የሰላም ምሰሶዎች እንዴት ይጽኑ?

0
180

ከእጃችን ሳለ ተራና ቀላል ይመስላል፤ ስናጣው ደግሞ እንደ እግር እሳት ያንገበግባል፤ ምክንያቱም የሁሉም ስኬቶች መሠረት ነውና፡፡

አያያዝን እና ጥንቃቄን ይሻል፤ እንደ ቀልድ ከሾለከ ደግሞ መመለሻው ይቸግራል። እጅግ አስፈላጊ ነውና ብዙ መንግሥታት በእሱ ስም ተቋማትን ሰይመዋል። በርካቶችም መጠሪያ ስማቸው አድርገውታል – ሰላም!

“ቢቻላችሁስ  ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚለው የታላቁ መፅሐፍ (መፅሐፍ ቅዱስ) መሠረታዊ አስተምህሮም ለሁሉም ነገር ሰላም ወሳኝ ስለመሆኑ ያሳያል፡፡

ሰላም ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ የተለየ ትርጉም አለው፤ ከአንደበታችንም አይጠፋም፤  በማለዳው ሰላም  አደራችሁ?

በእኩለ ቀን “ሰላም አረፈዳችሁ? ጀምበር ስታዘቀዝቅ ደግሞ  ሰለም አመሻችሁ?  የሚል ከወዳጅ ልብ የሚመነጭ መልካም ምኞትን በየቀኑ  እንለዋወጣለን።

የታላቁን መጽሐፍ ቃል መሠረት በማድረግ የሀይማኖት አባቶችም በቤተሰብ፣ በጎረቤት አልፎም በሀገር ውስጥ ግጭቶች ሲፈጠሩ  ቀደመው በመድረስ የማስታረቅና የመገላገል  የቆየና የዳበረ ልምድ አላቸው።

በሀገራችን ሰላም ሲናጋ፤ ግጭቶች ሲበራከቱ ቀድመው የሚገኙት የሀይማኖት አባቶች ናቸው። የሀይማኖት መሪዎች ጥላ ዘርግተው መስቀል አቁመው የተራራቁትን በማቀራረብ፤ የተጋጭቱን በማስታረቅ፤ የበደለም ክሶ ተበዳይም ተክሶ፤ የጥል ግድግዳ ፈርሶ  ሰላም እንዲቆም  ያደርጋሉ።

ግጭቶች አድገው አፈሙዝ ሲያማዝዙም የሀይማኖት አባቶች ጣልቃ ገብተው በመምከርና በማስታረቅ ለጥፋት የተመዘዙ ሰይፎችን ወደ ሰገባቸው እንዲመለስ ማድረግ አባታዊ ኃላፊነታቸው ነው።

ይህንን ያዳበረ ልምድ መሰረት በማድረግ በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታትን ዙሪያ መንግሥትና የሀይማኖት ተቋማት  ተባብረው በመሥራታቸው ብዙ ግጭቶች ደርቀው ሰላም እንዲሰፍን አድርገዋል።

ሰሞኑንም የአማራ ክልል አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከተቋማት አመራሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በሰላም ግንባታ፤ በግጭት አፈታትና በመንግሥትና የሀይማኖት ተቋማት ግንኙት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

በመውይይቱ የተገኙት የሀይማኖት አባቶች እንደተናገሩት ምንግዜም የሀይማኖት ተቋማትና መንግሥት ተመጋግበውና ተደጋግፈው ነው የሚሥሩት፤ በሰላምና ግጭት አፈታት ላይም በጋራ እየሠሩ ነው።

ማንኛውም ዕምነት መሠረቱ ሰላም ነው፤ የሚሰብከውም ስለ ፍቅር ነው፡፡ ከ95 በመቶ በላይ የአማራ ክልል ነዋሪ ደግሞ አማኝ ነው፡፡ በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት ዙሪያ የሀይማኖት ተቋማት ከመንግስት ጋር በመሥራታቸው የተሻለ ውጤት መምጣቱን የውይይቱ ተሳታፊ የሀይማኖት አባቶች ተናግረዋል።

ህዝቡ  የእምነት አባቶችን አምኖ የመቀበል አዝማሚያው  ከፍተኛ ነውና ሰላም ለማምጣትና ግጭትን ለመፍታት መንግስት ከሀይማኖት አባቶች ጋር መሥራቱ ለሰላም ጉልህ ፋይዳ አለው።

የሀይማኖት አባቶቹ አክለውም የሀይማኖት ተቋማት ሰላም ላይ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው በማንሳት ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገራችን ሰላም አዲስ መሠረት እንዲጥል ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች ከጎጥ እና ከብሔር እሳቤ ወጥተው ሀገርን አስበው መመካከርና መልካም አሻራ ማሳረፍ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ ሰላምን በማፅናት ረገድ የሀይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀው  ይህንን አጠናክረው በማስቀጠልና ሰላምን ማፅናት  የውይይቱ ዓላማ እንደሆነ ተናግረዋል። ድክመቶች ካሉም አርሞ በቀጣይ አብሮ ለመሥራት መወያየት እንደሚገባ ገልፀዋል።

