ኢትዮጵያ በታሪኳ በረጅም ጉዞ ውስጥ ብዙ ድሎችንና ፈተናዎችን አሳልፋለች። የውጭ ወረራን መከላከል፣ የመንግሥታት ለውጥ፣ አብዮቶች፣ የፖለቲካ ሽግግሮችና የትጥቅ ግጭቶች የታሪኳ አካል ሆነው ቆይተዋል። ቢሆንም ከእነዚህ በላይ የቆየው ችግር ግን በዜጎች መካከል በአንዳንድ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠረው የአመለካከት ልዩነት ነው። እነዚህ ልዩነቶች በየዘመኑ በፖለቲካ ውድድር ውስጥ ሲገቡ አንዳንዴ ወደ ግጭት አንዳንዴ ደግሞ ወደ ጦርነት ተቀይረዋል። በነዚህ ምክንያቶችም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይዎታቸውን አጥተዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ተፈናቅለዋል፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተጎድቷል፣ በማሕበረሰቡ መካከል ያለው መተማመንም ተሸርሽሯል።
ይህ እውነታ አንድ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል፤ “ኢትዮጵያዊያን ችግሮቻቸውን በጦርነት ይፈታሉ? ወይስ በውይይት?” የሚል፡፡ የዛሬው የሀገራዊ ምክክር ሂደት የተጀመረውም ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ነው።
ሁሉም ሊያውቀው የሚገባው ጉዳይ ሀገራዊ ምክክር ማለት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ብቻ የሚወያዩበት መድረክ ሳይሆን የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የሲቪል ማሕበራት፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ትውልደ ኢትዮጵያዉያን(ዲያስፖራዎች) እና መንግሥታዊ ተቋማት በአንድ መድረክ ተሰብስበው የሀገሪቱን መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚመለሱበት ሂደት ነው።
የተሳካ ሀገራዊ ምክክር የሚገነባውም በአካታችነት ላይ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች፣ ሲቪል ማሕበራት እና ሌሎች ማሕበረሰቦች የመናገር እድል ሲያገኙ ብቻ የሂደቱ ውጤት ሰፊ ተቀባይነት ያገኛል። ምክክሩ የሚሳካውም ተሳታፊዎች በሂደቱ ላይ እምነት ሲኖራቸው ነው። የሂደቱ ግልጽነት፣ ገለልተኝነት እና ፍትሐዊነትም የሕዝብን እምነት ያጠናክራሉ።
እምነት ከሌለ ግን ጥሩ ውሳኔ ቢወጣም ተፈጻሚ ለመሆን ይቸግራል። በማንኛውም ሀገራዊ ምክክር ሁሉም ወገኖች የሚፈልጉትን ሙሉ በሙሉ አያገኙም። የምክክር መንፈስ የሚመሰረተው በመደማመጥ፣ በመቻቻልና ለጋራ ጥቅም በመስማማት ላይ ነው። የሀገራዊ ምክክሩ እውነተኛ ስኬት የሚለካውም በሚወጡት ሰነዶች ብዛት ሳይሆን በሚተገበሩት ውሳኔዎች ነው። ለዚህም መንግሥት፣የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማሕበራት እና ሕዝቡ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም (15 July 2026) በይፋ ከተከፈተ ጀምሮም ጉባኤው ኮሚሽኑ ባፀደቀው የአሠራር ሥርዓት መሠረት እየተካሄደ ይገኛል። ሰፊ ተሳትፎን፣ ግልጽነትን እና በተቀመጡ ሥርዓቶች መሠረት እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤው በአሁኑ ወቅት በውይይት ሂደቱ አስፈላጊ ምዕራፎች ላይ መድረሱን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
ከመላው ኢትዮጵያ ከየወረዳው የተውጣጡ ተወካዮች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፌዴራል መንግሥት ተቋማት፣ ከሲቪል ማሕበራት፣ ከኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ማሕበረሰብ፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች እና ከሌሎች የተደራጁ ማሕበራዊ ቡድኖች የተውጣጡ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በጉባኤው እየተሳተፉ ናቸው። ይህ ሰፊ ተሳትፎ የተለያዩ አመለካከቶችና ልምዶች በሀገራዊ ውይይቱ ውስጥ እንዲንጸባረቁ የሚያስችል አካታች መድረክ ተፈጥሯል። ምክክሮቹ በሀገራዊ ደረጃ በተለዩ ስምንት የአጀንዳ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው።
