የስኬት ጅማሮ

0
190

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2019 ዓ/ም የትምህርት ዘመንን በተሻለ አቅጣጫ እንዲመራ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ከዕቅድ አዘገጃጀት ጀምሮ እስከ ሰው ኀይል፣ የትምህርት ቤት ግብዓትና የተማሪዎች ዝግጅት ድረስ እያጠናከረ መሆኑ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ይፋዊ የቴሌ ግራም ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ ቢሮው በቴሌ ግራም ገጹ ከዞን እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የክረምት የትምህርት ልማት ሥራዎች ልዩ ልዩ እቅዶችን በማቀድ ረገድ የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብ፣ትምህርት ቤቶችን ምቹ የመማሪያ አካባቢ ለማድረግ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሁም የማጠናከሪያ ትምህርት በተመረጡ የክፍል ደረጃዎች እና የትምህርት አይነቶች በበጎ ፈቃደኛ መምህራንና ወጣቶች እየተሰጠ መሆኑ አበረታች እንደሆነ ያስነብባል፡፡

በብዙ ዞኖችና ወረዳዎች ልዩ ልዩ መድረኮችን በመፍጠር የክረምት ሥራዎችን ከማህረሰቡ ጋር በመግባባት ለመፈጸም እየተደረገ ያለው ጥረት  እና  የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችም እንዳሉ ዘገባው ያብራራል፡፡ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል ከክልል እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ያለው የትምህርት ባለድርሻ አካላት ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ይገልጻል፡፡

እስካሁን ባለው በትምህርት መዋቅሩ ላይ ትልቅ መነሳሳት መፈጠሩን በመጥቀስ ለ2019 የትምህርት ዘመን ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑንም ያትታል፡፡ እቅድን በጥራት ማቀድ፣ የማጠናከሪያ ትምህርትን በስፋት መስጠት፣ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ማሻሻል፣ የመጽሐፍ ስርጭትን በትክክል መምራት፣ ለተማሪ ምዝገባ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እና አስፈላጊ ግብአቶችን ቀድሞ ማሟላት ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም መረጃው ጠቁሟል፡፡

በዚህ ረገድ የዞንና የወረዳ የዕቅድና በጀት ኃላፊዎች በ2019 የትምህርት ዕቅድ አዘገጃጀት ዙሪያ ሥልጠና መውሰዳቸው የዕቅድ አቅጣጫውን በአንድ መስመር ለማስጓዝ የተያዘውን ትኩረት እንደሚያሳይም ነው በቢሮው ቴሌግራም ገጹ የገለጸው።

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ አስራቴ  በዞኑ እየተደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት አሳውቀዋል፡፡ በ2019 የትምህርት ዘመን  በዞኑ 835 ሺህ 454 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በንቅናቄ ተጀምረዋል።

በዞኑ የትምህርት ቤቶችን  መሠረተ ልማት ማሟላት ከተሰጣቸው ትኩረቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት ኀላፊው 3 ሺህ 740 የተለያዩ የመማሪያ ክፍሎች ጥገና ተደርጎላቸዋል። በ2018 በጀት ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ 485 የመማሪያ ክፍሎችም ለ2019 ዓ/ም የመማር ማስተማር ሥራ ዝግጁ ማድረግ መቻሉን እና  የኮምባይንድ ዴስክና የጥቁር ሰሌዳ ጥገናዎችም መከናዎናቸውን ተናግረዋል።

 

የትምህርት ቤት ሀብትን ማሳደግም በዞኑ ከተያዙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አንዱ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በዚህም አንድ ሺህ 622 ሄክታር መሬት በማረስ ለትምህርት ቤቶች ገቢ ለማስገኘት ሥራ ተጀምሯል። በተማሪዎች ምገባ ረገድም ከአጋር አካላት እና ተቋማት ወደ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ሀብት እና ከ100 ኩንታል በላይ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች መሰብሰባቸው ተገልጿል።

በተማሪዎች ቁሳቁስ በኩልም ትልቅ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት። አራት ሺህ ደርዘን ደብተር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ባለው ጊዜ  ከ33 ሺህ ደርዘን በላይ ደብተር ተሰብስቧል። በተጨማሪም 6 ሺህ 158 ባኮ እስክርቢቶ፣ የደንብ ልብስና እርሳስ  መሰብሰቡንም ነው የተናገሩ። የተሰበሰበው የቁሳቁስ ሀብት በገንዘብ ሲተመን ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመትም ነው አቶ ደስታ ያብራሩት። ከዚህ በተጨማሪ ለቁሳቁስ መግዣ ከተለያዩ አካላት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት መሰብሰቡን ኃላፊው ጠቁመዋል።

