃይል ፍጆታ አወቃቀራቸውን በማብዛት በሩሲያ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ተገደዋል፡፡

የነዳጅ ምንጭን በአንጻራዊነት በፍጥነት መቀየር ቢቻልም፣ የጋዝ ንግድ ግን ከመሠረተ ልማት ዝግጁነት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ በመሆኑ አቅርቦቱን ወዲያውኑ ለመተካት ወይም አቅጣጫውን ለመቀየር የሚያስችለውን አቅም ውስን አድርጎታል፡፡

አውሮፓ በሩሲያ የጋዝ አቅርቦት ላይ ጥገኛ በመሆኗ የአቅርቦት ሂደቱ መስተጓጎል የጋዝ አቅርቦቷን እስከ 40 በመቶ ቀንሶባታል፡፡ ይህ ደግሞ ከአውሮፓ በተጨማሪ በሩሲያ ገቢ ላይ ከፍተኛ ኪሳራን አስከትሏል፡፡

እንደ ቻይና ያሉ ሌሎች ሀገራትም በዚህ ማዕቀብ ምክንያት የኃይል ዋጋ ጭማሪ እና የአቅርቦት እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት እና እሱን ተከትለው የመጡት ማዕቀቦችና የንግድ እገዳዎች፣ ባለፉት ዓመታት እየቀነሰ የነበረውን ዓለም አቀፍ ረሃብ እንደገና እንዲጨምር አድርገውታል፡፡

መረጃው አክሎም ክስተቱ ድርጅቱ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚያደርገው ጥረት እንቅፋት እንደሚሆንብት ስጋቱን አስቀምጧል፡፡

ሩሲያ እና ዩክሬን ዋና ዋና የግብርና ምርት (በዋናነት ስንዴ) አምራች ሃገራት ናቸው፤  ለዓለም አቀፍ የስንዴ ንግድ ያላቸው የጋራ አስተዋጽኦ 30 በመቶ የሚጠጋ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በጦርነቱ ምክንያት በተጣሉ ማዕቀቦች እና በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ በተደረጉ ገደቦች ምክንያት፣ ስንዴን፣ ገብስን እና በቆሎን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ምርቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩ በመታገዳቸው በሩሲያ እና በቤላሩስ ውስጥ ተከማችተው ቀርተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ መሠረታዊ የምግብ ዋጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡

ለዚህ ቀጥተኛ ተጎጂ የሆኑት እንደ መካከለኛው እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ያሉ የምግብ እና የእህል አቅርቦታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ከውጭ በሚያስገቡት ሀገራት ላይ ነው፡፡ እነዚህን ሀገራት ጦርነቱ የምግብ ፍላጎታቸውን የማሟላት እድል ነፍጓቸዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ በመናሩ ምክንያት የእርዳታው መጠን እንዲቀንስ አድርጓል፤ ይህም ማሕበራዊ አለመረጋጋትን እንደሚያባብሰው ነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያወጣው መረጃ የሚያመላክተው፡፡

ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው ጦርነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንድምታ አለው፡፡

እንደዘገባው ከሆነ ጦርነቱ የንግድ ፍሰቶችን እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን አበላሽቷል፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የንግድ ዕድሎች እንዲቀንሱ አድርጓል፡፡ የገንዘብ እና የፋይናንስ ገበያዎች መዋዠቅ አጋጥሟቸዋል፣ ይህም የፋይናንስ ገቢ ተግዳሮቶችን እና የኢኮኖሚ ውድቀትን አስከትሏል፡፡

እነዚህ የኢኮኖሚ ተፅዕኖዎች በቀጥታ የተሳተፉትን እና በዙሪያቸው ያሉትን ሀገሮች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል፡፡

የጦርነቱን ፖለቲካዊ ተፅዕኖ በተመለከተ ያስነበበው እና ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚያስነብበው ፖለቲኮ የተሰኘው ድረ ገጽ እንዳስነበበው ጦርነቱ ለዓለም አቀፍ ፖለቲካ እና ሥርዓት ሰፊ ውጤት አለው፡፡ ግጭቱ በሩሲያ እና በምዕራባውያን ሀገሮች መካከል ያለውን የጂኦፖለቲካ ውጥረት አባብሷል፣ እንዲሁም ሩሲያ ከእያንዳንዱ ሀገር ጋር ያላትን ግንኙነት አበላሽቷል፡፡

ይህ ደግሞ የዓለምን የፖለቲካ ገጽታ በመቀየር አለመረጋጋትን ፈጥሯል፡፡ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋት እና በክልሉ የምዕራባውያን ተጽዕኖ መጠናከር ለሩሲያ ስጋትን ፈጥሯል፡፡

የሞስኮ ታይምስ ዘገባ እንደሚያመለክተው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እ.አ.አ በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ የሩሲያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) በአንድ ነጥብ ስምንት በመቶ መቀነሱን አምነዋል፤ ይህም ጦርነቱ ከተስፋፋ ወዲህ ስለ ኢኮኖሚ መቀነስ የተሰጠ የመጀመሪያው ይፋዊ መግለጫ ነው፡፡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሚኒስትርም የመንግሥት የገንዘብ ክምችት እያለቀ መሆኑን አምነዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አራት ዓመታትን የተሻገረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተደርገዋል፤ ዳሩ ግን የሚፈለገውን ውጤት አላስገኙም፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቱን በአሜሪካዋ አላስካ ግዛት ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው መምከራቸው ለዚህ ዋና አብነት ነው፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ  4  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here