ኮሚሽኑ እንዳብራራው እያንዳንዱ ተሳታፊ በአንድ አጀንዳ ብቻ ተመድቦ በጉባኤው ቆይታ በሙሉ በዚያው የርዕስ ቡድን ውስጥ ይቆያል። እያንዳንዱ የርዕስ ቡድን በአማካይ 500 የሚደርሱ ተመካካሪዎችን ያካትታል፤ ይህም እያንዳንዱ አጀንዳ በጥልቀት እንዲመረመር እና በተከታታይ ውይይት እንዲታይ አስችሏል። የጉባኤው ተመካካሪዎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ በተዘጋጀ የተደራጀ የውይይት ዘዴ እየተመራም ነው።
ውይይቱ በ10 ሰዎች በተዋቀሩ አነስተኛ ቡድኖች ተጀምሮ፣ በ50 ሰዎች ወደተደራጁ ንዑስ ቡድኖች ተሸጋግሮ፣ 250 ተመካካሪዎችን ወደሚያካትተው ስልታዊ ቡድን አድጓል። ይህ ደረጃ በደረጃ የሚካሄድ ሂደት ተሳታፊዎች ሀሳብ እንዲለዋወጡ፣ የጋራ መግባባት የሚያስፈልጋቸውን ነጥቦች እንዲለዩ፣ የተለያዩ አመለካከቶችን እንዲያጠሩ እና ለቀጣይ ውይይቶች ጠንካራ መሠረት እንዲገነቡ አስችሏል።
ሂደቱም በ80 ገለልተኛ ባለሙያዎች ድጋፍ እየተከናወነ ነው። እነዚህ ባለሙያዎች ከእያንዳንዱ የምክክር ዙር በፊት ስለ አጀንዳዎቹ ተጨባጭ መረጃዎችን፣ ቴክኒካዊ ማብራሪያዎችን እና አስፈላጊ ገለጻዎችን ሰጥተዋል። የእነርሱ ሚና ተመካካሪዎች በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው እንዲመካከሩ ማስቻል እና የምክክሩን ነፃነት መጠበቅም ነበር።
ኮሚሽኑ እንደገለጸው ሌላው አስፈላጊ ምዕራፍ ደግሞ በጉባኤው የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅሮች ውስጥ የሚሳተፉ ተወካዮች መመረጣቸው ነው። ተወካዮቹ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከፌዴራል ተቋማት፣ ከወረዳ ፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማሕበራት፣ ከመምህራን፣ ከአንጋፋ ሀገር ወዳዶች እና ከመንግሥት ተቋማት የተውጣጡ ናቸው። በአጠቃላይ 330 ተወካዮች ለጉባኤው የውሳኔ ሂደት አስተዋጽኦ ለማበርከት ተመርጠዋል።
የውይይቱን ሂደት 160 ገለልተኛ አመቻቾች ሲመሩ፣ 158 ቃለጉባኤ ያዥዎች ደግሞ በውይይቶች የተነሱ ሀሳቦችን እና የተደረሰበትን ውጤት በሰነድ አስፍረዋል። ይህም ምክክሩ በተስማሙበት የአሠራር ሥርዓት መሠረት እንዲካሄድ እና የተመካካሪዎች አመለካከቶች በትክክል እንዲመዘገቡ አስችሏል።
ጉባኤውን ከኢትዮጵያ የሙያ እና ሲቪል ማሕበራት የተውጣጡ ታዛቢዎችም እየተከታተሉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ የእነርሱ ተሳትፎም የሂደቱን ግልጽነት፣ ክፍት መሆን እና ተዓማኒነት በማጠናከር የሕዝብ እምነት እንዲጎለብት አስተዋጽኦ አድርጓል። በአጠቃላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉባኤውን በተቀመጠው የአሠራር ሥርዓትና በመሪ መርሆቹ መሠረት ለማካሄድ ያለውን ቁርጠኝነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ነው ያሳወቀው።
ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ ዛሬ እየመከረች ያለችው የትናንት ችግሮችን ለመድገም ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ ሀገር ለመገንባት ነው። የምክክሩ ውጤት ምን እንደሚሆን ገና ባይታወቅም አንድ እውነት ግን ግልጽ ነው፤ በጦርነት የማይፈቱ ጉዳዮች በውይይት የመፍታት እድል አላቸው። ስለዚህ የዛሬው ሀገራዊ ምክክር የአንድ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የወደፊት አቅጣጫ ሊወስን የሚችል ታሪካዊ ሂደት ነው።፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