በክልላችን የሚታዩ ግጭቶች እንዲከስሙና  የሰላም ሁኔታው እንዲሻሻል የሀይማኖት ተቋማትና የእምነት አባቶች ሚናቸው ከፍ ያለ እንደነበር የገለፁት

ቢሮ አማካሪው በቀጣይም ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሀይማኖት አባቶች   የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ እና የችግሩን አሳሳቢነት  በመረዳት  ከመንግሥት ጋር በመተባበር በሠሩት የማግባባትና የመምከር ተግባር ግጭቶች እየረገቡና የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ እንዲመጣ  ሆኗል፤ ይህም ጠንካራ ሥራ መሠራቱን ማሳያ ስለመሆኑ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ ተናግረዋል።

ኮሎኔል ባምላኩ እንዳሉት የክልሉ መንግሥት ከሀይማኖት አባቶች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ አብረው እየሠሩ ነው፤ በሀይማኖት ተቋማት የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም መንግስት በቅርበት እየፈታ ይገኛል።

በተመሳሳይ የክልሉን ሰላም ለማስፈን የሀይማኖት ተቋማት በጎ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ መንግሥት ተገቢውን እገዛና ድጋፍ እያደረገ ነው፤ ድጋፉንም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

መንግሥት እና ሀይማኖት የተለያዩ ናቸው፤ መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ አይገባም፡፡  ቢሆንም ግን አብረውና ተባብረው የሚሠሩባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የሚጠቅሱት ኮሎኔል ባምላኩ ግጭትን ለመፍታትና ሰላምን ለመጠበቅ ሚዛናቸውን ጠብቀው አብረው እንደሚሠሩ አስረድተዋል።

ኮሎኔል ባምላኩ ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም ሲጠፋ አይደለም ተቋማት በግለሰብ ደረጃም እንኳን መኖር አይቻልም፤ ይህን በውል ተገንዝቦ ሁሉም የሰላም ጠባቂ ዘብ መሆን እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

በአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የሀይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለኸኝ መለሰ በበኩላቸው የሀይማኖት ተቋማትና የእምነቱ አባቶች ለግጭት አፈታትና ለሰላም መስፈን እንደ ምሶሶ የሚታዩ መሆናቸውን ነው ያነሱት።

የሀይማኖት ተቋማት እና መንግሥት በአወቃቀራቸው ቢለያዩም ለሀገረ ግንባታና በሰላም መስፈን ላይ በጋራ በመሥራት ጉልህ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

በሰላም ግንባታ፤ እርቅና ሽምግልና ላይ ተቀራርበው በመሥራት ሀገርን ማሻገርና የማልማት ተግባር ላይ የቆዬ አብሮነትም እንዳላቸው  አቶ አለኸኝ ጠቁመዋል።

የሕግ አንቀጥ

  • የግለሰብ ጥበቃዎች ከአንቀጽ 1 እስከ 11 እኩልነት ሁሉም የሰው ልጆች በነፃነት፣ በክብርና በመብት እኩል ሆነው ተወልደዋል ፤ እንዲሁም እነዚህን መብቶች ያለ ምንም ልዩነት የማግኘት መብት እንዳላቸው በዝርዝር ተቀምጧል።
  • ሕጋዊ ፍትሕ የማግኘት አንቀጽ 6 እስከ 11 በሕግ ፊት እንደ ሰው የመታወቅ መብት፣ ፍትሃዊ በሆነ ችሎት የመዳኘት መብት፣ የንፅህና ግምት  እና ያለ ሕግ አግባብ ከመታሰር የመጠበቅ መብት አለው ።
  • የሲቪል እና የፖለቲካ ነፃነቶች ከአንቀጽ 12 እስከ 2) ግላዊነት እና እንቅስቃሴ፣ የግል ሕይወት ጥበቃ (አንቀጽ 12)፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ እና ጥገኝነት የመጠየቅ መብት ፣ማንነት እና ቤተሰብ የዜግነት መብት በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡
  • ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ከአንቀጽ 22 እስከ 27 ደህንነት የማህበራዊ ዋስትና፣ እኩል ክፍያ የሚያስገኝ ሥራ የመሥራት እና በቂ የኑሮ ደረጃ (ምግብ፣ ቤት እና የጤና እንክብካቤን ጨምሮ) የማግኘት መብት መኖሩ ተዘርዝሯል።
  • እያንዳንዱ ሰው እነዚህ መብቶች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉበት የማህበራዊ ሥርዓት እንዲኖር የመጠየቅ መብት አለው።

 

(ግርማ ሙሉጌታ)

በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here