በአሜሪካ የፍሎሪዳ ግዛት ኗሪዉ ታዳጊ ናታን ቶማስ በነሀሴ 2023 እ.አ.አ በ18 ዓመት ከ346 ቀናት እድሜው በሚያሚ ዳዴ ኮሌጅ በመምህርነት በማገልገል በእድሜ ትንሹ ኘሮፌሰር ሊሆን መቻሉን ዩፒአይ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡
ዓለም አቀፍ የድንቃድንቅ መዝጋቢ ድርጅት አሁን 21 ዓመት የሆነው ናታን ቶማስ በነሀሴ ወር 2023 እ.አ.አ 18 ዓመት ከ346 ቀናት ላይ ሳለ በእድሜ አነስተኛው ለኘሮፌሰርነት የበቃ ወጣት መሆኑን አረጋግጧል፡፡ናታን ቶማስ ክብረ ወሰኑን የነጠቀው በ19 ዓመቱ ለኘሮፌሰርነት ከበቃው ኮሉን ማክላሪን ነበር፡፡
ናታን ቶማስ በ10 ዓመት እድሜው በሚያሚ ዳዴ ኮሌጅ ተመዝግቦ በ14 ዓመቱ ወደ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ መዛወሩንም ድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ በ18 ዓመቱ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ “የማስተርስ” ዲግሪውን አግኝቷል፡፡
ናታን ቶማስ አሁን ላይ በርቀት (ኦንላይን) ትምህርት በማስተማር ላይ ሲሆን በህግ የዶክትሬት ዲግሪውን በመማር በ2028 እ.አ.አ እንደሚያጠናቅቅ ነው በድረ ገጹ የተብራራው፡፡
ትንሹ ኘሮፌሰር አሁን በመማር ላይ ያለውን የህግ ትምህርት ሲያጠናቅቅ በዓዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ላይ ለመስራት ወይም ለመሰማራት ማቀዱን ድረ ገጹ በማጠቃለያነት አስነብቧል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


