በየዓመቱ በእንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን ከየሀገራት በሚሰባሰቡ ባለሙያዎች መካከል ዓለም አቀፍ መስታውት የማጽዳት ውድድር እንደሚካሄድ ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል፡፡ድረ ገጹ እንዳስነበበው አሸናፊው የሚሆነው ሦስት አርባ አምስት ኢንች በአርባ አምስት ኢንች የተለኩ መስታዉቶችን በፍጥነት በአነሰ የጊዜ ምጣኔ አፅድቶ የጨረሰ ነው፡፡
በውድድሩ ሦስት ዳኞች የሚሰየሙ ሲሆን ዳኞቹ ከማጠናቀቂያ ጊዜ ቁጥጥር ባሻገር የተከሰቱ ስህተቶችን ቆጥረው የሚያስቀንሱትን ነጥብ አስልተው ውጤቱን ያሳውቃሉ፡፡ለውድድር ተሣታፊዎች ዘመናዊ “በ “T” ቅርፅ የተሰራ የመስታዉት ማፅጃ፣ የተበጠበጠ ኬሚካል የያዘ ውኃም ይቀርባል፡፡
ተዋዳዳሪዎቹ በ”ፐ” ቅረፅ ማፅጃው ከባልዲው ውኃ እየነከሩ በመስታዉቱ ላይ በ “ኤስ” ቅርፅ ፈጥነው በማዟዟር ማፅዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የማፅጃው እጄታ ርዝመት 14 ኢንች አግድም እጄታው ላይ በ “T” ቅርፅ የተያያዘው ስፖንጅም ርዝመቱ 12 ኢንች ተለክቷል፡፡
ቁሶቹ ለሁሉም የሚሰጡ ሲሆን ፈጥኖ ጥርት አድርጐ በአጭር ጊዜ ማጽዳት አሸናፊ ያደርጋል፡፡
እስከ አሁን በተደረጉ ዓለም አቀፍ መስታዉት የማጽዳት ውድድሮች በክብረ ወሰንነት የተያዘው በ2009 እ.አ.አ ቴሪ ብሮውስ በተባሉ ተሣታፊ የተመዘገበው ዘጠኝ ሰከንድ ከ14 ማይክሮ ሰከንድ ነው፡፡
ክብረወሰኑን እስከ አሁን መስበር ቀርቶ የቀረበ ውጤት ያስመዘገበ አለመኖሩንም ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡በውድድሩ ተወዳዳሪው በሚያፀዳው መስኮት ላይ ቀጭን ክር መሳይ መስመር ወይም የውኅ ጠብታ ከተገኘበት በዳኞች ዜሮ ነጥብ አምስት ሰከንድ ይቀጣል (ይጨመርበታል)፤ በመስታዉቱ ላይ ወፍራም መስመር ወይም ጭረት ካስቀረ ደግሞ አንድ ሰከንድ እንደሚጨመርበት እና እንደሚሰላ ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


