የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም 42 ሄክታር መሬት ይዞታ አለው። የስታዲየሙ ግንባታ የተጀመረው በ2002 ዓ.ም በ780 ሚሊየን ብር በጀት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
አብዛኛው የስታዲየሙ ስራም “ተጠናቋል” በሚል የተለያዩ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ተስተናግደውበታል። ከዚህ ባለፈም አኀጉራዊ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ተካሄደውበታል።
ይሁን እንጅ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጥቅምት 7/2014 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ስታዲየሙን ተመልክቶ አኀጉራዊ ጨዋታዎች እንዳይደረጉበት አግዶታል።
“ይህ ግዙፍ ስታዲየም ምን ምን ጉዳዮች ስላልተሟሉለት ነው በካፍ የታገደው?” መባሉ አይቀርም።
ካፍ በእግድ ደብዳቤው ላይ በዋናነት የስታዲየሙ የመጫወቻ ሣር ደረጃውን የጠበቀ አለመኾኑን አስታውቋል። ስለኾነም ሣሩ በተፈጥሮ ሣር መቀየር እንዳለበት ምክረ ሐሳብም አስቀምጧል።
አንድ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለውድድር ብቁ ከሚያስብሉት ጉዳዮች አንዱ ጨዋታዎችን በምሽትም ማስተናገድ ሲችል ነው ያለው ካፍ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከዚህ አንጻር ከደረጃ በታች በመኾኑ ጨዋታዎችን ማስተናገድ አይችልም ብሏል።
ደረጃቸውን ያሟሉ የመልበሻ ክፍሎች እንዲኖሩትም ካፍ ጠይቋል።
ተመልካቹ ዘና ብሎ ጨዋታዎችን የሚያይበት ምቾት ያለው ወንበር፣ እንግዶች በሚገኙበት ቦታ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ ቴሌቪዥን እና የድምጽ ሲስተም፣ የሚዲያ ክፍሎች፣ የመኪና ማቆሚያ፣ በምሽት ሳይቀር ልምምድ ሊያሠራ የሚችል ሜዳ እና ሌሎች ጉዳዮች አለመኖር ለባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመታገድ ምክንያት ናቸው ብሏል ካፍ።
የአማራ ክልል መንግሥትም የተባሉትን ጉዳዮች በጸጋ ተቀብሎ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመመደብ የካፍን ብቻ ሳይኾን የዓለም አቀፉን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ)ንም ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ሊመልስ የሚችል ሥራ አከናውኖ እያጠናቀቀው ይገኛል።
ካፍ በእጥረት ያነሳቸውን ብቻ ሳይኾን ነገ ላይ ሊጠይቅ የሚችለውን ጥያቄ ታሳቢ በማድረግ ቀሪ ሥራዎችን ወደ ማጠናቅ ተደርሷል።
ከዋናው የእግር ኳስ መጫዎቻ ሜዳ በተጨማሪ በቅጥር ግቢው ሁለት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎች ተሰርተዋል። ዋናውን ሜዳ ጨምሮ በተመሳሳይ ሰዓት ሦስት ጨዋታዎችን ማስተናገድም ያስችላሉ።
ሜዳዎቹ የውሃ ሥርገት መከላከያ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ “ግሪጎሪ” በተባለ ዕውቅ የፈረንሳይ ኩባንያ ተሰርቶላቸዋል።
ይህ ኩባንያ “ግሪጎሪ” ደግሞ 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በአስደማሚ ኹኔታ የተካሄደባቸውን የኮትዲቮር ምርጥ ስታዲየሞችን የገነባ ኩባንያ መኾኑን ልብ ይሏል።
በካፍ ጥያቄ መሠረት ስታዲየሙ ለመለማመጃ እና ለውድድር የሚያገለግሉት ሜዳዎች ለሴት እና ለወንድ ተጫዋቾች፣ ለዳኞች፣ ለኳስ አቀባዮች የልብስ መቀየሪያ ክፍሎች በልዩ ኾኔታ ተዘጋጅተውለታል።
ደረጃቸውን የጠበቁ የመታጠቢያ እና የመጸዳጂያ ክፍሎችንም ይዟል።
ስታዲየሙ አራት ቡድኖች በአንድ ጊዜ የስፖርት ትጥቅ ሊቀይሩባቸው የሚችሉ ዘመናዊ እና ምዕሉ ክፍሎችም አሉት፡፡
በአንድ ጊዜም 23 የተለያዩ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንዲችል ኾኖ ነው አሁን ላይ እየተጠናቀቀ የሚገኘው።
ይህ ውብ እና ዘመናዊ ስታዲየም ሙሉ በሙሉ ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ200 በላይ ለሚኾኑ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችም ቋሚ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል ነው የተባለው ።
ስታዲየሙ የስፖርት ቁሳቁስ መሸጫ ሱቆችንም በመያዝ
ሁለገብ አገልግሎቶችን ይሰጣል ተብሏል።
ጨዋታ ሲኖር ብቻ የሚከፈት ሳይኾን ጨዋታ በሌሉባቸው ቀናትም የተለያዩ አገልጋሎትን እንዲሰጥ ኾኖ ነው ግንባታው እየተሳለጠ የሚገኘው፡፡
ሻይ እና ቡና የሚሸጡባቸው ካፍቴሪያዎች እና ጅም ቤቶችም በወጉ ተደራጅተዋል።