የተማሪዎችን የትምህርት ውጤት ለማሻሻል የማጣቀሻ መጻሕፍት ማሰባሰብም ትኩረት ተሰጥቶት የተሠራ መሆኑን  ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ እስካሁንም ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚያገለግሉ አንድ  ሺህ 867 የተለያዩ መጻሕፍት መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህ ተግባርም የትምህርት ጥራትን ለማሳካት ያግዛል ነው ያሉ፡፡

በተያዘው ክረምት ከዚህ ሥራ ጎን ለጎንም ዘጠኝ ሺህ 368 የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እያገኙ መሆኑ ተገልጿል። ይህ ከታቀደው ቁጥር በላይ የተፈጸመ መሆኑ በትምህርት ሥራው ላይ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል።

በተመሳሳይ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ አቶ ሳሙኤል አለማየሁ እንዳሉት የትምህርት ቤቶች ጥገና፣ የግቢ ማስዋብ፣ የወንበርና የጥቁር ሰሌዳ ጥገና እንዲሁም የትምህርት ግብዓት ማሰባሰብ ሥራዎች ተከናውነዋል። ባለፈው ዓመት ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች በአጋር ድርጅቶችና በመንግሥት ድጋፍ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎላቸው የተማሪዎች ምገባ ተከናውኗል። በ2019 ዓ.ም ይህንን የምገባ አገልግሎት የበለጠ ለማስፋት ከመንግሥትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል። በተጨማሪም ወደ አምስት ሺህ ደርዘን የሚጠጋ ደብተር መሰብሰባቸውና 24 የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸው ተገልጿል። የግቢ ማስዋብና የማሳመር ሰራ መሰራቱንም ነው ምክትል ኃላፊው ያብራሩት፡፡

በአጠቃላይ የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ዝግጅት በአንድ ዘርፍ የተገደበ ሳይሆን በዕቅድ፣ በሰው ኀይል፣ በመሠረተ ልማት፣ የተማሪዎች ቁሳቁስ በማሰባሰብ፣ በምገባ፣ ለተማሪዎች አካዳሚክና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት በማስረጽ እንዲሁም የማህበረሰብ ተሳትፎን ያካተተ ሰፊ ሥራ ተከናውኗል።

በዚህ ሂደት የሚታየው ዋና መልዕክትም የትምህርት ዘመን ስኬት የሚጀምረው ተማሪው ወደ ክፍል ከገባ በኋላ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት በሚደረገው የተቀናጀ ዝግጅት መሆኑ ነው።

ቀጣዩ ፈተና ደግሞ የተዘጋጁትን ዕቅዶችና የተሰበሰቡትን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ውጤት መቀየር ነው። የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ የሚያሳዩት ትምህርት ቤቶችን ማስተካከልና ቁሳቁስ ማሟላት ብቻ ሳይሆን የትምህርት ሥርዓቱን በጠንካራ ዕቅድ፣ በተደራጀ ሰው ኀይልና በተማሪው ላይ በሚያተኩር አሠራር ለመምራት የተያዘ አቅጣጫ መኖሩን ነው።

ቀጣዩ ተግባር 2019  የትምህርት ዘመን የቢሮው፣ የዞኖችና ወረዳዎች፣ የትምህርት ቤቶች፣ የመምህራን፣ የወላጆችና የመላው ማህበረሰብ የጋራ ኃላፊነት ነው። በቅድመ ዝግጅቱ የተጀመረው ትብብር ወደ ትምህርት ቤት ሥራ ከተሸጋገረና የተያዙ ዕቅዶች በተግባር ከተፈጸሙ የትምህርት ሥርዓቱን ለማሻሻል የተያዘው ጥረት ተጨባጭ ውጤት ሊያስመዘግብ ይችላል። የትምህርት ዘመኑ ስኬት በመጨረሻ የሚለካው በተዘጋጁ ሰነዶች ወይም በተሰበሰቡ ግብዓቶች ብቻ ሳይሆን በተማሪዎች  ውጤት፣ በመምህራን የማስተማር ጥራትና በትምህርት ቤቶች የሚፈጠረው የተሻለ የመማር ማስተማር ምህዳር ነው።

ግዕዝ በአማርኛ

አልቦ         ዜሮ

አህዱ         አንድ

ክልኤቱ      ሁለት

ሠልስቱ      ሦስት

አርባዕቱ      አራት

ሐምስቱ      አምስት

ስድስቱ       ስድስት

ሰባዓቱ       ሰባት

ስመንቱ      ስምንት

ተሰዓቱ       ዘጠኝ

አሥርቱ      ዓሥር

 

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here