በአብዛኛው ቀጥ፣ ዘና ብለው የሚቀመጡ ሰዎች ተደፍተው ወይም ዘመው ከተቀመጡቱ የበለጠ በአዎንታዊ ስሜት፣ ኃላፊነት መውሰድ እና ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚችሉ ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በካናዳ ማክጊል ዩኒቨርስቲ የተደረገ አዲስ ጥናት ውጤት እንዳመላከተው የሰዎች አቀማመጥ በስሜታዊ ሁኔታ እና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተፅእኖ ያሳርፋል፡፡
ለናሙና ጥናት የተመረጡ ተሳታፊዎች ከፊሎቹ ቀጥ ብለው እንዲቀመጡ ከፊሎቹ ደግሞ ቁጥጥር በተደረገበት፣ በተጐነበሰ ወይም በዘመመ አቀማመጥ ጥያቄ እንዲመልሱ እና በታብሌት ኮምፒውተር የሞባይል መተግበሪያን እንዲገመግሙ ተደርገዋል፡፡ በውጤቱም ከሁለቱ ቡድኖች ቀጥብለው እንዲቀመጡ የተደረጉት የበለጠ በአዎንታዊ ስሜት ኃላፊነት መውሰዳቸው እና መወሰናቸው ተረጋግጧል፡፡
ተመራማሪዎቹ በናሙና ጥናቱ ከፊል ተሳታፊዎቹን በተስተካከለ ጠረጴዛ እና ወንበር ተቀምጦላቸው ቀጥ ብለው እንዲቀመጡ አድርገዋል፡፡ ቀሪዎቹን ተሳታፊዎች ደግሞ በእጃቸው ታብሌት ኮምፒውተር ተሰጥቷቸው የስሌት ጥያቄ ወደ ፊት ዘመው ወይም አጐንብሰው እንዲሰሩ ነው ያስቻሏቸው፡፡
በሌላ ጥናትም ከፊል ተሳታፊዎች አጐንብሰው ፊኛ ወይም የኘላስቲክ ከረጢት በትንፋሻቸው እንዲነፉ ወይም በኃይል እንዲወጥሩ አድርገዋቸዋል፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ቀጥ ብለው ተቀምጠው የተሰጣቸውን የኘላስቲክ ፊኛ በሚችሉት አቅም ነፍተው እንዲወጥሩ አዘዋቸዋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ያስመዘገቡት ውጤት ሲመዘን ቀጥ ብለው ወንበር ላይ ተቀምጠው ፊኛ የነፉቱ የበለጠ መወጠር ችለዋል፡፡ አጐንብሰው ወይም ወደፊት ተደፍተው ፊኛ የነፉት ቀጥ ብለው ከተቀመጡት ያነሰ አፈፃፀም ነው ያስመዘገቡት፡፡
የዘመሙት ወይም ቀጥ ብለው ያልተቀመጡት ይፈነዳል፤ ይጐዳኛል ከሚል ውጤታቸው ዝቅ ማለቱን ተመራማሪዎቹ ተገንዝበዋል ፡፡ በመጨረሻም አቀማመጥ ውሳኔ አሰጣጥ እና ኃላፊነት መውሰድ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን ነው ያሰመሩበት – ተመራማሪዎቹ፡፡፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