የጅም ቤቶች አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ደረጃቸውን የጠበቁ የፉት ሳል ሜዳ፣ የአንፊ ቴዓትር፣ የብስክሌት መጋለቢያ፣ የአዋቂዎች እና የታዳጊዎች የውኃ መዋኛ ገንዳዎች፣ የሜዳ ቴኒስ እና የጠረጴዛ ኳስን ሊያጫውት በሚችል መልኩ ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል።
120 የመገናኛ አውታሮችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችሉ ዘመናዊ ክፍሎችም ተለይተው እየተሠሩለት ነው ።
የቀጥታ ሥርጭት እና ለጦማሪያን (ብሎገሮች) አገልግሎት መስጫ የሚኾኑ ክፍሎችም ከተሟላ የኢንተርኔት መሥመር ጋር እየተዘረጋለት ይገኛል_የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም።
ልዩ የክብር እንግዶች የሚገቡበት እና የሚወጡበት የተለየ በር እና አሳንሰር(ሊፍት) አለው።
ጨዋታዎችን በምሽት ጭምር ማስተናገድ የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ መብራት እና ግቦቹን በምልሰት የሚያሳዩ እንዲሁም ግቦችን እና የጨዋታውን ሰዓት የሚያሳዩ ግዙፍ ስክሬኖችም እየተገጠሙለት ይገኛሉ።
የባሕር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም በፀሐይ እና በዝናብ የማይበላሽ ዘመናዊ ወንበር የመግጠም ሥራውን በሜድሮክ-ኢትዮጵያ ሥር ያለ “አዲስ ጋዝ” የተሰኘ ንዑስ ተቋራጭ በግሩም ኹኔታ አከናውኖታል።
ወደ ስታዲየሙ የሚያስገቡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ሁለት በሮች ወደ አምስት እንዲያድጉም ተደርገዋል።
የስታዲየምን ደህንነት የሚጠብቁ በርካታ እጅግ ዘመናዊ የሲሲሲቲቪ ካሜራዎች እና የዲጂታል ቲኬቲንግ መቆጣጠርያም እየተገጠመለት ይገኛል።
የተገጠመው ወንበር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የዓለም ዓቀፉን እግር ኳስ ማኀበር (ፊፋ) የደረጃ መስፈርትን ያሟላ ነው፡፡
ይህ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከእግር ኳስ ጨዋታ ባሻገር ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ተዋቂዋ አትሌት መሠለች መልካሙ ለአሚኮ መናገሯ ይታዎሳል።
አትሌቶች የሩጫ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የሚያበቃን ሰዓት ለማሟላት ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ስለሌለ በሌሎች ሀገራት ሄደው ልምምድ እንደሚያደርጉ ነው አትሌት መሠለች ያስታዎሰችው።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በመገንባቱ በተለያዩ ርቀቶች የሚሳተፉ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድር ለመሳተፍ የሚያበቃቸውን ሰዓት ለሟሟላት ወደ ውጭ ሀገር ሄደው መለማመድን ያስቀርላቸዋል ነው ያለችው።
አትሌቶቹ ሰዓት ለማሟላት የሚሄዱባቸው ሀገራት በጣም ሞቃት ወይም በጣም ቀዝቃዛ እንደሚኾኑ የተናገረችው አትሌት መሠለች ይሄ ደግሞ በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ነው ያለችው፡፡
በሀገራችን ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ሲኖር ግን አትሌቶች በተመሳሳይ ቦታ እና በተመሳሳይ የአየር ንብረት በመለማመድ ተወዳድረው ሀገራቸውን አሸናፊ ማድረግ አይሳናቸቸውም ብላለች አትሌት መሠለች።
ለዚህ ደግሞ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መጠናቀቅ የነበረውን ችግር ያስወግደዋል ነው ያለችው።
ከሰሞኑም ካፍ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታዎችን ማድረግ የሚያስችለውን “የደረጃ ሦሥት” ፍቃድ መሥጠቱን የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ ጋሻው ተቀባ ተናግረዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም “ስታዲየሙ ዕውቅና ያገኘው በካፍ እንዲስተካከሉ የተሰጡትን አስተያየቶች በአግባቡ በማስተካከል ነው” ብለዋል።
የካፍን መስፈርቶች በመከተል ስታዲየሙ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ እንዲኾን በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አቶ ጋሻው ጠቁመዋል።
የተሰሩት ስራዎች ውጤታማ በመኾናቸው በካፍ ዕውቅና ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
(ሙዋሊሙ)
በኲር የነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


