ያንጉዲ ራሳ ብሔራዊ ፓርክ

0
42

ያንጉዲ ራሳ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ በአፋር ክልል ነው የሚገኘው፡፡ ስፋቱ 4730 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡ የፓርኩ ቀጣና በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በጅቡቲ እና  ኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ነው የተካለለው፡፡

ለፓርኩ መመስረት በዋናነት በአፍሪካ የመጥፋት አደጋ ያንዣበበበትን የዱር አህያ መጠበቅ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡ የፓርኩ መልካምድር በአብዛኛው ሜዳ፣ ደረቅ የወንዝ ዳርቻ እና ኮረብታዎችን አካቷል፡፡ የፓርኩ ስያሜ መነሻ በቀጣናው ካለው የያንጉዲ ተራራ  እና በዙሪያው ያለውን የራሳ ሜዳ መሰረት ያደረገ ነው፡፡በፓርኩ ውስጥ የአዋሽ ወንዝ እና ወቅት ጠብቀው የሚፈሱ ሌሎች አነስተኛ ወንዞችም ይገኛሉ፡፡

በዝናብ ወቅት የወንዞች ዳርቻ ረግረጋማ በመሆኑ ሰፊው የፓርኩ ቀጣና የግራር ዛፍ እና ቁጥቋጦ የሚታይበት ሳር ለበስ ነው፡፡

ፓርኩ ደረቅ አካባቢን የሚላመዱ የዱር እንስሳት መኖሪያ ነው፡፡ እንደ ዜብራ መልኩ ከተዝጐረጐረው የዱር  አህያ በተጨማሪም የሜዳ ፍየል፣ ሳላ፣ ዝንጀሮ፣  ጥንቸል፤  ከአዳኞች አቦሸማኔ፣ ጅብ እና ቀበሮ፤ ከተሳቢ እንስሳት እባብ እና እንሽላሊት መገኘታቸው ተረጋግጧል፡፡

በፓርኩ ከዓዕዋፍ 230 ዝርያዎች እንደሚገኙም  ድረ  ገፆች  አስፍረዋል፡፡

የዓየር ንብረቱ በዓመት ውስጥ አብዛኛው ሞቃታማ እና ደረቅ ነው፡፡

ለጐብኚዎች ከመስከረም እስከ ጥር ያሉት ወራት ተመራጭ ናቸው ምክንያቱ ደግሞ እንደየወቅቶቹ ከሰሜን የሚፈልሱ አእዋፍን መመልከት ማስቻሉ ነው፡፡

የፓርኩ ዋና መስሪያ ቤት በገዋኔ ነው የሚገኘው፡፡ ለጐብኚዎች ማረፊያ በቅርበት በሚገኙት ገዋኔ፣ ሚሌ እና ዱብቲ ከተሞች ማግኘት ይቻላል፡፡

የፓርኩ የበላይ ተጠባባቂ አካል የኢትዮጵያ የዱር አራዊት ጥበቃ ባለስልጣን ነው፡፡ ለፓርኩ ዘላቂነት ልቅ ግጦሽ፣ የእርሻ መሬት መስፋፋት፣ የደን መመንጠር እና ህገወጥ አደን በስጋትነት ተጠቁመዋል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክ ዶት ኦርግ፣ ወርቅ አምባ ቱር ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

 

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 11   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here